የነዳጅ ዘመን አብቅቶ የባትሪ ዘመን እየመጣ ይሆን?

አዳዲስ ሃሳቦችን የሚያመነጨው ኢሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አዳዲስ ሃሳቦችን የሚያመነጨው ኢሎን መስክ

ኢሎን መስክ ቢሊየነር ነው። ሁሌም እንደተሳካለት።

በቅርቡ ወደ ህዋ ሳይንቲስቶችን ይዞ የመጠቀ የመንኮራኮር ታክሲ ሰርቶ ተሳካለት። ከዚያ በፊት እጅግ ዝነኞቹን የቴስላ መኪኖች ፈጥሮ ተሳክቶለታል። ከዚያ በፊት ፔይፓል የክፍያ ዘዴን ፈጥሮ፣ አትርፎ ሽጦታል።

የፈጠራት የህዋ ታክሲ "ሰፔስ ኤክስ" ትባላለች። ማርስ አድርሳ ትመልሳለች። ጥሩ ብር ያለው መሳፈር ይችላል። ናሳ ራሱ የራሱን መንኩራኮሮች ጡረታ አስወጥቶ ሲያበቃ ከዚህ ሰውዬ ታክሲ መኮናተር ጀምሯል።

ስፔስ ኤክስ የሰማይ ታክሲ ሲሆን ቴስላ ደግሞ እጅግ የረቀቀ የምድር ታክሲ ነው። በኤሌክትሪክ የሚሰራ፣ ራሱን በራሱ የሚሾፍር የነገ ዘመን ታክሲ።

ይሄ ሰውዬ በ2012 ተስላ መኪናንም ሆነ ሰፔስ ኤክስን የሚያስንቅ የሳይንስ ልቦለድ የሚመስል ነገር ደግሞ አመጣ።

ነገሩ የተጠነሰሰው የሰው ልጅ በትራንስፖርት ረገድ እንደ ግመል እየተንቀረፈፈ ለምን ይጓዛል ከሚል ቁጭት ነው። መኪናም፣ አውሮፕላንም ባቡርም ቀርፋፋ ናቸው ይላል ቢሊየነሩ ኢለን መስክ።

እነ መኪና፣ እነ ባቡር እንዲህ የሚያንቀረፍፋቸው ሁለት ነገር ነው። አንዱ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጣ የአየር ግፊት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰበቃ ነው።

እነዚህን መቆጣጠር ቢቻልስ ብሎ አሰበ፣ ኢሎን። ሀይፐርሉፕ (hyperloop) የሚባል ነገር ፈጠረ።

ሀይፐርሉፕ ልክ ይሄ ከአገር አገር በሚዘረጋ የጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ ውስጥ እጅግ በፈጠነ ጉልበት መጓዝ ማለት ነው፤ በደምሳሳው።

ለምሳሌ አዲስ አበባ አንድ ክፍለ ከተማ የሚሰራ ሰው ለሻይ ሰዓት መቀሌ ቆንጆ ቡና ጠጥቶ ወደ ቢሮው መመለስ ይችላል፣ በሀይፐርሉፕ። በሰዓት 700 ማይል ይምዘገዘጋል።

የቀናት ጉዞ የደቂቃዎች ጉዳይ ይሆናል።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የማይመስል ነገር ነው? ሁሉም አሁን እውን የሆነ ቴክኖሎጂ ትናንት የማይመስል ነገር ነበር፡፡ እስኪሆን ድረስ ሁሉም ፈጠራ እብደት የሚመስል ነገር አለው። ሀይፐርሉፕም እንደዚያው ነው።

ወደ ህዋ የተደረገው የስፔስኤክስ ጉዞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ወደ ህዋ የተደረገው የስፔስኤክስ ጉዞ

የፈለገ ቢሆን እንዴት በዚህ ፍጥነት መምዘግዘግ ይቻላል?

ምክንያቱም መግነጢሳዊ ኃይል የትራንስፖርት ዘዴን ስለሚያዘምነው ነው። ተንሳፋፊ የመግነጢሳዊ ኃይል (Magnetic Levitation) ቴትራሳይክሊን ክኒን የመሰለውን የባቡር መሳፈሪያ ፉርጎ ከሚጓዝበት ሀዲድ አንሳፎ አየር ላይ ያበረዋል። ስለዚህ ሰበቃ አይፈጠርም። ሰበቃ ከሌለ ደግሞ ፍጥነት አለ።

ይህ እንደ ንፋስ ውልብ ብሎ መጓዝ ቅዠት ከመሰለዎ ተሳስተዋል። በፈረንሳይም በእንግሊዝም ተግባር ላይ ሊውል በሙከራ፣ በፍተሻና በምርምር ላይ ነው።

ስለ ሀይፐርሉፕ ተምዘግዛጊ ባቡር ለጊዜው እዚህ ላይ ገታ እናድርግ።

ይሄ ቢሊየነርና የቴክኖሎጂ ፈጣሪ ኢሎን መስክ ተአምር ይሰራል፣ ዓለምንም ይገለባብጣታል የተባለው ከላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች አይደለም። ባትሪ ላይ እየፈጠረ ያለው ነገር ነው አሁን መነጋገሪያው።

የኢሎን መስክ ባትሪ፤ የዓለም ዝሆኑ ባትሪ

የኢሎን መስክ ቴክኖሎጂያዊ አብዮት ያመጣል የተባለለት ይህ የባትሪ ፈጠራ ምን ይሆን?

የሊትየም ባትሪዎች መፈጠራቸው ነው አዲሱ ነገር።

እጅግ ቀላል ክብደት የሚኖራቸው የሊትየም ባትሪዎች እውን ሲሆኑ እጅግ ጠፍጣፋና በጣም ቀጭን ስልኮች ይኖሩናል።

በስልኮቻችን ስለ ባትሪ ሳንጨነቅ ለ40ኛ ዓመት ልደታችን ቻርጅ ያደረግነውን ስልክ በ70ኛው ዓመት ልደታችን "ባትሪዬ እያለቀ ነው እስኪ ቻርጀር አቀብሉኝ ልጆች!" ልንል እንችላለን።

ለምሳሌ የኤሌክትሪክ መኪና ሊመጣ ነው ሲባል ብዙ ሰዎች 'የማይመስለውን' ሲሉ ተጠራጥረው ነበር።

አሁን የኤሌክትሪክ መኪናዎች በአውሮፓ ጎዳና በየመንገዱ በተተከሉ ስልክ እንጨቶች ባትሪ ሲጠጡ ነው የሚያድሩት። በየጎዳናው የሚታየው ይኸው ነው።

መንግሥታት ዜጎቻቸው የነዳጅ መኪናን እርግፍ አድርገው ትተው ወደ ባትሪ መኪና ጠቅልለው እንዲገቡላቸው ማበረታቻ ጭምር እየሰጡ ነው። በዚህ ረገድ ፈረንሳይ ዘምታበታለች።

አሁን የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ለመግዛት ስናስብ አንድ ነገር ያሳስበናል። ወይም ሁለት ነገር፤ ዋጋና ባትሪ ቻርጀር።

መኪናዬን እየነዳሁት ባትሪ ቢጠፋስ? ተቀያሪ ባትሪ ትይዛለህ…

ተቀያሪ ባትሪው ቢያልቅስ?

የብዙዎች ጭንቀት ይህ ነው። የባትሪን ነገር በስልካችን ስለምናውቀው ቻርጅ ማድረግ የሚባል ነገር ሐሳቡ ራሱ ሳያስፈራን አልቀረም።

ያም ሆኖ ዓለማችን ከነዳጅ ወደ ባትሪ ዘመን እየተሸጋገረች ነው። የነገሩ ጠንሳሽ ኢለን መስክም ሆነ ቴስላ የአክሲዮን ገበያው ደርቶላቸዋል።

ባለፈው ዓመት ቴስላ እጅግ ስኬታማ የሆነውን የቶዮታ መኪና አምራች በአክሲዮን ገበያ በልጦት ነበር። ምንም እንኳ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ቶዮታ ከቴስላ በ30 እጥፍ መኪና የሸጠ ቢሆንም።

አሁን ቴስላ ኩባንያ ስኬታማ የመሆን ምስጢሩ ይሄ ኢለን መስክ የሚባል ቢሊየነርና የቴክኖሎጂ ፈጣሪ እርሱ የነካው ነገር ሁሉ ስኬታማ እንደሚሆን እየታወቀ በመምጣቱ ሊሆን ይችላል።

እሱ ደግሞ መጪው ዘመን የባትሪ ዘመን ነው ብሎ አውጇል። እሱ ካለ ነገሩ ትክክል ሳይሆን አይቀርም።

የኤሌክትሪክ መኪኖች ቻርጅ ሲደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኤሌክትሪክ መኪኖች ቻርጅ ሲደረጉ

የዓለም ዝሆን ባትሪ ምንድነው?

ባትሪን ስናስብ ስልካችን ወይም መኪናዎቻችን ናቸው ቀድመው የሚመጡብን።

ባትሪዎችን የከሰል ኃይልን እያጠፉት እንደሆነ እምብዛምም አላስተዋልን ይሆናል።

ምናልባት ወደፊት ከሰልም ሆነ ትልልቅ የወንዝ ግድቦችን ማቆም ፋሽኑ ያለፈበት ነገር ሊሆን ይችለል።

በመጪው ዘመን እጅግ ግዙፍ ባትሪዎች አንድ ከተማን በኤሌክትሪክ ሊያንቦገቡጓት ይችላሉ።

ምናልባት ወደ አዲስ የኃይል መመንደግ ዘመን እየገባን ይሆናል ይላሉ ፕሮፌሰር ፖል ሺሪንግ። ፕ/ር ፖል በለንደን ዩነቪርስቲ ኮሌጅ የባትሪ ቴክኖሎጂ ተመራማሪ ናቸው።

ፕሮፌሰር ፖል የኤሌክትሪክ መኪናዎች በመጪዎቹ 10 ዓመታት የአውሮፓን የባትሪ ፍላጎት በመቶ እጥፍ ያሳድጉታል ብለው ይጠብቃሉ።

ይህ የባትሪ ፍላጎት የሚቆየው ታዲያ ባትሪዎች ዋጋቸው ሲረክስ፣ ዕድሜያቸው ሲረዝም እና የኃይል ፍላጎትን በአስተማማኝ ሲመልሱ ነው።

ይህን ሁሉ ማሟላት ለአንድ ቴክኖሎጂ አይከብድም? ዋጋ ረክሶ፣ ፍጥነትና ጉልበት ጨምሮ፣ ዕድሜ ረዝሞ፣ ፍላጎት አሟልቶም እንዴት ይሆናል?

"ሐሳብ አይግባዎ" ይላል ኢሎን መስክ። በእርግጠኝነት የባትሪ ዘመን እየመጣ ነው።

የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ቻርጅ እየተደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ቻርጅ እየተደረጉ

የማይሞት ባትሪ ሊመረት ይችላል?

ባለፈው ሳምንት አንድ የቻይና ኩባንያ ጉድ ያስባለ ምርት ይዞ ወጥቷል።

አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደርጎ አንድ ሚሊዮን ማይል መጓዝ የሚያስችል ባትሪን አምርቷል።

በምህጻር ስሙ ካትል (CATL) የሚባለው ይህ የቻይና ኩባንያ ቴስላን ጨምሮ ለብዙ ኢንዱስትሪዎችና አምራቾች ባትሪ አቅራቢ ነው።

አንድ መኪና 2 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር እንዲነዳ የሚያስችል ባትሪን ነው አመረትኩ የሚለው። ይህም ማለት አንድ መኪና ለ16 ዓመት ቻርጅ ሳይደረግ ሊነዳ ይችላል እንደማለት ነው።

አሁን ባለው እውነታ ብዙዎቹ የመኪና ባትሪዎች ዋስትና የሚሰጡት ከ60 ሺህ እስከ 160 ሺህ ማይል አገልግሎት እንደሚሰጡ ቃል በመግባት ነው። ይህም ከ3 እስከ 8 ዓመት የመኪና ኤሌክትሪክ ባትሪ ዋስትና ማለት ነው።

ይህ አዲስ ዝሆኔ ባትሪ ግን ነገሩን ሁሉ ወደ ሌላ ምዕራፍ አሳድጎታል።

ባትሪውን ያመረተው ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ የዚህ ባትሪ ዋጋ ከሌሎች ከማናቸውም ባትሪዎች በ10 እጥፍ ሊበልጥ ይችላል ሲሉ ውድ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል። ውድስ ቢሆን ማን ይፈራል? ዋናው አስተማማኝ አገልግሎቱ ነው።

እርግጥ ነው ለኤሌክትሪክ መኪና አምራቾች አስር ጊዜ መቀያየር የማያስፈልገው፣ 10 ጊዜ ቻርጅ መደረግ የማያስፈልገው፣ የሕይወት ዘመኑ እንደ ማቱሳላ የሆነ ባትሪ ሲመረትላቸው ገበያቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉ አይቀርም።

ሆኖም ይህ መልካም ዜና ለኤሌክትሪክ መኪና ብቻ ነው የሚጠቅመው ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል።

ይህ ዜና ባትሪን ለሚፈልጉ ምርቶች ሁሉ የምሥራች ነው። ለምሳሌ ለንፋስ ኃይል ተርባይን፣ ወይም ለፀሐይ ኃይል ማጠራቀምያ ፓናሎች እጅግ አስደናቂ ዜና ነው።

አንድ ባትሪ የዕድሜ ዘመኑ በዚህን ያህል ረዘመ ማለት ንፋስ ባይኖርም ተርባይኑ ኃይሉን በባትሪ ያጠራቅማል። የፀሐይ ኃይል ያጠራቀመው ፓኔል ፀሐይ ባትወጣም ጉልበቱን በባትሪው ያጠራቅማል። ባትሪው ደግሞ ሙሉኝ ሳይል አገልግሎት ይሰጣል ማለት ነው።

ግዙፎቹን ነገሮች ትተን ስለ ስልካችንና ባትሪዎቹ ብናወራ ራሱ ከዚህ ወዲያ ስልካችን ቻርጅ መደረግ ላያሻው ይችል ይሆናል።

አንድ የማይንቀሳቀስ ግዙፍ ባትሪ ቤታችን በማስቀመጥ ከፀሐይም ይሁን ከኤሌክትሪክ ኃይልን እንዲሰበስብ ካደረግነው በኋላ ከዚያ ወዲያ ስለ መብራት መጥፋት ጭራሽ ላናስብ እንችላለን ማለት ነው።

ቻይና ውስጥ ያለው አዲሱ የቴስላ ፋብሪካ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቻይና ውስጥ ያለው አዲሱ የቴስላ ፋብሪካ

ርካሹ አማራጭ?

በቀጣይ ዘመን የሚመረቱ ባትሪዎች ርካሽ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም።

ለምሳሌ ለኤሌክትሪክ መኪና የሚሆን የባትሪ ዋጋ ውድድር በመኖሩ አሁን ከ100 ዶላር በታች ገብቷል።

ርካሽ ባትሪዎች ደግሞ ብዙ ነገሮችን ያቀላሉ። ደንበኞች ዝሆኔ ባትሪዎችን መኪናዎቻቸው ላይ ለመግጠም አያቅማሙም።

ሁለት ጥቅምን ያስገኛሉና።

አንዱ ጥቅም ዝሆኔ ባትሪዎች አንድ ጊዜ ቻርጅ ከተደረጉ ረዥም ርቀት ስለሚወስዱን ነው። ለምሳሌ ከዚህ በኋላ አንድ የአሌክትሪክ መኪና አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደርጎ በትንሹ 800 ኪሎ ሜትር ሊነዳ ይችላል።

ሁለተኛው ደግሞ ዝሆኔ ባትሪዎች ጥቂት ደቂቃ ቻርጅ ቢደረጉ በርካታ ጉልበት መያዝ ስለሚችሉ ነው። ለምሳሌ 10 ደቂቃ ቻርጅ የተደረገ የኤሌክትሪክ መኪና 300 ማይል ሊጓዝ ይችላል።

ይሄ ማለት ማደያ ገብተው ነዳጅ ቀድተው የሚወጡበት ሰዓት እንደማለት ነው።

በቅርብ ቀን የቴስላ መኪናዎች ፈጣሪ ኢለን መስክ ኤስ እና ኤክስ ለሚባሉት ወደ እኛ አገር ገና ላልገቡት መኪናዎች ይህን አዲስ ባትሪ ገጥሞ አዲስ የብስራት ዜና ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል።

የባትሪ ቴክኖሎጂው በአየር ንብረት ለውጥ ላይም አውንታዊ ሚና ይኖረዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የባትሪ ቴክኖሎጂው በአየር ንብረት ለውጥ ላይም አውንታዊ ሚና ይኖረዋል

እነዚህ ባትሪዎች የት ይመረታሉ ?

እነዚህ እጅግ አጓጊ፣ ዋጋና ጉልበት ቆጣቢ ባትሪዎች በየት ሊመረቱ ይሆን?

የዚህ የቴክኖሎጂ ጥንቅር ዘጋቢ በለንደን እንደሚሆን ይገምታል።

ሰሞኑን ኢሎን መስክ በእንግሊዝ ሉተን አየር መንገድ የግል ጄቱ አርፋ ነበር።

ምናልባት የመስክ ትልቁ የዝሆኔ ባትሪ ፋብሪካ በዚህች ትንሽዬ ከተማ ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ተጠርጥሯል።

ሌላኛው እነዚህን ባትሪዎች አምራች ፋብሪካ በሂውስተን ቴክሳስ ሊሆን ይችላል የሚከፈተው።

እነዚህ ጊጋ ፋብሪካዎች የሚል ስም የተሰጣቸው ያለምክንያት አይደለም። በቢሊዮን ዋት ጉልበት መቋጠር የሚችሉ ባትሪዎችን ስለሚያመርቱ ነው።

ጥሬ እቃዎች ከቻይናው ካትል ኩባንያ እንደሚመጡ ይጠበቃል። ከኮባልት ነጻ የሆኑ ባትሪዎችን ለማምረት ዘዴው ተገኝቷል። ኮባልት አንደኛ ውድ ማዕድን ነው። ሁለተኛ በዋናነት የሚመረተው ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ነው። የሚመረተው ደግሞ የልጆችን ጉልበት በመበዝበዝ ጭምር ነው።

በዚህ የባትሪ ምርት ዋናው ማዕድን ሊትየም ነው የሚሆነው። ያንን ደግሞ ከደቡብ አሜሪካ በርካሽ ለማውጣት መንገዱ ተይዟል።

አዲሱ ባትሪ ሕይወታችንን በምን መንገድ ይቀይራል?

ይህንን ጽሑፍ ስጀምር ከኢሎን መስክ ፈጠራዎች ሁሉ ይህ የባትሪ ፈጠራ ዓለምን ይቀይራል ብያችሁ ነበር።

ይህ እምነቴ አሁንም አልተቀየረም። የማቱሳላን እድሜ የሚይዙ ባትሪዎች ሲፈጠሩ ኃይል የምናገኝበት መንገድ ሙሉ በሙሉ ይቀየራል።

ከዚያ በኋላ ማንም ሰው ከቤንዚንና ከናፍጣ መኪና ጋር አይንደፋደፍም።

ይህን የምናደርገው ባትሪ በሚፈጥረው ምቾት ነው። የኤሌክትሪክ መኪናዎች ጉልበት ለመቋጠር ምቹ ከሆኑ፣ በዋጋ ርካሽ ከሆኑ ማን ወደ ናፍጣ ይሄዳል?

ሌላም ትልቅ ምክንያት አለን፤ ወደ ኤሌክትሪክ መኪና ፊታችንን ለማዞር… የአየር ንብረት ለውጥ።

የካርበን ልቀትን በአያሌው ለመቀነስ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ተመራጭ መሆናቸው እሙን ነው። በአጭር ሰዓት የሚሞሉ ባትሪዎች መፈጠራቸው ደግሞ የኃይል ቁጠባን በእጥፍ ይጨምራል።

ለዚህም ነው ነገ የባትሪ ዘመን ነው የምንለው።