የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የመስፋፋት ስጋት ያጠላበት የኢትዮ-ሱዳን ድንበር

በምዕራብ ጎንደር ዞን የሙቀት ልኬት ሲካሄድ

የፎቶው ባለመብት, West Gondar communication office

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሦስት ወረዳዎች 17 ቀበሌዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር ከሱዳን ጋር የሚዋሰኑ ሲሆን በየዕለቱም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድንበሩን በማቋረጥ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ። በዚህ ምክንያትም አካባቢው ከኮሮና መስፋፋት ጋር በተያያዘ የስጋት ቀጠና ሆኗል።

እንደአማራ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሆነ ማክሰኞ (ግንቦት 25/2012) በክልሉ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የተገለጹት ሰባት ሰዎች በሙሉ ከዚሁ ከምዕራብ ጎንደር ዞን ነው። ኢንስቲትዩቱ እንዳለው ከሆነ ግለሰቦቹ ከ25 እስከ 53 ዓመት የሆናቸው ወንዶች ናቸው።

በአማራ ክልል እስከ ማክሰኞ ድረስ ቫይረሱ ከተገኘባቸው 83 ሰዎች መካከል 62ቱ በዚሁ ዞን የሚገኙ ናቸው። ወደ አካባቢው ከሚገባው ሰው አንጻር የተለያዩ ችግሮች እየተከሰቱ ነው።

በአካባቢው በለይቶ ማቆያ ማዕከል እጥረት እየተሰቃየን ነው ያሉት የመተማ ወረዳ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በቃሉ እውነቱ ናቸው።

እንደ አቶ በቃሉ ከሆነ ኮኪት ለይቶ ማቆያ ማዕከል ላይ ስፍራ በመጥፋቱ ብዙ ሰው ማስገባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህንንም ሲያብራሩ "የኮኪት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጀመሪያ ጥናት ተደርጎበት ስንሠራ ለ80 ሰዎች ብቻ ነው የሚሆነው ብንልም ስላልቻልን 400 ሰዎችን አስገባን። መጀመሪያ ቀን 2 ሰዎች ፖዘቲቭ ሆኑ [ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል]፤ በሚቀጥለው ጊዜ 8 ሰዎች [ቫይረሱ] ተገኝቶባቸዋል። ይህ ደግሞ መጨመሩ አይቀርም" ብለዋል።

በአካባቢው ከሱዳን ከ200 እስከ 300 የሚሆኑ ሰዎች በየዕለቱ ይገባሉ። "በመተማ ዮሃንስ ብቻ ኳራንቲን ከተጀመረ በኋላ ከ1300 የሚበልጡ ሰዎች ሙቀት ለክተን መርምረን ወደ መኖሪያቸው ልከናል" ሲሉ ገልጸዋል።

ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ በሚረዝመው የኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ህጋዊ እና ህገ ወጥ በሆነ መንገድ የሚገባባቸው ብዙ በሮች መኖራቸው ሌላው አሳሳቢ ነገር ነው።

"በደሎሎ፣ በቲያ፣ በቱመት እና በሌሎችም በሮች አንዴ ዘግተን ብንሰራ ጥሩ ነበር" ይላሉ አቶ በቃሉ። እንደ የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊው ከሆነ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ ብዙ መግቢያ ቦታዎች አሉ። መጀመሪያ በሽታውን ለመከላከል ከቋራ እስከ ምዕራብ አርማጭሆ ድረስ መስመሩ መዘጋት አለበት የሚሉት ኃላፊው፣ ከዚያም በዚህ ይውጡ በዚህ ይግቡ በማለት መለየት እና ከሱዳን የሚመጡትን ሰዎች ይዞ ማከም ይቻል ነበር ሲሉ ለበቢሲ ተናግረዋል።

" ከዚያ ኳራንታይን በማመቻቸት ሰዎችን 14 ቀን አቆይቶ ናሙና በመውሰድ ቫይረሱ ያለባቸውን ማከም ሌሎችን ደግሞ ወደ ቀዬአቸው መላክ ነው ያለበት። በክፍል እና በቦታ ጥበት ምክንያት ግን አልሆነም " ሲሉም ያስረዳሉ።

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት የምዕራብ ጎንደር ዞን የማህበራዊ ልማት ኃላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ " ያለው የኮሮና ስርጭት አስደንጋጭ ነው። የዞኑ አቅም ትንሽ፣ ቀዳዳው ብዙ ነው። ሰፊ ድንበር ስለሚጋራ እና ብዙ በሮች ስላሉት የስርጭቱ ሁኔታ አስደንጋጭና አሳሳቢ ችግር ላይ ነን ማለት ይቻላል።"

"ዞኑ ካለው ስፋት አኳያ በተለይ ተደጋግፍን ሰዎቹ ሲገቡ መያዝ ካልቻልን ከዞኑ አቅም በላይ ነው" ይላሉ።

እንደ ኃላፊዋ ከሆነ ከ700 በላይ ናሙናዎች ከዞኑ ለምርመራ ተልኳል። እስካሁን 62 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ለማረጋገጥም ተችሏል። "61 በለይቶ ማቆያ ያሉ ናቸው። አንድ ሰው ግን ኮኪት ከተማ ላይ የግል ፋርማሲ ያለው ሰው በሥራ ላይ እያለ ምልክት አሳየ። ወደ ለይቶ ማቆያ አስገባነው። ሲመረመር ፖዘቲቭ ሆነ" ብለዋል ሲስተር ክሽን።

ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ የማስገባት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። አንዳንዶቹ ደግሞ በፈቃድ ወደ ለይቶ ማቆያ ገብተዋል ብለውናል።

ኮሮና
Banner

ሲስተር ክሽን አክለውም ከግለሰቡ ጋር ንክኪ ካላቸው ሰዎች መካከል ከሱዳን ከመጣ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው መኖራቸውን ይናገራሉ። "በሆነ አጋጣሚ [ከሱዳን] ሾልኮ ገብቷል ማለት ነው። እንዲህ አይነት ችግር ነው ያለው። አሁን ባለው ሁኔታ ዞኑ ተጋላጭነት ትንሽ ሰፋ ያለ ነው።"

ወደ አካባቢው የሚገቡ ሰዎች የዞኑ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ከመላው አገሪቱ የሚመጡ ናቸው ያሉት ኃላፊዋ እነዚህ ሰዎችን ለማቆየት የሚያገለግሉት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ለይቶ ማቆያዎቹ ምቹ አለመሆናቸውን የሚናገሩት ሲስተር ክሽን ከማዕከሎቹ የሚጠፉ ሰዎችም እንደነበሩ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

"[ከለይቶ ማቆያ] የጠፉ ሰዎች ነበሩ። ሥራውን ከጀመርነው ቆይተናል። 575 ለይቶ ማቆያ አቆይተን ተመርምረው ወጥተዋል። ከለይቶ ማቆያው መጀመሪያ ላይ የሾለኩ አሉ። አንዳንዶቹ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር እና ደቡባዊ ጎንደር እኛ ጥቆማ ሰጥተን ተይዘዋል። አንዳንዶች ከእኛ አካባቢ የያዝናቸው አሉ። አንዳንዶች የጠፉንም አሉ። ከዚያ በኋላ ግን ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን ከሚሊሻ በተጨማሪ በልዩ ሃይል ጥበቃ እየተደረገ ነው" ሲሉ አሁን ስላለው ሁኔታ አስረድተውናል።

በሱዳን አዋሳኝ ቦታዎች ላይ 19 ዋና ዋና በሮች እንዳሉ ለቢቢሲ የገለጹት የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ፣ በዞኑ 7 የሚደርሱ የለይቶ ማቆያ ማዕከሎች መኖራቸውን ይናገራሉ።

ኃላፊው አክለውም በእነዚህ በሮች የሚገቡት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው ብለዋል። ለዚህም ተጨማሪ ማዕከሎች እንደሚያስፈልጉ አስምረውበታል።

"በረሃ ውስጥ ማሽላ ቆረጣ እና ጥጥ ለቀማ ላይ የቆየ ኃይል ነው። ስለዚህ ወደ ዞኑ በየትኛውም አቅጣጫ የመግባት ዕድል አለው። በዚህ ረገድ 19 ዋና ዋና የሚባሉ በሮችን ለይተን እነሱ ላይ ርብርብ ለማድረግ እየሞከርን ነው" ይላሉ።

ከሱዳን የሚዋሰኑ 17 ቀበሌዎችን ተለይተው ስልጠና ተሰጥቷል። ክትትል በማድረግ እየተሠራ ቢሆንም የሚገባው ሰው ቁጥሩ ሰፊ ነው። በመተማ ዮሃንስ በኩል ብቻ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሰው የሙቀት ልኬት ተደርጓል ያሉት አቶ አደባባይ ከዚያ ውስጥ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገባ የተደረገው 1400 እንደሚደርስ ያስረዳሉ።

"መጀመሪያ የሙቀት ልኬት በማድረግ ብቻ ነበር የምናሳልፈው፤ በኋላ ላይ ግን ነገሩ ሲጠብቅ እና ሱዳን አካባቢ ኮሮና ሲከሰት እኛም ጠበቅ ብለናል። አሁን 14 ቀን አቆይተን ምርመራ በማድረግ ነጋቲቭ የሚሆኑት ብቻ ናቸው እየሄዱ ያሉት። አሁን 700 በላይ ሰዎች በተለያዩ ስፍራዎች ኳራንቲን ላይ ይገኛሉ" ብለዋል።

በአካባቢው ሦስት መሠረታዊ ችግሮች መኖራቸውን አቶ አደባባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከሚገባው የሰው ቁጥር አንጻር ያሉት የለይቶ ማቆያ ማዕከሎች አነስተኛ ናቸው። በተጨማሪም " ያሉትም ጥቂት ናቸው። እነዚህም ከመመዘኛው በታች ናቸው። ትምህርት ቤቶችን ነው እየተጠቀምን ያለነው" ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።

"ሁለተኛ አካባቢው ላይ በለይቶ ማቆያ ማዕከሎቹ ልክ የማግለያ ማዕከሎች (Isolation center) ያስፈልጋል። በለይቶ ማቆያ የተለየ ምልክት የሚያሳዩትን ብቻቸውን ለይቶ ማቆየት ያስፈልጋል። ገንደውሃ ከተማ ላይ ካለው አንድ ገስት ሃውስ ውጭ ለዚህ የሚረዳ የማግለያ ማዕከል የለንም። ። ሌላው አሁን ላይ የማግለያ ማዕከልነት እያገለገለ ያለው መተማ ሆስፒታል ነው።"

በሦስተኛነት ያነሱት የኮቪድ ላብራቶሪ እና ህክምና መስጫ ጉዳይ ነው። "ምርመራው እና ህክምና መስጫውም ጎንደር እና ባህርዳር ላይ ነው" ብለውናል።

ዞኑ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለምርመራ የሚያገለግለውን ማሽን ማግኘት የቻለ ሲሆን አስፈላጊ ግብዓቶች ተሟልተው በቅርቡ ሥራ እንደሚጀመር ዋና አስተዳዳሪው ያስረዳሉ።

"ክልሉ በተለይ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር የተመራ የክልል ቡድን መጥቶ አካባቢውን በአካል ካየ በኋላ በበጀትም በቁሳቁስም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናቅሮ እየቀጠለ ነው። በፌደራል መንግስት በኩል አሁንም የተጠናከረ ድጋፍ ያስፈልጋል። በዞን በክልል ወይም በወረዳ ብቻ የሚፈታ አይደለም። የአቅማችንን እየሠራን ነው። የፌደራል መንግስት ማድረግ ያለበትን ማድረግ አለበት" ብለዋል።

ሲስተር ክሽንም ምርመራ ለመጀመር ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ላደረገላቸው ምስጋና አቅርበው ህክምና መስጫውም በአካባቢው የህክምና ማዕከላት አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተሟልተው እንዲጀመሩ ጠይቀዋል። ከለይቶ ማቆያ ማዕከል አንጻር ብዙ ሰዎችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማስተናገድ የሚያስችሉ ተገጣጣሚ ማቆያዎችን ወይንም ድንኳኖችንም ቢሆን የፌደራል መንግሥት እገዛ ቢያደርግልን ብለዋል። ካልሆነ ግን አሁን ባሉት ማዕከላት ብዙ ሰዎች በአንድ ሰፊ ክፍል ስለሚቆዩ "እኛ ካስገባናቸው በኋላም ሊተላለፍባቸው ይችላል " ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸውልናል።