በርካታ ኬንያውያን ለምን ኮሮናቫይረስ የለም ብለው ያምናሉ?

ኬንያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሳይንስን የተመረኮዘው ዓለም አቀፍ መረጃ እንደሚያሳየው ወደ 600,000 ሰዎች በኮቪድ-19 ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ሆኖም ግን ኬንያ ውስጥ አንድ ሰው “ኮሮናቫይረስ ይዞኛል” ቢል ውሸታም ወይም የመንግሥት ቅጥረኛ ሊባል ይችላል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ከበሽታው አገግማ ከሆስፒታል የወጣችው አይቪ ብሬንዳ ሮቲችን ብዙዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ሲያብጠለጥሏት ነበር።

መንግሥት፤ ሕዝቡን ስለ ኮሮናቫይረስ መኖር ለማሳመንና ድጎማ ለማግኘት ሲል አይቪን እንደመለመለ ብዙዎች ያምናሉ።

በሽታው መሰራጨት በጀመረበት ወቅት፤ ኮቪድ-19 አፍሪካውያንን አይዝም የሚል የተሳሳተ እሳቤ ነበር።

አሁን ላይ ኬንያ ውስጥ 11,000 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙና 200 ሰዎች እንደሞቱ ሪፖርት ቢደረግም፤ ኮሮናቫይረስ የሚባል ወረርሽኝ የለም ብለው የሚያምኑ ጥቂት አይደሉም።

አንድ መኪና አጣቢ “ኮሮናቫይረስ የዘመናችን ትልቁ ውሸት ነው” ሲል፤ አንዳንድ ጋዜጠኞች ደግሞ “ዘለግ ያለ ጊዜ የወሰደ ጉንፋን ነው” ይላሉ።

ፓስተር ሮበርት ቡራሌ የተባሉ ታዋቂ ተናጋሪ፤ በበሽታው ተይዘው ናይኖቢ ሆስፒታል ቢገቡም፤ የምርመራ ውጤታቸው የሐሰት ነው የሚል ወሬ ተናፍሷል።

ቤንሰን ሙሱንጉ የተባሉ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ፤ በጽኑ ህሙማን ማቆያ ለ15 ቀናት ህክምና ተደርጎልኛል ብለው እንዲዋሹ መንግሥት ገንዘብ ከፍሏቸዋል የሚል የተሳሳተ መረጃ መሰራጨቱም አይዘነጋም።

መሰል ወሬዎች በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች እውነታውን እንዳይናገሩ ጫና እያሳደሩ ነው።

“የሕዝብ እንደራሴዎች ጥርጣሬ እያጫሩ ነው”

ፖለቲከኞችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በቫይረሱ ቢያዙም፤ ማኅበረሰቡ ያገለናል ብለው ስለሚፈሩ የምርመራ ውጤታቸውን ለሕዝብ አያሳውቁም።

ስለበሽታው በግልጽ የሚናገሩ ጥቂቶች ናቸው። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ “እርስዎ ወይም የሚወዱት ሰው በኮቪድ-19 ተይዟል? ተብሎ ሲጠየቅ” የበርካቶች መልስ “በፍጹም” ነው።

የእነዚህን ሰዎች ጥርጣሬ ያጎላው የሕዝብ እንደራሴ ጁድ ንጆሞ ሐምሌ ላይ ለፓርላማ አባላት ያደረጉት ንግግር ነው። እናታቸው ከሞቱ በኋላ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ስለተረጋገጠ በሌሊት፣ በአስቸኳይ ለመቅበር መገደዳቸውን ለፓርላማው የጤና ዘርፍ ኮሚቴ አስረድተዋል።

“ጊዜ እንዲሰጠን ለምኜ ነበር፤ ነገር ግን በአስገዳጅ ሕጉ ምክንያት ዘጠኝ ሰዓት ላይ መረጃው ደርሶን፣ ማታ ሁለት ሰዓት እንድንቀብር ተደረገ፤ ለ82 ዓመታት ሕይወቷ የሚመጥን ሽኝት አላደረግንም” ብለዋል።

የሕዝብ እንደራሴው እናታቸውን ከቀበሩ በኋላ ስለ ኢንፍሉዌንዛ ለሚያጠና ማዕከል እና ለናይሮቢ ሆስፒታል ናሙና ሰጥተው፤ ሟቿ ኮሮናቫይረስ እንዳልያዛቸው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

የኬንያ የህክምና ምርምር ተቋም የምርመራ ውጤት፤ ቫይረሱ መኖሩንም አለመኖሩንም ሊያሳይ የሚችልበት እድል እንዳለ ለማስረዳት ሞክሮ ነበር። ሆኖም የሕዘብ እንደራሴው ንግግር በሽታው የለም የሚለውን ጥርጣሬ አጉልቷል።

አሁንም ድረስ በሽታው እንዳለና አስጊ እንደሆነም ያልተረዱ ኬንያውያን አሉ። በሴራ ትንተና የሚያምኑ መብዛታቸው በመንግሥት እና በሕዝቡ መካከል ያለውን መተማመን ቀንሷል።

በሌላ በኩል አገሪቱ ጥላቸው ከነበሩ እገዳዎች አንዳንዶቹን እያነሳች ነው።

ለሕዝቡ ግልጽ መረጃ መስጠት ያሻል

በናይሮቢ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኦሙ አንዛላ እንደሚሉት፤ አፍሪካ ውስጥ በሽታን በተመለከተ ለሕዝብ ግልጽ መረጃ ያለመስጠት ልማድ አለ።

የአገር መሪዎች ሲታመሙ እንኳን በሚስጥር ለህክምና ወደ ውጪ አገራት ይሄዳሉ እንጂ በአደባባይ ስለህመማቸው አይናገሩም።

በጤናው ዘርፍ የሚሠሩ ሙያተኞች ለሕዝቡ በቂ መረጃ አልሰጡም ሲሉ ፕሮፌሰሩ ይወቅሳሉ። የማኅበረሰቡን ጥያቄ በማድመጥ፤ ሰው ሊረዳው በሚችለው አገላለጽ ስለበሽታው ማስረዳት እንደሚገባቸውም ይመክራሉ።

ለሕዝቡ መግለጫ ሲሰጥ የጤና ባለሙያዎች ብቻ በሚረዱት ቋንቋ መሆን የለበትም። በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ያለ ሰው በሚረዳው መንገድ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል።

መግለጫው ይህን አታድርጉ፣ ያን አድርጉ ከሚል ትዕዛዝ ባለፈ ዝርዝር መረጃ የያዘ መሆንም ይጠበቅበታል።

ሕዝቡ ጥያቄው ከተመለሰለት እንዲሁም እውነታውን ከተረዳ፤ የበርካቶችን ሕይወት መታደግ ይቻላል።

[ይህ ጽሑፍ በዋይሂጋ ሙዋራ ተዘጋጅቶ ከአፍሪካውያን ጋዜጠኞች የተላኩ ደብዳቤዎች በሚስተናገዱበት አምድ የተነበበ ነው።]

ኮሮና
Banner