ቲማቲም የወንዶችን የዘር ፍሬ ያበረታ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊኮፒን የተባለው በቲማቲም ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር የወንዶችን የዘር ፍሬ ጥራትና አቅም በእጅጉ ሊጨምረው እንደሚችል አንድ ጥናት ጠቆመ።
በእንክብል መልክ የተዘጋጁ የቲማቲም ተዋጽኦዎችን እንዲጠቀሙ የተደረጉ ጤናማ ወንዶች፤ የዘር ፍሬያቸው የተሻለ ጥራት ማሳየቱን ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎች ገልጸዋል።
የሥነ ተዋልዶ ባለሙያዎች እንደሚሉት ጥናቱን ለማካሄድ የተለያዩ የመውለድ ችግር ያሉባቸውን ወንዶች ተጠቅመዋል።
የመውለድ ችግር ያለባቸው ወንዶች ጤናማ የሆነ ሕይወት እንዲከተሉና አጥብቀው የሚይዙ የውስጥ ልብሶችና ሱሪዎችን ከመልበስ እንዲቆጠቡ የእንግሊዝ ጤና አገልግሎት ድርጅት ይመክራል።
በተጨማሪም በተቻለ መጠን ጭንቀትን መቀነስና የፍቅር አጋራቸው እንቁላሎችን ማምረት በምትጀምርባቸው ጊዜያት አዘውትሮ ግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም የመውለድ ዕድልን ከፍ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
ነገር ግን የተለያዩ ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገሮችን በመጠቀም የወንዶችን የመውለድ አቅም የመጨመር ሃሳቦች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቀባይነትን እያገኙ የመጡ ይመስላል።
ሊኮፒን ልክ እንደ ቫይታሚን ኢ እና ዚንክ በቅርቡ ብዙ ጥናት እየተሠራበት ነው። ሊኮፒን የወንዶችን የዘር ፍሬ አቅም ከመጨመር ባለፈ ብዙ ጤና ነክ ጥቅሞች እንዳሉት እየተገለጸ ነው።
ከነዚህ መካከል የልብ ህመምን ለመከላከልና አንዳንድ የካንሰር ዓይነቶችን ቀድሞ ለመከላከል ያለው ጥቅም ብዙ እየተባለለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቲማቲም ውስጥ የሚገኘውን ሊኮፒን ሰውነታችን በቀላሉ ፈጭቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ስለሚቸገር ተመራማሪዎቹ ንጥረ ነገሩን በሳይንሳዊ መንገድ ከሰበሰቡ በኋላ በጥናቱ ለተሳተፉት ወንዶች በየቀኑ በእኩል መጠን አከፋፍለዋል።
በተጨማሪም በቂ የሆነ ሊኮፒን ሰውነታቸው እንዲያገኝ በየቀኑ 2 ኪሎ የበሰለ ቲማቲም መመገብ ነበረባቸው።
ለ12 ሳምንታት በቆየው የሙከራ ጥናት 60 ወንዶች ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን ከበሰለው ቲማቲም ጎን ለጎን 14 ግራም የሚመዝን በሳይንሳዊ መንገድ የተዘጋጀ የሊኮፒን እንክብል እንዲወስዱ ተደርገዋል።
ምርምሩ ሲጀመር፣ በስድስተኛው ሳምንትና በጥናቱ መጨረሻ ላይ የተሳታፊዎቹ የዘር ፍሬዎች ተመርምረዋል። በዚህም መሠረት የዘር ፍሬ ቁጥር ላይ ምንም ጭማሪ ባይታይም የዘር ፍሬዎቹ እንቅስቃሴ ላይ ግን ከፍተኛ ለውጥ መታየቱ ተገልጿል።
ቲማቲም እንዲመገቡ የተደረጉት ወንዶች የዘር ፍሬዎች ጤናማ ቅርጽ ያላቸው ሲሆን በፍጥነት መዋኘትና ጽንስ መፍጠር የሚችሉ ሆነው ስለመገኘታቸው ደርሰንበታል ብለዋል ተመራማሪዎቹ።
''በዚህ ሰዓት ለወንዶች ልንሰጣቸው የምንችለው ምንም ዓይነት ምክር የለም'' ብለዋል በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሼፊልድ የሥነ ምግብ ባለሙያ የሆኑትና ጥናቱን በዋናነት ሲመሩ የነበሩት ዶክተር ሊዝ ዊሊያምስ።
''ምናልባት የሚጠጡትን የአልኮል መጠን እንዲቀንሱና ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲከተሉ ልንነግራቸው እንችላለን፤ ነገር ግን ይህ በጣም ጠቅለል ያለ ምክር ነው።'' ብለዋል።
ዶክተር ሊዝ አክለውም የምርምር ሥራው ገና ብዙ የሚቀሩት ነገሮች ስላሉ በሰፊው ሙከራ ሊደረግበት እንደሚገባም አሳስበዋል። ነገር ግን እስካሁን የተገኘው ውጤት አበረታችች መሆኑን ግን አልሸሸጉም።
ከዚህ በመቀጠል የሚጠበቀው በሙከራው የተሳተፉ ወንዶች የዘር ፍሬዎች ጤናማ ከመሆን ባለፈ ጽንስ እንዲፈጠር የማድረግ አቅማቸው ምን ያክል እንደሆነ መመርመር እንደሆነ ዶክተር ሊዝ ገልጸዋል።













