ዚምባብዌ የቅንጡ ባለሀብቶቿን የሀብት ምንጭ ልትመረምር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የገንዘብ ግሽበት በዳዴ እያስኬዳት የምትገኘው ዜምባብዌ ህመሟ ሮበርት ሙጋቤ ነበሩ ቢባልም ዛሬም መሻሻል አልሰመረላትም፡፡
በአገሪቱ ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ ዝቅጠት ለመገደብ የዚምባቡዌ ባለሥልጣናት አዳዲስ ሙከራዎችን ይዘዋል፡፡
ትናንት ይፋ የሆነ መረጃ እንደሚያስረዳው በዝምባብዌ አንድ ባለሀብት ፍርድ ቤት ከሙስና ነጻ ቢያደርገውም እንኳ የሀብት ምንጩን አሳማኝ በሆነ ሁኔታ ማስረዳት ካልቻለ ሀብት ንብረቱ ይታገድበታል፡፡
የዚምባብዌ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ማታንዳ ሞዮ እንዳሉት ከዚህ በኋላ የሚቀናጡ ባለሀብቶች ላይ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡
አሁን አሁን በዚያች አገር ሕዝቦች የዕለት ጉርሳቸውን ማግኘት እየተሳናቸው መጥቷል፡፡ ውሃና መብራት እንኳ በቅጡ ማግኘት ቅንጦት ሆኗል፡፡ የዳቦና የነዳጅ ወረፋውም አይጣል ነው፡፡ ዜጎች መኪናቸው ላይ ነዳጅ ጠብ ለማድረግ ከአንድ ቀን በላይ የተሰለፉበት አጋጣሚም ነበር፡፡
"አሁን የተያያዝነው ምርመራ ዘዴ የቅንጦት አኗኗር ዘዬን በሚከተሉ ባለሀብቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግን ነው፡፡ እንዲቀናጡ ያስቻላቸውን ገንዘቡን ከየት አመጡት? የሚቀናጡበት ሁኔታና ሀብታቸውስ አሳማኝ ነው? ለመሆኑ ግብር ከፍለው ነው የሚቀናጡበት? የሚለውን እናጠናለን" ብለዋል ኮሚሽነር ሞዮ።
የጸረ ሙስና ኮሚሽኑ በዚህ መንገድ የሰዎችን የሀብት ምንጭ እንዲመረምር ሥልጣን የተሰጠው በ2019 ነበር፡፡
በዚህ መንገድ ምርመራ የሚደረግባቸው የዚምባብዌ ባለሀብቶች ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሄደው የተጠየቁትን ማብራሪያ መስጠት ይኖርባቸዋል፤ ካልሆነ ግን ሀብት ንብረታቸው ይታገዳል፡፡
ዚምባብዌ ይህን የምርመራ ዘዴ በመጠቀም ደረጃ የመጀመርያ አገር አይደለችም፡፡
በዚህ የምርመራ ዘዴ መሰረት ባለሀብቱ የሀብት ምንጩን ንጹሕነት በቅጡ የማስረዳት ዕዳ ይኖርበታል፡፡
የሙስና ጉዳዮችን በማጥናት የሚታወቀው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ዚምባብዌ የኮሮናቫይረስ ሕክምና ቁሳቁሶች ግዢ ጨረታ ሂደትን ለሙስና የተጋለጠ እንደነበር ስጋቱን ገልጾ ነበር፡፡
ድርጅቱ እንዳለው ቁሳቁሶቹ ዋጋ እጅጉኑ ተጋኖ ነው ግዢ የተፈጸመው፤ ይህም ሙስና መኖሩን አመላካች ነው ብሎ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ የዚምባብዌ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ኦባዲህ ሞዮ የግዢ ሥርዓትን ባለመከተል ክስ ተከፍቶባቸዋል፡፡ በሐምሌ ወር ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡












