ለሰው ልጅ ምርጡ ምግብ እንቁላል ይሆን?

እንቁላል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰው ልጅ ከሚበላቸው ምግቦች መካከል እጅግ ፍጹም የሆነውን ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል፤ እንቁላል ግን ለፍጹምነት የቀረበ የምግብ አይነት እንደሆነ ይነገርለታል።

እንቁላል በቀላሉ መገኘት ይችላል፣ በቀላሉ መብሰል ይችላል፣ ዋጋውም ርካሽ የሚባል ሲሆን ለሰውነታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ፕሮቲንንም በብዛት ይዟል።

በዩኒቨርሲቲ ኦፈ ከነቲከት የሥነ ምግብ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ክሪስቶፈር ብሌሶ እንደሚሉት እንቁላል ሁሉም አይነት አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች ያሉት ሲሆን፤ አንድን ፍጥረት በተገቢው ሁኔታ ለማሳደግ ብቻውን በቂ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

ከዚህ በተጨማሪ እንቁላልን ከሌሎች ምግቦች ጋር ቀላቅሎ መመገብ ሰውነታችን ቫይታሚኖችን በቀላሉ ለመሰብሰብ ያስችለዋል። ለምሳሌ አንድ ጥናት እንደጠቆመው እንቁላልን ከአትክልት ጋር መመገብ በአትክልቱ ውስጥ ያለውን ቫይታሚን ኢ የመሰብሰብ ሥራን ቀላል ያደርገዋል።

ነገር ግን በእንቁላል ውስጥ ያለው የኮሌስትሮል መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ለብዙ ዓመታት መከራከሪያ ሆኖ ቆይቷል። ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ደግሞ ለልብ በሽታዎች ያጋልጣል።

በእንቁላል ውስጥ የሚገኘው አስኳል እስከ 185 ሚሊግራም የሚደርስ ኮሌስትሮል በውስጡ ይይዛል።

ይህ ማለት እንቁላል ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ማለት ነው?

ኮሌስትሮል በጉበታችንና በጨጓራችን ውስጥ የሚመረት ቢጫ ቀለም ያለው 'ፋት' (ጮማ) ሲሆን በእያንዳንዱ የሰውነታችን ሴሎች ውስጥ ይገኛል። ብዙዎቻችን መጥፎ ነገር እንደሆነ እናስባለን። ነገር ግን ኮሌስትሮል ሴሎቻችንን ሸፍኖ ከተለያዩ ነገሮች ይጠብቃቸዋል። ከዚህ ባለፈም ቫይታሚን ዲ ለማምረትና እንደ ቴስቴስትሮን እና ኦስትሮጅን ያሉ ሆርሞኖችን ለማማንጨት ይረዳል።

ምንም እንኳን ሰውነታችን ኮሌስትሮልን በራሱ ማማረት ቢችልም ከተለያዩ የእንስሳት ምርቶችም ሊያገኝ ይችላል። ለምሳሌ የበሬ ሥጋ፣ እንቁላል፣ አይብ እና ቅቤን መጥቀስ ይቻላል።

መርሳት የሌለብን እንደ ልብ በሽታ ላሉ ከፍተኛ የጤና እክሎች የሚያጋልጠን ኮሌስትሮል በተፈጥሯዊ መንገድ የሚመረተው ሳይሆን፤ ሰው ሰራሽ የሆነው በተጠበሱ ምግቦች፣ ኬኮችና ሌሎችም ውስጥ የሚገኙት ናቸው።

በእንቁላል ውስጥ የሚገኘው የኮሌስትሮል መጠን ከተለያዩ የእንስሳት ምርቶች የበለጠ ቢሆንም የስብ (ፋት) ክምችቱ ግን በጣም አነስተኛ ነው። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ደግሞ ይህ የስብ ክምችት የደም ቧንቧችንን በመድፈን ለልብ በሽታ ሊያጋልጠን ይችላል።

እንቁላል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቦስተን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ኤሊዛቤት ጆንሰን እና ባልደረቦቻቸው በሰሩት ጥናት መሰረት ከቀጥተኛ የእንስሳት ተዋጽኦ የምናገኘው ኮሌስትሮል ለልብ ህመም እንደሚያጋልጥ ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም።

ሰውነታችን ኮሌስትሮልን እንደ እንቁላል ካሉ ምግቦች ማግኘት ከቻለ በራሱ የሚያመርተውን መጠን መቀነስ ይችላል። ይህ ማለት ደግሞ ተፈጥሯዊው ኮሌስትሮል መቼም ቢሆን በሰውነታችን ውስጥ መኖር ካለበት መጠን አያልፍም ማለት ነው።

የዘርፉ ባለሙያዎች በቅርቡ በሰሩት ጥናት እንቁላል ምንም አይነት የጤና እክል እንደማያስከትል አረጋግጠናል እያሉ ነው። ተመራማሪዎቹ ባለፉት 17 ዓመታት 30 ሺህ ሰዎች ስለተመገቧቸው ምግቦች የሚያትቱ መረጃዎችን ሲያሰባስቡ ነበር።

በጥናቱም መሰረት በየቀኑ እንቁላል የሚመገቡ ሰዎች በተለያዩ የልብ በሽታዎች የመሞት እድላቸው 18 በመቶ የቀነሰ መሆኑን የደረሱበት ሲሆን በደም ግፊት የመያዝ እድል ደግሞ እንቁላል ከማይመገቡት ጋር ሲነጻጸር 28 በመቶ የቀነሰ ነው።

ምንም አንኳን እርግጠኛ ሆኖ መደምደም ባይቻልም እንቁላል ከጉዳቱ ጥቅሙ እንደሚጎላ መገመት ቀላል ነው። በእንቁላል ውስጥ የሚገኘው ኮላይን የተባለው ንጥረ ነገር የመርሳት በሽታን ለመከላከልና ጉበታችን ከጎጂ ነገሮች ለመከላከል ይረዳል።