ሐኪሞችን ግራ ያጋባው የኮሮናቫይረስ ወረርሽንና የሚያስከትለው ጉዳት

ሆስፒታል ውስጥ (ስዕል)

በመላው ዓለም የሚገኙ የጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ብታቀርቡላቸው ሁሉም የሚሰጧችሁ መልስ አንድ ነው፤ ‘’እንደዚህ አይነት ነገር ከዚህ በፊት አይተን አናውቅም‘’ የሚል።

ምንም እንኳን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ከወደ ቻይና የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ በሽታ እየመጣ እንደሆነ ቢሰሙም ሌላው ቀርቶ እጅግ የካበት ልምድ አላቸው የሚባሉት ጽኑ ህሙማን ሐኪሞች እንኳን ግራ ግብቷቸዋል።

በዚህ ቫይረስ ከሚጠቁት ሰዎች አብዛኞቹ ቀላል የሚባሉ ምልክቶችን የሚያሳዩ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከነጭራሹ ምንም ምልክት አያሳዩም።

ነገር ግን በኮቪድ-19 ሕይወታቸውን እስከማጣት ከሚደርሱት መካከል አብዛኞቹ ከዚህ በፊት ሌላ ከባድ በሽታ ያለባቸውና የተወሳሰበ የጤና ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ናቸው።

በርካታ ዶክተሮች ልክ የኮሮናቫይረስ ዜና ሲሰማ የሳንባ ምች የሚያስከትልና የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ጉንፋን መሰል በሽታ አልያም ‘ሲዝናል ፍሉ’ (ወቅት ጠብቆ የሚከሰት ጉንፋን) ሊሆን እንደሚችል ገምተው የነበረ ቢሆንም፤ ቫይረሱ ግን ከዚህም የባሰ እንደሆነ ተረድተዋል ይላሉ የጽኑ ህሙማን ክፍል ዶክተር የሆኑት አንቶኒ ጎርደን።

‘’ኮሮናቫይረስ ከዚህ በፊት ከምናውቃቸው የመተንፈስ ችግር ከሚያስከትሉ በሽታዎች በእጅጉ ይለያል። በተጨማሪም ጉዳቶቹና ምልክቶቹ ከሰው ሰው የተለያየ መሆኑ ደግሞ ነገሮችን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርጋቸዋል’’ ብለዋል።

ሳንባ

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

የምስሉ መግለጫ, የኮሮናቫይረስ ታማሚ ስካን የተደረገ ሳንባ

የሳንባ ላይ ጉዳት

ኮሮናቫይረስ ጠንከር ያለ የጤና እክል የሚያስከትልባቸው ሰዎች ሳንባቸው ውሀ መቋጠርና የደም መርጋትን የመሳሰሉ ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል።

በወርሃ መጋቢት ቫይረሱ ፈጣን በሆነ መልኩ መሰራጨት ሲጀምር የኦክስጅን እጥረት ያጋጠማቸው ታማሚዎች በየሆስፒታሎች መታየት ጀምረው ነበር።

በተጨማሪም ከመተንፈሻ አካላላቸው በተጨማሪ ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ታማሚዎችም ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል በሚወሰዱ ጊዜ ዶክተሮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ተጋብተው ነበር።

"አንዳንድ ህሙማን በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የኦክስጂን መጠን እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ እንኳን እንደማንኛውም ጤናማ ሰው ሲንቀሳቀሱ መመልከት ደግሞ ያልተለመደ ነው" ይላሉ በሰሜናዊ ለንደን ዊቲንግተን ሆስፒታል ጽኑ ህሙናን ክፍል ውስጥ የሚሰሩት ዶክተር ሂዩ ሞንትጎመሪ።

‘’ቫይረሱ ኦክስጂን ወደ ሰውነታችን በአግባቡ እንዳይዳረስ ቢያደርግም በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ምናልባት ሳንባችንን ላይጎዳ ይችላል። ለዚህም ነው ብዙ ዶክተሮች ይህንን በሽታ ለማከም የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎችን መጠቀም ላይ የሚያንገራግሩት’’ ይላሉ።

ዶክተር ሂዩ ይህንን ያሉት ምንም እንኳን የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎቹ [ቬንትሌተር] ከፍተኛ እገዛ ቢያድርጉም ሳንባ ላይ ብቻ ማተኮሩ ለአንዳንድ ታማሚዎች ምንም ለውጥ ባለማምጣቱ ነው።

Lungs

እብጠትና ደም መርጋት

በኮሮናቫይረስ በምንያዝበት ወቅት የደም ቧንቧዎቻችን ያብጣሉ፤ ይህ ደግሞ ደማችን እንዲረጋ የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ ህመሙ በጣም በባሰባቸው ላይ የደም መወፈር ያስከትላል።

እንግሊዝ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ወደ ጽኑ ህሙማን ከፍል ከገቡ ሰዎች መካከል 2000 የሚሆኑት ኩላሊታቸው ስሥራውን አቁሞ ነበር።

ሌላው ከኮሮነቫይረስ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ታማሚዎች አንጎላቸው ውስጥ እብጠት መታየቱ ነው።

ይህ ደግሞ ታማሚዎቹ ግራ እንዲጋቡና የሌሉ ነገሮችን እንዲመለከቱ ያደርጓቸዋል፤ ባስ ሲል ደግሞ መንቀጥቀጥና ራስን መሳት ድረስ ሊሄድ ይችላል።

በሰውነታቸው ውስጥ የኦክስጂን እጥረት ሲኖር ደግሞ ነገሮች ይበልጥ ይባባሳሉ።

ከዚህ በፊት እንደ የደም ግፊት፣ ስኳርና የልብ ህመም ያለባቸው ሰዎች በቫይረሱ የመጠቃት እድላቸው ከፍ ያለ ቢሆንም ሌሎች ከግምት ውስጥ ሚገቡ ነገሮች እንዳሉም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

እነዚህም እንደ እድሜ፣ ጾታ፣ ውፍረትና መሰል ነገሮች ናቸው።

Blood

በተለይ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች

ብሪታኒያ መንግሥት ይፋ ባደረገው አንድ መረጃ መሰረት እንግሊዝ፣ ዌልስ እና ሰሜናዊ አየርላንድ ውስጥ ወደሚገኙ የጽኑ ህሙማን ክፍል ከገቡ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች መካከል 70 በመቶዎቹ ወንዶች ሲሆኑ፤ በተጨማሪም 70 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከመጠን በላይ ውፍረት ያላቸው ናቸው።

በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እያሉ ህይወታቸው ካለፈ ታማሚዎች መካከል ደግሞ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ነበር።

ምንም እንኳን አንዳንዶች ቀለል ያለ ምልክት አልያም ከነጭራሹ ምንም ምልክት የማያሳዩት፣ አንዳንዶች በቀላሉ ሲድኑ ሌሎች በጠና የሚታመሙት በእርግጠኝነት ለምን እንደሆነ ዶክተሮች ማወቅ ባይችሉም፤ የሰውነታችን አሰራርና የዘረመል ሁኔታዎች ድርሻ እንዳላቸው ግን በርካቶች ያምናሉ።

በአሁኑ ጊዜ የዘርፉ ባለሙያዎች ካሏቸው መልሶች ይልቅ የጥያቄዎቻቸው ቁጥር ከፍተኛ ነው።

Gut
ኮሮና
Banner