በዓመት 2ሚሊዮን ብር የሚያስከፍለው ትምህርት ቤት ጥቁሮችን ይቅርታ ጠየቀ

ዲሊቤ ኦኒያማ

የፎቶው ባለመብት, DILLIBE ONYEAMA

የምስሉ መግለጫ, ዲሊቤ ኦኒያማ

የኢትን ትምህርት ቤት በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኝና በትምህርት ጥራቱ የገነነ ሥመ ጥር እንዲሁም ውድ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒትር ቦሪስ ጆንሰንን ጨምሮ ንጉሣዊያን ቤተሰቦችና ሌሎች ሥመ ጥር ፖለቲከኞች ተምረውበታል፡፡

የዚህ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ታዲያ ለመጀመርያው የትምህርት ቤቱ ጥቁር ተማሪ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ናይጄሪያዊው ደራሲ ዲሊቤ ኦኒያማ ከኢትን ኮሌጅ ለመመረቅ የመጀመርያው ጥቁር ነው፡፡ የ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ማትሪክ) የወሰደው እንደ አውሮፓዊያኑ በ1969 ዓ. ም ነበር፡፡

በኢትን ኮሌጅ ተማሪ ሳለ ይደርስበት የነበረው ዘረኝነት በተመለከተ መጽሐፍ ጽፎ አሳትሞ ነበር፡፡

ይህን በማድረጉም ትምህርት ቤቱ ‹‹እኔ ዘንድ ዝር እንዳትል›› በሚል ለረዥም ዘመን አግዶት ቆይቷል፡፡

የዚህ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሳይመን ሄንደርሰን "ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ ነገሮች ከዚያ በኋላ ተሻሽለዋል፡፡ ነገር ግን ብዙ ይቀረናል" ብለዋል፡፡

‹‹ከኛ ትምህርት ቤት የወጡ ጥቁሮች ተማሪ ሳሉ በዘረኝነት ችግር ይደርስባቸው እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ ይህን መቀበልና ማሻሻል ይኖርብናል፡፡›› ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

የዚህ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ዲሊቤ ኦኒያማንም ቢሆን ይቅርታ መጠየቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

‹‹በአካል አግኝቼው ወደ ተማረበት ትምህርት ቤት ጋብዤው ይቅርታ ማለት እፈልጋለሁ ብለዋል የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ለቢቢሲ።

ዲሊቤ ኦኒያማን የደረሰበት ምንድነው?

ዝነኛው ደራሲ ኦኒይማን ለቢቢሲ እንደተናገረው ‹‹አሁን እሱን ይቅርታ መጠየቅ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ስለ ኢተን ያለኝ አመለካከትንም አይቀይረውም፡፡›› ብለዋል፡፡

ናይጄሪያዊው ደራሲ በየቀኑ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ዘረኝነትን ያስተናግድ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡

‹‹ለምንድነው ጥቁር የሆንከው፣ ጸጉርህ ውስጥ ምን ያህል ዝንብና ቅማል ነው ያለው? እናትህ ለመሆኑ አፍንጫዋ ውስጥ አጥንት አለ?›› ይሉኝ ነበር ሲል ይደርስበት የነበረውን ዘረኝነት ጠቅሷል፡፡

ኦኒያማን በትምህርቱ ደከም ሲል ወይም በስፖርት የተሻለ ውጤት ሲያስመዘግብ መምህራኑ ‹‹ይህ በዘሩ ምክንያት የመጣ ነው›› ይሉት እንደነበር ያስታውሳል፡፡

በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ባመጣ ጊዜ ደግሞ ‹‹እንዴት ጥቁር ሆነው እንዲህ አይነት ውጤት አገኘህ፤ ኮርጀህ መሆን አለበት›› ይሉታል፡፡

ትምህርት ቤቱን ከለቀቀ በኋላ በዚያ ትምህርት ቤት የገጠመውን ሁሉ ጽፎ በማሳተሙ ነበር በ1972 ትምህርት ቤቱ ደብዳቤ የላከለት፡፡

መጽሐፍ በመጻፉም መቼም ቢሆን የተማረበትን ትምህርት ቤት ዳግም መጎብኘት እንደማይችል የሚገልጽ ደብዳቤ ነበር የተላከለት፡፡

አሁን የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ይቅርታ ያሉት የጆርጅ ፍሎይድን በነጭ ፖሊስ ግድያ ተከትሎ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ከተቀጣጠለ በኋላ ነው፡፡

በእንግሊዝ ባለፉት ሳምንታት ሁለት ግዙፍ ኩባንያዎች በተመሳሳይ ጥቁሮችን ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

ባሪያ ያመላልሱ ለነበሩ የመርከብ ድርጅቶች የመድን ዋስትና ይሰጥ የነበረው ሎይድስ ኦፍ ሎንደን ኩባንያ በባሪያ ንግድ ላይ ለነበረው ሚና ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን፣ ቢራ ጠማቂው ግሪን ኪንግ የኩባንያው መስራች ድሮ በካሪቢያን በባሪያዎች ጉልበት ላይ ላደረሰው መከራ ይቅርታ ጠይቋል፡፡.

ኢተን ትምህርት ቤት በንጉሥ ሄነሪ ስድስተኛ የተመሰረተ ሲሆን ይህም እንደ አውሮፓዊያኑ በ1440 የሆነ ነው፡፡

በኢተን የትምህርት ጥራት የላቀ ሲሆን አሁን እዚያ ለመማር በዓመት 50ሺህ ዶላር ክፍያን ይጠይቃል፡፡