ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ መፈጸም ''እየተለመደ መጥቷል''

በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ የግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ኃይል የመጠቀም ዝንባሌ እየተለመደ መምጣቱን አንድ ጥናት አመላከተ።
በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ከተሳተፉ 42 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች፤ በፈቃድ ላይ በተመሰረተ የግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ምቾት የሚነሳ ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ ቢያንስ አንድ ግዜ ፈጽመናል ብለዋል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች በተለያዩ ወቅቶች በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት በጥፊ መመታት፣ አንገት ታንቆ መያዝ፣ ጨርቅ አፍ ውስጥ መጠቅጠቅ እና ምራቅ እንደተተፋባቸው ገልጸዋል።
ይህን መሰል ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ ከፈጸሙ ሴቶች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ መፈጸማቸው ፍርሃት እንዲሰማቸው አድርጓል ወይም ብስጭት ውስጥ ከትቷቸዋል።
የ23 ዓመቷ ወጣት የሆነችው አና፤ በፍላጎቷ ከሶስት የተለያዩ ወንዶች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ወሲብ ስትፈጽም ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ አጋጥሟታል።
እርሷ እንደምትለው በወሲብ ወቅት ኃይል መጠቀም የጀመረው ፀጉሯን መጎተት እና በጥፊ በመመታት ነበር። ከወንዶቹ አንዱ አንገቷን በክርኑ አንቋት እንደነበር ትገልጻለች።
"በጣም ተደናገጥኩ" የምትለው አና፤ "በከፍተኛ ሁኔታ ምቾት ነሳኝ፤ ፈራሁኝ። አንድ ሰው በመንገድ ላይ አንገትህን ቢያንቅህ ወይም በጥፊ ቢመታህ ወንጀል ነው" ስትል የተፈጠረባትን ስሜት ትገልጻለች።
አና ስለደረሰባት ነገር ከሴት ጓደኞቿ ጋር ስታወራ ነበር ይህ መሰል ተግባር ብዙዎችን እንደሚያጋጥም የተረዳችው።
"ሁሉም ወንዶች ቢያንስ አንድ አይነት መልክ ያለው ኃይል የተቀላቀለበት ተግባር ለመፈጸም ይሞክራሉ" ትላለች።
አና በወሲብ ወቅት በሚያጋጥማት ኃይል የተቀላቀለበት ተግባር ለቀናት ህመም እንደሚሰማት እና ፊቷ በልዞ የሚቀርበት ሁኔታዎች ተፈጥረው እንደነበረ ታስታውሳለች።
"አንዳንድ ሴቶች ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ መፈጸም ሊያስደስታቸው እንደሚችል እገምታለሁ። ችግሩ ግን ወንዶች ሁሉም ሴቶች ሊያስደስታቸው እንደሚችል ማሰባቸው ነው" ትላለች አና።
ሳቫንታ ኮምሬስ የተሰኘ አጥኒ ኩባንያ እድሜያቸው ከ18-40 በሆኑ እና በዩናይትድ ኪንግደም በሚኖሩ 2002 ሴቶች ላይ ነው የዳሰሳ ጥናት ያካሄደው።
በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ከተሳተፉ ሴቶች መካከል 8 በመቶ የሚሆኑት በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ የግብረ ስጋ ግንኙነት ባደረጉ ቁጥር በወንድ አጋራቸው በጥፊ መመታት፣ መታነቅ፣ ጨርቅ አፋቸው ውስጥ በመጠቅጠቅ እንዲታፈኑ ማድረግ እና መረቅ እንደሚተፋባቸው ተናግረዋል።
12 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ይህን መሰል ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ እንደሚፈጽሙ የተናገሩ ሲሆን፤ 22 በመቶ የሚሆኑት አልፎ አልፎ ያጋጥመናል ብለዋል።
56 በመቶ በበኩላቸው ይህን መሰል ኃይል የቀላቀለበት ወሲብ ፈጽመው እንደማያውቁ የተናገሩ ሲሆን፤ 2 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አስተያየታቸውን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሳቫንታ ኮምሬስ በጥናቱ ላይ የተሳተፉት ሴቶች እድሜና የሚኖሩበት አካባቢ መላው ዩናይትድ ኪንግደምን ይወክላል ብሏል።
31 በመቶ የሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ መፈጸም ፈጽሞ እንደማይፈልጉ የተናገሩ ሲሆን፤ 38 በመቶ የሚሆኑት ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ ሁሌም መፈጸም እንደማያስደስታቸው ገልጸዋል።
የሴቶች ፍትህ ማዕከል የተሰኘ ተቋም የጥናቱን ውጤት በማስመልከት ለቢቢሲ "ይህ ቁጥር ወጣት ሴቶች ለሚያዋርዷቸው ድርጊቶች ፈቃዳቸውን እንዲሰጡ የሚደረግን ግፊት ያሳያል" ብሏል።
በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ኤማ ለረዥም ዓመታት ከቆየችበት ግንኙነት በቅርቡ ተለያይታለች።
"ወሲብ እየፈጸምን ሳለ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ያንቀኝ ጀመር። በጣም ነበር የተደናገጥኩትና የፈራሁት። በወቅቱ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር፤ ምክንያቱም ይህ ሰው በጉልበት ይበልጠኝ ስለነበር ነው"
ኤማ ይህ አይነት ኃይል የተቀላቀለበት ተግባር ልቅ የሆኑ የወሲብ ፊልሞችን ከመመልከት ሊመነጭ እንደሚችል ትገምታለች።
ስቴቨን ፖፕ የስነ-አእምሮ ሃኪም ሲሆን ከወሲብ እና ግንኙነት ጋር የህክምና አገልግሎት ለታካሚዎቹ ይሰጣል።
"ሰዎች ይህን ኃይል የተቀላቀለበት ተግባር የሚፈጽሙት የተለመደ ነገር እንደሆነ አድርገው ስለሚያስቡ ነው። ይህ ግን በጣሙን ጎጂ ልማድ ነው። የጥንዶችን ግንኙነት ዝቅ ከማድረጉም በላይ በግንኙነት ውስጥ ኃይል ተቀባይነት እንዲኖረው ያደርጋል" ይላል የስነ-አእምሮው ሃኪሙ ስቴቨን።

















