ከአስተናጋጅነት ምርጡን የአፍሪካ ባንድ የመሰረተው ሙዚቀኛ

የፎቶው ባለመብት, The Standard
በኬንያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ስመጥር ከሆኑት አንዱ የሆነው ጆን ንዜንዜ ከሰሞኑ ህይወቱ አልፏል።
ኬንያ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ወቅት፤ ግድያ፣ ስቃይና መቆርቆዝ የጥቁሮች እውነታ በነበረበት በዚያ ዘመን በሚያቀነቅናቸው ዘፈኖቹ ተስፋን መፈንጠቅ የቻለ ነው።
ድምጻዊ፣ ጊታር ተጫዋች፣ እንዲሁም ዳንሰኛው ጆን ንዜንዜ የኬንያን ትዊስት የተባለውንም የሙዚቃ አይነትም ከፍ ወዳለ ስፍራ በማድረስ አሻራውን ያኖረ ሙዚቀኛ ነው።
በጎርጎሳውያኑ 1960ና 1970ዎቹም በምሥራቅ አፍሪካ በፈንክ የሙዚቃ አይነት ምርጥ ሥራዎችን ካበረከቱት ባንዶች መካከልም አንዱ የእሱ ነበር።
"ታዋቂ ስትሆን በተወሰነ መልኩ እብሪተኛ ወይም ትዕቢተኛ መሆንህ አይቀርም። እኔም በእብሪተኛነቴ ነው የእራሴን ኤይር ፊየስታ ማታታ ባንድ የመሰረትኩት" በማለት ከመሞቱ በፊት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጿል።
ባንዱ ከኮንጎ የመጡ ስደተኞችንም ያካተተ ሲሆን በዓለም ላይ እውቅና ለማግኘትም የወሰደበት ጊዜ ጥቂት ዓመታትን ነው።
በጎርጎሳውያኑ 1968ም በአልጀሪያ ተካሂዶ በነበረው የመላው አፍሪካ የሙዚቃ ፌስቲቫልም በተደረገው ውድድር ባንዱ ሦስተኛ ወጥቷል።
ከአንድ ዓመት በኋላም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ለብዙ ወራት ቆይታ በማድረግ በርካታ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።
ቢቢሲ አፍሪካ ምርጡ የአፍሪካ ባንድ በሚል በ1971 ሽልማትን የሰጣቸው ሲሆን በወቅቱም ስመ ጥር ከነበሩት ከአሜሪካዊው ጄምስ ብራውንና ኦሲቢሳ ቡድንም ጋር አብረው ለንደን ውስጥ አቀንቅነዋል።

የፎቶው ባለመብት, President Records
በዚህ በለንደን በነበራቸው ቆይታ ከፍተኛ ሙገሳና ውደሳን ቢጎናጸፉም የባንዱ መጨረሻም ሆነ። የባንዱ በርካታ አባላት ኬንያውያኑም ሆነ የኮንጎ ዜግነት ያላቸው በእንግሊዝ ለመቆየት በመወሰናቸው የባንዱም ፍጻሜ ሆነ።
"ወደ ኬንያ ልንመለስ ስንል ኮንጎዎቹ የባንዳችን አባላት ኬንያ ውስጥ በስደተኝነት ከምንኖር እዚሁ ብንቆይ ይሻላል አሉ። በርካቶችም ለንደን ለመቆየት በመወሰናቸው ባንዱ ፈረሰ በማለት" ጆን ይናገራል።
ባንዱ ቢፈርስም ጆንን ብቻውን የሚወደውን ሙዚቃ ከመቀጠል አላገደውም። ሌሎች ባንዶችንም ተቀላቅሎ ተጫውቷል። በመዲናዋ ናይሮቢም ፊልኮ ለሚባል ስቱዲዮም ለተለያዩ ሙዚቀኞችም ፕሮዲውስ አድርጓል።
የሙዚቃውን ዓለም እንዴት ተቀላቀለ?
በወቅቱ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር በነበረችው የኬንያዋ መዲና በጎርጎሳውያኑ 1940 ነው የተወለደው። ትምህርቱን የተከታተለው በናይሮቢ እንዲሁም የቤተሰቦቹ የትውልድ ቦታ በሆነችው ምዕራብ ኬንያ ነው።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም አቁሞ በሆቴል ውስጥ በአስተናጋጅነት ተቀጠረ።
የሙዚቃ ጉዞው ግን የተጠነሰሰው ከዚያ በፊት ነው፤ በአስራዎቹ እድሜ ላይ እያለ የአባቱን ጊታር አንስቶ የሙዚቃ ህይወቱን 'ሀ' ብሎ ጀመረ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጊዜው ስመ-ጥር በነበረው ኖርፎክ ሆቴል ነው በአስተናጋጅነት የተቀጠረው። የሆቴሉ ሠራተኞችም ያድሩ የነበረው በዚያው በሆቴሉ ውስጥ ነበር።
ክፍሉን ይጋራው ከነበረው ዳውዲ ካባካም ጋር ሙዚቃዎችን ማቀናበር እንዲሁም መቅረፅ ጀመሩ።
ወደ በኋላ ግን ዳውዲ ብቻውን ሙዚቃዎቹን እንዳቀናበረ በተደጋጋሚ በመናገሩ ጆን ደስተኛ አልነበረም።
ለሙዚቃዎቹ ዳውዲ በብቸኝነት ስሙ በሬድዮ መነገሩ ያናደደው ጆን ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በመሆን ለሕዝብ ጆሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የደረሰውን 'አንጀሊክ' የተሰኘ ነጠላ ዜማውን ቀረፀ።
ከሁሉ በላይ ሙዚቃው በሬድዮ በመጫወቱ በወቅቱ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረለት ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር "ገንዘቡ አይደለም፤ ዋናው ለእኔ ሙዚቃዬ ነው" ብሏል።
በኬንያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ታዋቂ ከሆኑ ዘፈኖች ውስጥ አንዱ የሆነው 'አንጀሊክ' የሴት ፍቅረኛው ወደ ቤት እንድትመለስ የሚማፀን ሙዚቃ ነው።
ከአንጀሊክ በፊት ከዳውዲ ጋር አግኔታ ስለምትባለው ፍቅረኛውም ዘፍኖ ነበር። በወቅቱ ጆን ያላወቀው አግኔታ የዳውዲም ፍቅረኛ መሆኗን ነው።
ግጥሙም ላይ አግኔታን እንዴት ናይሮቢ እንደተዋወቃት፤ ይዋደዱ እንደነበርና በወቅቱ ባል ወይም ጓደኛ እንዳላት ሲጠይቃት እንደሌላት መንገሯን እናም አንድ ቀን እሷ ቤት ሄደው አብረው በተኙበት ወቅት በር ተንኳኳ።
ማነው ሲልም "የቤቱ ባለቤት ነኝ" አለው። ግጥሙም ላይ አግኔታ ይህ ሥራ ኣሳፋሪ ነው ይላታል። ሁለት ፍቅረኛ መያዝ ይላል። ከሰውየው ጋርስ ተጣልቼ ቢሆን? ተጎዳድተንስ ቢሆን? ምን ታደርጊ ነበር በማለት በግጥሙም ይጠይቃል።
ጆን ሙዚቃው በራሱ እውነተኛ የህይወት ታሪክ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የሴቶቹን እውነተኛ ስም ግን ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።
If a woman loves your song, even the men will love it"
በሚስረቀርቅ ዜማ የብዙዎች ልብ ውስጥ መግባት የቻለው ሙዚቀኛ ዝናንም ማትረፍ የቻለው ፍቅርን በውብ ቃላት መግለፅ በመቻሉ ነው። በወቅቱ በተለያየ ጊዜ ይወዳቸው ለነበሩ ሴቶች የነበረውን ፍቅር ገልጿል፤ ልብ ስብራቱንም እንዲሁ።
"ሴቶችን በሙዚቃህ ማስደሰት ካልቻልክ ሙዚቃህ ብዙ ትርጉም አይኖረውም። ሴቶች ሙዚቃህን ሲወዱ ነው ወንዶችም የሚከተሉት" በማለትም በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር።
"ወጣቶች ነበርን፤ ፍቅርም ውስጥ ነበርን" በማለት አክሏል።
ጆን በመድረክ አዘፋፈኑ እንዲሁም ታዳሚዎቹን በዘፈኖቹ በመማረክ ከፍተኛ ሙገሳና ውደሳን አትርፏል። ከዚህ የመድረክ ስጦታውም ጋር ተያይዞ በርካታ የዘመኑ ዘፋኞች ሙዚቃቸው ከጥበቡ ይልቅ ለቴክኖሎጂ ከፍተኛ ስፍራ በመስጠታቸው ሥራቸውንም ሆነ ሙዚቃውን አያውቁትም በማለትም ተችቷቸዋል።
"አንዳንድ ሙዚቀኞች የትኛው የሙዚቃ መሳርያ ቁልፎች ላይ ዘፈኖቹ እንደሚያርፍ እንኳን አያውቁም፤ አቀናባሪው ብቻ ነው የሚያውቀው" ብሏል።
የእሱ ሙዚቃዎች ከግጥም ይዘታቸውም ጋር ተያይዞ ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገር እንደቻሉም በኩራትም ይናገራል።
"የእኔ ሙዚቃ የግጥም ጥልቀት ነበረው፤ ሙዚቃውም ጊዜ ተወስዶበት በደንብ ተደርጎ ነው የተሰራው። የዘመኑ ግን ዛሬ ተሰርተው ለነገ ይቀርባሉ። ወዲያውም ይሰለቻሉ" በማለት ከአምስት ዓመት በፊት ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።
ከአንጀሊክ በተጨማሪ በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነትን ማትረፍ የቻሉት በስዋሂሊ ከተቀነቀኑት መካከል 'ኒናሙይሊላ ሱዛና' (ለሱዛን እያለቀስኩ ነው)፣ 'ኒ ቪዙሪ ኩዋ ና ቢቢ' (ሚስት ሲኖርህ መልካም ነው)፣ 'ማርሻይ ያ ዋሬምቦ' (የሴቶች ሽቶ) የመሳሰሉ ሙዚቃዎቹ ይገኙበታል።
ነገር ግን ለቢቢሲ እንደተናገረው የአንጀሊክን ያህል ድንበሮችን የተሻገረ እንዲሁም በሌላው ዓለምም መግነን የቻለ ሙዚቃ እንደሌለው ተናግሮ ነበር።
በጎርጎሳውያኑ 2004 ወራትን ባስቆጠረው የመርከብ ጉዞ ላይ ጃፓንን ጨምሮ በሲንጋፖርና በሌሎች አገራትም ለወራት ያህል ተጫውቷል።
"የሆነ ደረጃ ላይ ከደረስክ በሙዚቃህ ገንዘብ ታገኝበታለህ። አንጀሊክ በርካታ አገራት ወስዶኛል" ብሎም ነበር።
በጎርጎሳውያኑ 2014ም ከሌላ ኬንያዊ ሙዚቀኛ ፒተር አክዋቢ ጋር በመሆን በአሜሪካ የሙዚቃ ጉዞ ያደረገ ሲሆን በስሚዝሶኒያን ፌስቲቫልም ላይ ተጫውቷል።
ይህ ጽሑፍ በGoogle YouTube. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የGoogle YouTube ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ YouTube ይዘት መጨረሻ
ከተወዳጅ ሙዚቀኛነቱም በተጨማሪ ለሌሎች ሙዚቀኞች ያለውን ድጋፍም በተለያየ መንገድ ያሳይ የነበረ አርቲስት ነው።
እንደ ሌሎች አገራት በኬንያ የሚገኙ ሙዚቀኞች ሥራዎችም በሕገወጥ መንገድ ተባዝተው ጎዳናዎች ላይ ይቸረቸራሉ። የተለያዩ የምሽት ክበቦችም ሆኑ የመዝናኛ ቦታዎች ያለ ሙዚቀኞቹ ፈቃድ ያጫውታሉ።
ይህንንም ለመታገል ከቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ጋር የሚሰራ የኬንያ የሙዚቃ ቅጅ መብቶች ማኅበርን ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በመሆን መስርቷል። የቦርድ አባልም ሆኖ ለብዙ ዓመታት አገልግሏል።
የኬንያ መንግሥት ሙዚቀኛው በአስርት ዓመታት ውስጥ ላበረከተውም ጉልህ ሚና በጎርጎሳውያኑ 2009 ሽልማት አበርክቶለታል። ከሌሎች አራት ስመ ጥር ሙዚቀኞችም ጋር በመሆን የአገሪቱን ከፍተኛ ሽልማት በወቅቱ ከነበሩት ፕሬዚዳንት ምዋይ ኪባኪ እጅ ተቀብሏል።
በጎርጎሳውያኑ 2016 ጡረታ የወጣ ሲሆን፤ ኑሮውንም በምዕራብ ኬንያ በምትገኘው ካይሞሲ በምትባል ግዛት አድርጎ ነበር። የ80 ዓመቱ ሙዚቀኛ በካንሰር ህመም ሲሰቃይ ቆይቶ ህይወቱ ያለፈው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር።
የኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ለሙዚቀኛው የነበራቸውን አድናቆት እንዲሁም የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል "ለሙዚቃ የተሰጠች ነፍስ ነበረው። ድምፁ የሚገርም ነበር። በሙዚቃዎቹ ላይ ያሳየው ፈጠራና ችሎታ የዘመኑ ወርቃማ ሙዚቀኛ ብለው አያንሰውም" ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ አክለውም "ጥሎልን ባለፈው ድንቅ ሙዚቃዎቹ ሁልጊዜም እናስታውሰዋለን። ስሙ ከመቃብር በላይ ነው። አንረሳህም" ብለዋል።












