ኮሮናቫይረስ፡ በወረርሽኙ ወቅት ጀርመኖችን በሙያዋ የምታግዘው ኢትዮጵያዊት

ምፅላል ክፈለየሱስ ማቺ

የፎቶው ባለመብት, Mitslal Kifleyesus-Matschie

በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሰው የሚያውቀኝ በዶክተር ምፅላል ነው። ባለቤቴ ጀርመን ስለነበርና በባሕላቸው ስም መቀላቀል የተለመደ ስለሆነ ያባቴንም እንዳላጣ በማሰብ ምፅላል ክፈለየሱስ ማቺ ሆንኩኝ። ልጅ እያለሁ ጦርነት ማስቆም እመኝ ነበር። በ21 ዓመቴ በተባበሩት መንግሥታት የጦር መሳሪያ ቁጥጥርና ቅነሳ ላይ ላይ መሥራት ጀመርኩ።

በተባበሩት መንግሥታት ስትራቴጂስት ሆኜ በምሠራበት ወቅት የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጉባዔ በተባበሩት መንግሥታት ዋና አጀንዳዎች መካከል እንዲሆን ከሠሩት ሰዎች መካከል ነበርኩኝ። ያስፈልጉ ከነበሩት የ76 አገራት ፊርማዎች 23 አገራት እንዲፈርሙ ያደረኩት እኔ ነበርኩኝ። የኛም ቡድን ይህን ራቲፋይ በማስደረጉ የኖቤል የሰላም ተሻላሚ ሆነን ነበር። በዚያን ጊዜ ብቸኛዋ ሴት ኢትዮጵያዊት ነበርኩኝ።

አሁንም ቢሆን የምታገለው ኬሚካልና ባዮሎጂካል የሆኑ መሣሪያዎች እንዲጠፉ አልያም እንዳይስፋፉ በማድረግ ነው። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ኢላማዬን ትንሽ ዞር አድርጌ ትኩረቴን በእርሻ ሰብል ላይ አድርጌያለሁ። በአገር ቤት ሳይንስን ተጠቅሞ ከአርሶ አደሮች ጋር በመሥራት ኢትዮጵያ የሚበቅሉ ሰብሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመንና በጃፓን ተቀባይነት እንዲኖራቸው አድርጊያለሁ።

አሁን ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝ ከተነሳ ጀምሮ 'ሳይንስና ቴክኖሎጂ በኮሮናቫይረስ' እና 'ኢነር ጀርኒ' የተሰኙ ሁለት የተለያዩ የዩትዩብ የነፃ የመረጃ አገልግሎቶችን መስጠት ጀምሬያለሁ። ወደዚህ ግን የገባሁት ከመሬት ተነስቼ አልነበረም።

እዚህ፣ ጀርመን የነበሩ ዶክተሮች እና ነርሶች፣ ጣሊያን የተፈጠረውን ዓለም ካየ በኋላ፣ በጣም ከባድ የአዕምሮ ረብሻ ገጥሟቸው ነበር። ከዚህ ቀደም ደግሞ እኔ በተለያዩ መድረኮች ላይ በሳይንስ የተደገፉ የውስጣዊ ሰላም ንግግሮችን አድርጌ ስለነበር እርዳታ እንዳቀርብ ጥያቄ ቀረበልኝ። ለቀረበልኝ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ብዬ ለሁሉም ይጠቅማል ብዬ በማሰብ የዩትዩብ ቻናል ከፍቼ ንግግሩን በበይነ መረብ ማስተላለፍ ጀመርኩኝ።

የመጀመሪያው ንግግሬንም በፍርሃት ዙሪያ 'ፍርሃትን ማሸነፍ' በሚል ርዕስ አቀረብኩኝ። ሳይንስና መንፈሳዊነት አንድ ላይ የሚሄዱ የአንድ አካል ሁለት ጎኖች ናቸው ብዬ አምናለሁ። እንዲያውም ብዙ መንፈሳዊ ተብለው የሚታሰቡ ሃሳቦች በሳይንስ ማስረዳት ይቻላል ባይ ነኝ። አይንስታይንም ለልጁ በፃፈላት ደብዳቤ እንደሚለው ፍርሃትን ማሸነፍ የሚቻለው በፍቅር ነው፤ ስለዚህ ከፍርሃት ለመላቀቅ የፍቅርን ጉዞ በዩትዩብ አስጀመርኩኝ። ይህን ጉዞ ስጀምርም ብዙ ስዎች የምሥጋና መልዕክት አድርሰውኛል።

ምፅላል ክፈለየሱስ ማቺ ከልጆች ጋር ተቃቅፋ

የፎቶው ባለመብት, Mitslal Kifleyesus-Matschie

ስለ ፍቅር እና ስለዚህ ውስጣዊ ጉዞ በማወራበት ጊዜ ብዙ ሰዎች፣ በተለይ ደግሞ አገር ቤት ያሉ ሰዎች፣ ስለ ሃይማኖታዊ ጉዞ የማወሳ ይመስላቸዋል። ምንም ቢመሳሰል ግን እኔ ስለ ሳይንስ ነው የማወራው። ማለትም ስለ ኤፒጄኔቲክስ፣ ኒዩሮሲኖፕሲስና ኒዩሮሚረሪንግ ነው የማወራው።

አያቶቻችን ድሮ አንዳንድ ሰው ሲታመም 'ይህ ነገር ከዘር የመጣ ነው' ይሉ ነበር። ይህ ደግሞ ኤፒጄኔቲክስ ይባላል። በዘረመል (ዲኤንኤ) የመጡ በሽታዎች ቢሆኑም እንኳን አሁን በሳይንስ እገዛ ማሸነፍ፣ መዳን፣ መለወጥ ይቻላል ነው እያልን ያለነው። የዩትዩብ ቻናሉም ዋናው ዓላማ በሃይማኖታዊ ሳይሆን በመንፈሳዊው እና በሳይንስ መካከል ያለውን የመረዳት ክፍተት ለመዝጋት ነው።

ደም ብዛት ወይንም የስኳር በሽታ አብዛኛውን ጊዜ በዘር የሚመጡ መሆናቸውን ሰዎች ይረዳሉ። የአዕምሮ ችግሮችም ልክ እንደዚያው በዘር ሊመጡ እንድሚችሉ ለማስረዳት እጥራለሁ። አንዳንዴ በዘር የሚመጡት የአዕምሮ ችግሮችም ሆኑ አካል ላይ የሚፈጠሩ በሽታዎች ከመወለዳችን ሊታዩ ይችላሉ። አንዳንዴ ደግሞ ቢኖሩም እንኳን ሁኔታዎች ካልተመቻቹላቸው ላይታዩ ይችላሉ። እናም ብዙ ጊዜ በውጥረት በጭንቀት መካከል ወይንም በአካባቢው ያሉ ሁኔታዎች ሊቀሰቅሷቸው ይችላሉ።

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ላይ ለሚገኝ ሰው ደግሞ መፍትሔውን ለማግኘት እርዳታ ማቅረብ ያስፈልጋል። የሚቀርበውን መፍትሔ የሚቀበል ሰው ደግሞ ከችግሩ የመላቀቅ አጋጣሚው ሰፊ ይሆናል። እርዳታ መጠየቅ ያለበት ደግሞ ከአቅም በላይ ሲሆን ሳይሆን ከመጀመሪያው ነው። በባህላችን በተለይ የአዕምሮ ችግሮችን ለመቀበል ስለሚያቅተን የመሸፋፈን ልማድ አለ። ይህ ብዙ ጠቃሚ አይደለም።

አብዛኛውን ጊዜ የሚታዩ ችግሮች ከሌሉ በስተቀር ራስን የመቀየር ሃሳብ 'ትራንስፎርሜሽን' አይመጣልንም። ፆም፣ ፀሎትና ፀበልም ሆነ መንፈሳዊ ጉዞዎች የሚደረጉት ጭንቀት ሲኖር ወይንም መፍትሔ ፍለጋ ነው። እነዚህ መጥፎ ናቸው ሳይሆን እያልኩኝ ያለሁት፣ ልክ በችግር ጊዜ መንፈሳዊነትን እንደምንፈልገው ሁሉ በሌላም ጊዜ ልናዘወትረው ይገባል ነው የምለው። ይህም ሳይንሳዊ ነው።

ምፅላል ክፈለየሱስ ማቺ

የፎቶው ባለመብት, Mitslal Kifleyesus-Matschie

በተለይ አሁን ደግሞ ዓለም ያለችበት ሁኔታ ሁላችንንም የሚያሳስብ በመሆኑ ውስጣዊ ጉዞ ከምንጊዜም በላይ ጠቃሚ ነው። በአገራችን ለምሳሌ የተለያዩ መንፈሳዊና ባህላዊ የሆኑ የመንፈስ እርጋታ የሚሰጡ መፍትሔዎች አሉ። እነዚህን ባህላዊ የሆኑ መንፈሳዊ እርካታና እርጋታ የሚሰጡ መፍትሔዎች በሳይንሱ ዓለም 'ትራንስፎርሜሽን' የምለው ውስጣዊ የጉዞ ዓይነት ነው።

ሳይንስ 'ትራንስፎርሜሽን' የሚለው ራስን ከማዳመጥ የሚመጣ መፍትሔ ሲሆን በቀላሉ ለማስረዳት ያህል ከሕፃንነታችን አንስቶ ነፍስ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ የተማርናቸው ብዙ ነገሮችን መቀየር ማለት ነው። እነዚህም ትምህርቶች ማንነታችን ያዋቀሩ ዋና ባህሪያችን ምሰሶዎች ሆነዋል። የምንፈራቸው፣ የምንወዳቸው ብሎም የምናስባቸውና የምንመኛቸው ነገሮች ሁሉ ሳይቀር በዘረ መልና በአካባቢያችን ማንነታችንን ያቋቋሙ ናቸው። የሚገኙትም በኒዩሮኖቻችን ነው። እነዚህን ነው ማንም ሰው መቀየር ይችላል እያልኩ ያለኹት። ለመቀየር ደግሞ ሥራ ይጠይቃል። የትራንስፎርሜሽን ሥራ ማለት ነው።

ይህንን በኒዩሮኖቻችን የተፃፈ መረጃ በውስጣዊ ጉዞ መቀየር አቅም የሌላቸው ደግሞ በመድሃኒት እርዳታ ሊቀይሩት ይችላሉ። እሱ ግን ሌላ ጉዳይ ነውና እኔም የማተኩረው በፈቃደኝነት ራሳቸውን ከተለያዩ በዘር የመጡም ሆኑ ከአካባቢ የተወረሱ ልማዶችን ለማላቀቅ እርዳታ እየሰጠኹ እገኛለሁ። በጀርመን የጦርነቱ ትውስታ በብዙዎች ዘር መረጃ ውስጥ ስላለ ይህ የኮሮና ወረርሽኝ ብዙ ጭንቀቶችን ቀስቅሷል። ሁኔታው እስኪረጋጋ ደግሞ ውስጣዊ እርጋታ እንዲያገኙ ስረዳቸው ቆይቻለሁ።

ኮሮና ከመምጣቱ በፊት ብዙ ጀርመኖችን እንደዚሁ እረዳ ነበር ። እንደውም በሳይንሱ አንዳንዴ ከተለመደ አካባቢ መውጣትና መንፈሳዊ የሆኑ ነገሮችን ማድረግ ከራስ ጋር ለመነጋገር ጥቅም ስላለው ኢትዮጵያ ድረስ ይዥያቸው የሄድኩት ብዙ ጀርመኖች አሉ። አሁን መጓዝ ባይቻልም የተለያዩ መፍትሔዎችን በመጠቀም አግዛቸዋለሁ።

ለምሳሌ በኮሮና ንብረት ያጡ፣ ዕዳ ያለባቸው፣ ከሥራ የተባረሩ ብዙ ሰዎች አሉ። እነርሱም ጉድጓድ ውስጥ ያሉ ያህል ስሜት ሊሰማቸው እንደሚችል ይገባኛል። ብመክራቸው በአሁን ሰዓት ከጉድጓዱ ለመውጣት መጣር እንደሌለባቸው ነው። ምክንያቱም ባለው እውነታ ምክንያት ያንን ማድረግ በጣም ከባድ ይሆንባቸዋል። ከዚህ ይልቅ የነበሩበትን እንዲያስቡ፣ ተመልሰው ወደነበሩበት መመለስ እንደማያቅታቸው እንዲያስቡ፣በተጨማሪም ሕልሞቻቸውን፣ መሆን የሚፈልጉትንና ማድረግ የሚመኟቸው ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ አበረታታቸዋለሁ።

ኮሮና
Banner