ሩሲያ የኮሮናቫይረስ ክትባት መረጃዎችን ለመመንተፍ ሞክራለች መባሏን ውድቅ አደረገች

በዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያ አምባሳደር

በዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያ አምባሳደር የአገራቸው የደህንነት ተቋም የኮሮናቫይረስ ክትባት ምርምርን ለመስረቅ ሙከራ አድርጓል በሚል የቀረበውን ክስ ውድቅ አደረጉ።

አምባሳደር አንድሬ ኬሊን " በዚህ ክስ ፈፅሞውኑ አላምንም ፤ ምንም ትርጉም የሚሰጥ ነገርም የለውም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የደህንነት ተቋም የሩሲያ የመረጃ ሰርሳሪዎች የሩሲያ የደህንነት አገልግሎት ተቋም አካል በመምሰል የኮሮናቫይረስ ክትባት ለመስራት እየጣሩ ያሉ ተቋማትን ኢላማ ማድረጋቸውን ያስታወቀው ሐሙስ ዕለት ነበር።

የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የመረጃ መረብ ደኅንነት ማዕከል፤ መረጃ መንታፊዎቹ ከሞላ ጎደል "የሩሲያ የደኅንነት አገልግሎት አካል" እንደሆኑ በመምሰል እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁሞ ነበር።

"በዚህ ዓመት ኤፒቲ29 የተባለው የመረጃ መንታፊ ቡድን በካናዳ፣ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም በኮቪድ -19 ክትባት ላይ የሚሰሩ በርካታ ድርጅቶችን ኢላማ ያደረገ ሲሆን፤ ከምርምሩ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የአዕምሯዊ ንብረቶችን ለመስረቅ የታሰበ ሊሆን ይችላል" ሲል የገለፀ ሲሆን የዩናይትድ ኪንግደም የመረጃ መረብ ደህንነት ተቋም መረጃ መንታፊዎች 95 በመቶ የሩሲያ የደህንነት ተቋም አካል ይመስሉ እንደነበር ጠቅሷል።

ይህንን እንዲያረጋግጡ የተጠየቁት አምባሳደሩ በቀጥታ ምላሽ ባይሰጡም " መንታፊዎቹ መኖራቸውንም የሰማሁት ከእንግሊዝ መገናኛ ብዙኃን ነው"ብለዋል

"ይህ ግን ክትባት እየተሰራ እንደሆነ ለማወቅ ጠቃሚ ነው" ያሉት አምባሳደሩ፤ የሩሲያ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ አር-ፋርም፤ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተሰራውን የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለመስራት ከአስትራዜኔካ ጋር መተባበሩን አስታውቀዋል።

ከዚህም ባሻገር ሩሲያ በዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲካ ጣልቃ ገብታለች በሚል የቀረበውን ክስም አምባሳደር ኬሊ አጣጥለውታል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ዶሚኒክ ራብ፤ ሩሲያ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የአገሪቷ ምርጫ ጣልቃ ለመግባት ፍላጎት እንደነበራት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገኘ መረጃ እንዳሳየ ተናግረዋል።

በበይነ መረብ ላይ የተገኘው ይህ መረጃ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ሌበር ፓርቲ ሲጠቀምበት የነበረና የዩናይትድ ኪንግደምንና የአሜሪካን የንግድ ውይይቶች ዝርዝር የያዘ ነው ብለዋል።

ይህንን በሚመለከት የተጠየቁት አምባሳደሩም፤ "በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብነትን የሚያሳይ ምንም ነጥብ አላየሁም" ሲሉ መልሰዋል።

"በምንም መልኩ ጣልቃ አልገባንም፤ ጣልቃ መግባታችንን የሚያመለክትም አንድም ነጥብ አላየንም፤ ምክንያቱም እኛ ወግ አጥባቂው ሌበር ፓርቲ የአገሪቷ መሪ ቢሆንም፤ አሁን ካለው በተሻለ ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር እንሞክራለን" ብለዋል።

አምባሳደር ኬሊን አክለውም የሩሲያ ባለሥልጣናት በአገሪቷ በቅርቡ የተካሄደውን የሕገ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔ እያጠኑ መሆናቸውን በመግለፅ፤ በርካታ የመረጃ መረብ ጥቃቶች መነሻቸው ከዩናይትድ ኪንግደም ግዛት እንደሆነ ደርሰውበታል ብለዋል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ሩሲያ የተመሳሳይ ፆታን የሚከለክለውንና ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ለቀጣዮቹ 16 ዓመታት በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚያስችለው ሰፋፊ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ ድምፅ መስጠቷ ይታወሳል።

ነገር ግን ሩሲያ በመረጃ መረብ ጥቃት ላይ በመሳተፏ እንደ አገር ዩናይትድ ኪንግደምን አልከሰሰችም ነበር ብለዋል። በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ግን አልሰጡም።