“ከአሁን በኋላ ስለወላይታ የሚመለከተው የዞኑ ምክር ቤት ብቻ ነው የሚል እምነት አለኝ”

የወላይታ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አበበች እራሾ

የፎቶው ባለመብት, Ethopan Insider

በደቡብ ክልል ምክር ቤት እኣካሄደው ባለው ጉባዔ ላይ የወላይታ ዞን ተወካዮች አለመሳተፋቸው ተሰምቷል።

ከስብሰባው ቀደም ብሎም በልዩ ስብሰባ ላይ ላለመሳተፍ መወሰናቸውን የወላይታ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አበበች እራሾ ለመገናኛ ብዙሃን ገልፀው ነበር።

የወላይታ ዞን በደቡብ ክልል 39 መቀመጫዎች እንዳሉት የሚታወቅ ሲሆን የዞኑ ተወካይ የምክር ቤት አባላት ትናንት በተጀመረው የክልሉ ጉባኤ ላይ እንዳልተሳተፉ ገልፈዋል።

በበምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ የዞኑ ተወካዮች ላለመሳተፍ የደረሱበትን ውሳኔ ምከንያት ሲያስዱም የዞኑ ሕዝብ ለምክር ቤቱ ያቀረበው በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ "ተደማጭነት አላገኘም" በሚል መሆኑን ገልፀዋል።

የወላይታ ዞን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በራሱ ክልል ሆኖ ለመደራጀት ጥያቄውን ቢያቀርብም ሳይታይ በመቅረቱ የተነሳ ለፌሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ ማለታቸውን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት አስረድተዋል።

አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ አበበች እራሾ የወላይታ ሕዝብ ጥያቄውን በተገቢው መልኩ ለክልሉ ምክር ቤትም ሆነ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን አስረድተው፤ ከአሁን በኋላ የወላይታ ብሔን የሚመለከቱ አጀንዳዎች ቢኖሩ በብሔሩ ምክር ቤት ካልሆነ በፌደራል መስተናገድ አለባቸው እንጂ እኛ በሌለንበት በክልሉ ምክር ቤት መሆን የለበትም ብለዋል።

ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እነሆ፡

በክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ላለመሳተፍ የወሰናችሁበትን ምክንያት እስቲ አስረዱኝ?

የወላይታ ብሔርን በክልል የመደራጀት ጥያቄ በተመለከተ ከአንድ ዓመት በፊት ነው ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ያቀረብነው። ያንን ጥያቄ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሕገ መንግሥቱ መሰረት መመለስ ነበረበት፤ ሥልጣኑ እስከዚያ ድረስ ነው። ሪፍረንደም ማደራጀት ነው። አላደራጀም።

ከዚህ የተነሳ በዞኑ ላይ በርካታ ውጥረቶች ነበሩ። ይመለሳል በሚል እምነትም ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች በሕጋዊ መንገድ ይመለሳሉ የሚል ተስፋ ተጥሎ ስንከታተል እስከ ታህሳስ 10/2012 ድረስ አንድ ዓመት እስኪሆነው ጠብቀናል።

እስከዚያ ድረስ የተመለሰ ምንም ምላሽ የለም። ስለዚህ እኛ የብሔሩ ተወካዮች በክልሉ ምክር ቤት ወደ 39 መቀመጫ ነው ያለው። ስለዘህ በተለያዩ ጊዜ በተገኙ አጋጣሚዎች፣ በተደረጉ መደበኛ ያልሆኑ ጉባኤዎች አስፈላጊ ጉዳዮች በሚካሄዱበት ሁሉ አጀንዳው እንዲቀርብ በጽሁፍ የአሰራር ደንቡ በሚፈቅደው መሰረት ጠይቀናል።

አባላት ደግሞ በየጊዜው በጉባዔ ላይ ተገኝተን በሚሰጠው እድል ለመጠየቅ ተሞክሯል። የሕዝባችንን ድምጽ ለመስማት ፍላጎት የለም። ስለዚህ ከዚህ የተነሳ እኛ ቀጣይ ምንድን ነው ማድረግ ያለብን የሚለውን የብሔሩ ምክር ቤት አስተዳደር አስቸኳይ ጉባኤ ተጠርቶ ነው ይግባኝ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሄድ ያደረገው።

ስለዚህ ደቡብ ክልል ምክር ቤት ከአሁን በኋላ ለእኛ ምንም የሚሰጠው ምላሽ እንደሌለ ታምኖበት አባላት ቀጣይ በሚኖሩ ጉባዔዎች አንገባም የሚል አቋም ተይዞ ነው ያልገባነው።

ይህ ማለት ዞኑ ከአሁን በኋላ በደቡብ ክልል ምክር ቤት ውስጥ ወካይ የለውም ማለት ነው?

ተወካይ ቢኖር ባይኖር የሚተላለፉ ውሳኔዎች በአብላጫ ድምጽ ነው። የእኛ ጉዳይ የብሔሩ ፍላጎት እየታየ አይደለም። የውክልና ተግባር ሕዝብን እንጂ ግለሰብ እዚያ መቀመጫ ኖሮት፣ ቢገባም ባይገባም ያለው የአብላጫ ድምጽ ነው።

ብሔሩ የራሱ ፍላጎት እየተጠበቀለት ስላይደለ የሌላው ፍላጎት ላይ ብቻ ውሳኔ እያስተላለፈ የሚመለስበት አሰራር ነው እስካሁን ድረስ ያየነው፤ ስለዚህ ይህ ለእኛ የሕዝቡን ክብር ማስጠበቅ ካልቻልን እዚያ ለሚቀጥሉት ጊዜያት መገኘት አስፈላጊ አይደለም።

አሁን የተያዘው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕዝቡን ጥያቄ መመለስ አለበት የሚለውን የእኛን ጥያቄ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ ነው።

የአባላቱ ቀጣይ እርምጃዎች ምንድን ነው የሚሆነው?

ቀጣይ እምጃ የሚሆነው እኛ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ አስገብተናል። አሁን ከደቡብ ክልል ተከታትለን የምናገኘው ምላሽ የሚኖር አይመስለኝም። ስለዘህ ቀጣይ እርምጃው ፌዴሬሽን ምክር ቤት በአፋጣኝ ከምርጫ ቦርድ ጋር ተነጋግሮ የብሔሩን ሪፍረንደም እንዲያደራጅ የመከታተል ሥራ ነው የምንሠራው።

በቅርቡ በተደረገ ስብሰባ የደቡብ ክልል እንደ አዲስ እንደሚራጅ ተሰምቷል። ይህ ውሳኔን እስከ መጨረሻው ታግሳችሁ ለመከታተል አላሰባችሁም ነበር?

አንደኛ እሱ ጉዳይ የእኛ ጥያቄ አይደለም። በዚህ መልኩ የደቡብ ክልል እንዲደራጅ የእኛ ጥያቄ እዚያ ውስጥ የለበትም። የጠየቅነው ራሱን ችሎ በክልል የመደራጀት ጥያቄ እና ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ነው።

ከዚያ ውጪ ያሉ ጥያቄዎች እና የሚወከሉ አካላትም ሕዝብ ተመራጮች ስላይደሉ በእርሱ ጉዳይ ውስጥ ብዙም ተሳትፊ አይደለንም። ለመሳተፍም አንፈልግም።

እኛ ሕዝቡ የብሔሩ ጥያቄ እንዲመለስ ሕጋዊና ሕገመንግሥታዊ ጥያቄዎችን ነው ያቀረብነው። አሁን የተጀመረው ነገር የአገሪቱ መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት የሚያድጋቸው ካልሆኑ በስተቀር ወደ ሕዝብ ቀርበው ሕዝብ ተችቶ ይመቸኛል ብሎ ሕዝብ የተቀበለው ነገር አይደለም።

ስለዚህ አልተወያየንበትም እያሉኝ ነው?

እኛ አልተወያየንም።

አዲስ አበባ ላይ በነበረው ስብሰባ ላይ ተገኝታችሁ የነበራችሁን ቅሬታ አስረድታችሁ ነበር?

እኛ ልንገኝም አንችልም። እኛ እኮ የሕዝቡን ጥያቄ፣ እኔ አሁን እንደ አፈ ጉባኤ የሕዝቡን ጥያቄ ነው የማስተባብረው እንጂ በዚያ ጉባኤ ላይ ልገኝም አልችልም። መገኘትም አልፈልግም። ምክንያቱን እርሱ አይደለም ጥያቄያችን።

ስለዚህ በዚያ መልኩ ሊመለስ ከሆነ ራሱ አጀንዳውን አምጥቶ፣ ሕዝብ ሰብስቦ ማወያየት ያለበት ራሱ ነው። የኛ ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሰረት እንዲመለስ ብቻ ነው የምንፈልገው።

ወላይታ ዞንን ወክሎ በስብሰባው ላይ እንዲገኝ የተጋበዘ ነበር?

የተጋበዙ አካላት ይኖራሉ። ግን እርሱ ላይ እኔ አስተያየት መስጠት አልፈልግም።

ኮሮናቫይስ በተስፋፋበት በዚህ ወቅት የእናንተን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ እድል ይኖራል ብለው ያምናሉ?

እኔ እንግዲህ ኮሮናቫይረስ በአገራችን ላይ ከተከሰተ ወራት አስቆጥሯል። አሁን የምናነሳው ጥያቄ የአንድ ዓመት እድል የነበረው ነው። ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሄደም ስድስት ወር ያስቆጠረው ነው። በፍጥነት ከምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ሪፍረንደም እንዲካሄድ የመስራት ጉዳዮች መስራት ከተቻለ እኮ የሁለት የሦስት ቀን ሥራ ነበር። ግን አልተሰራም።

ይኼ ነገር አሁን በዚህ ወቅት ይመልሳሉ ወይ? አላውቅም። የራሳቸው የተሰጣቸው ስልጣን ስለሆነ በራሳቸው ስልጣን ገደብ ውስጥ ሆነው የሚሰጡትን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው።

አገሪቱ የኮሮናቫይረስ ወረረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል በሚል የጣለችው የተለያዩ ገደቦች አሉ። በዚህ ገደብ ውስጥ ሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ የምርጫ ቦርድ የወላይታን ጥያቄ መመለስ ይቻላሉ ብለው ያምናሉ?

የሚቻልባው መንገዶች አሉ። ካልተቻለም እኮ ለሕዝቡ መነገር አለበት።

አልችልም ብሎ መንገር አለበት እንጂ ሰበቡ አሁን ስለመጣ፤ በሰበብ ውስጥ ሆኖ የሕዝቡን ጥያቄ ማፈን አይቻልም።

እናንተ ሁላችሁም ከደቡብ ክልል ምክር ቤት ወጥታችኋል እንደነገሩኝ፤ በደቡብ ክልል የሚተላለፉ ውሳኔዎች ቢኖሩ ጥያቄዎች ተቃውሞዎች ቢኖሩ የወላይታ ሕዝብን ወክሎ የሚናገረው በምክር ቤት ውስጥ አሁን ማነው?

የሚቀርቡ አጀንዳዎች ናቸው የሚወስኑት። በብሔሩ ጉዳይ ከአሁን በኋላ መወሰን የሚችለው የብሔሩ ምክር ቤት ነው የሚል እምነት አለኝ። በብሔሩ ጉዳይ ማንም ከእዚያ ወላይታ እንዲህ ይሁን ብሎ አንስቶ ሊናገርም፣ ሊወስንም አይችልም።

ስለዚህ ብሔሩን የሚመለከቱ አጀንዳዎች ቢኖሩ በብሔሩ ምክር ቤት መመራት አለባቸው። ካልሆነ በፌደራል መስተናገድ አለባቸው እንጂ እኛ እዚያ ባልተገኘንበት እና በሌለንበት ሁኔታ ስለእኛ አንስቶ ማንም ሊያወራ አይችልም። አጀንዳው ያድር ይሆናል እንጂ የሚል እምነት ነው ያለኝ።

በሕዝቡ ጉዳይ ላይ ማንም ሌላ አካል ሊወስን አይችልም። ግን በራሳው አጀንዳዎች፣ ብሔርን በማይመለከቱ፣ አገርን ለመምራት ሕዝብን ለመምራት የሚሆኑ አጀንዳዎች በሚኖሩበት ጊዜ በአብላጫ ድምጽ እየሰሩ መቆየት ይችላሉ።

ስለዚህ ከአሁን በኋላ ስለወላይታ የሚመለከተው የብሔሩ ምክር ቤት እንጂ የደቡብ ምክር ቤት አይደለም እያሉኝ ነው?

አዎ!