የዘር ጥላቻን የሚያራግቡ የፌስቡክ ጓደኞቻችንን ምን እናድርጋቸው?

ሁላችንም ቢያንስ አንድ የሆነ ጽንፈኛና የዘር ጥላቻን የሚያራግብ የፌስቡክ ጓደኛ ይኖረናል። የሚጽፋቸው ነገሮች የሚያቆስሉ፣ የሚሰጣቸው አስተያየቶች የሚያበግኑ።
ይህን ሰው እንምከረው ወይስ "እንቦልከው"?
እኔን አሁን መከራ እያበላኝ ያለ አንድ አብሮ አደጌ አለ። የፌስ ቡክ ጓደኛዬ ነው። በዘር ጥላቻ የተለከፈ ነው።
የእርሱን የፌስቡክ ሰሌዳ ጭራሽ ባላየው ደስ ይለኛል። ቶሎ ቶሎ ገረፍ አድርጌ ለማለፍ እሞክራለሁ።
ይህ ሰው አሁን የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ ዘረኝነቱ ብሶበታል።
ብዙ ሰዎች ስለእርሱ ስነግራቸው "አንቺ ደግሞ ቀለል አድርጊው እስኪ፤ አታካብጂ" ይሉኛል።
ለምን ቀላል ነገር አድርገው እንደሚያስቡት አይገባኝም። ለእኔ እጅግ ዘረኛ አስተያየቶችን ከፌስቡክ ጓደኞቼ ሰሌዳ ላይ ስመለከት የሆነ የማቅለሽለሽ ስሜት አለው።
ከፌስቡክ ውጪም እንዲሁ ነው። ሰዎች በተለያየ መንገድ ነው ዘረኝነታቸውን የሚያንጸባርቁት፤ አውቀውም ሆነ ሳያውቁት።
ለምሳሌ እዚህ እንግሊዝ ውስጥ ብዙ ሰዎችን ስተዋወቅ "የእኔ ቆንጆ ከየት ነሽ?" ይሉኛል፤ ልክ እንደ ብርቅዬ እንሰሳ እየተመለከቱኝ።
"ከዚሁ ከእንግሊዝ" እላቸዋለሁ።
"ማለቴ የምር ከየት ነሽ. . . ?" ይሉኛል። በሌላ ቋንቋ (የቆዳ ቀለምሽን አይተሽዋል? ፈረንጅ አይደለሽም እኮ፤ ይህ የፈረንጅ አገር ነው።) እያሉኝ ነው።
ይህ ዓይነቱ አስተያየት እኔና እህቴ ድሮ ወደ አንደንዳንድ የለንደን ቡና ቤቶች መሄድ ለምን እንፈራ እንደነበር ያስታውሰኛል።
ቡና ቤቶቹ ውስጥ ለመስተናገድ ስንገባ "የእኛ ደንበኞች እኮ በብዛት የአውሮፓ ጎብኚዎች ናቸው" ይሉናል። ምን ማለታቸው ነው? (ጥቁሮች እባካችሁ አትምጡብን እያሉን ነው)
ሌላው ግርም የሚሉኝ ጸጉሬን የሚነካኩ ሰዎች ናቸው። እኔምለው? የሆነች የቤት ውስጥ ድመት ነው እንዴ የምመስላቸው?
ዘረኝነት አንድን ጥቁር "አንተ ኔግሮ!" ብሎ መጥራት ብቻ የሚመስላቸው አሉ። ዘረኝነት እጅግ ውስብስብና ጥልቅ ጉዳይ መሆኑን ለምን አይረዱም?
አሁን እዚህ ፌስቡኬ ላይ እየመጣ ዘረኛ አስተያየት የሚሰጠውን ጓደኛዬን ምን እንደማደርገው ግራ ገብቶኛል። ለእርሱ ዝቃጭ አስተያየት መልስ መስጠት በራሱ ጉልበትን መጨረስ ሆኖ ይሰማኛል።
ግን ደግሞ እንዲህ ሲንዘባዘብ ዝም ማለትም አግባብ መስሎ አልተሰማኝም። ዝም ሲባል ትክክል የሆነ ቢመስለውስ?
በመጨረሻ አንድ ነገር ለማድረግ ወሰንኩ። ከዚያ በፊት ግን አሁን የምፈልገው "አንፍሬንድ" የሚለውን ቁልፍ ልጫን ነው ወይስ ምላሽ ልስጠው? በሚል ከእራሴ ጋር ተሟገትኩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማኅበራዊ ሥነልቦና አዋቂ ዶክተር ኬዎን ዌስት እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች ግለሰቡ ምን ማሳካት ነው የፈለገው በሚለው ላይ የሚወሰኑ ነው የሚሆነው ይላል ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ምክሩን ሲለግስ።
"ጤናሽን መጠበቅ ከፈለግሽ ለእንዲህ ዓይነት የፌስቡክ ጓደኞችሽ ባትመልሺ ይመረጣል። ለእነርሱ ምላሽ ብትሰጪ ጨጓራሽን ይበልጥ ይልጡታል።"
". . .ነገር ግን ዓላማሽ ነገሮችን ቀስበቀስ እንዲረዱና ባንቺ ጫማ ውስጥ ሆነው ሁኔታዎችን እንዲያገናዝቡ ከሆነ፤ መልስ መስጠቱ ክፋት የለውም።"
". . . እርግጥ ነው እንደነዚህ ዓይነት ዘረኞች ባንቺ አስተያየት ዘረኝነታቸውን እርግፍ አድርገው ይተዋሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን መባል ያለበትንና መባል የሌለበትን ነገር እያወቁ እንዲመጡ ምክንያት ትሆኛቸዋለሽ።"
ይህ የዶክተር ኬዎን ምክር ልክ ሊሆን ይችላል።
እኔ ፌስቡክ ላይ አስተያየት ስሰጥ ሁልጊዜም "ጀመረሽ ደግሞ ይቺን የዘር ጨዋታ ልታመጫት ነው?" ይሉኛል።
ሌሎች ጓደኞቼን በነገሩ እንዲያማክሩኝ ጠየቅኳቸው። "ኧረ ለመሆኑ ምንድነው የምታደርጉት? ዘረኛ ሰው ፌስቡክ ላይ ሲገጥማችሁ? አልኳቸው።"
አንዷ ጓደኛዬ አሊሻ ስታንዲንግ 27 ዓመቷ ነው።
አሊሻ "ለዘረኛ አስተያየቶች ምላሽ መስጠት ጀመሬ ነበር። የሚገርምሽ እየባሰባቸው ሄደ" አለችኝ። ቀጠለች፣
"ለምሳሌ ልንገርሽ። 'ብላክ ላይቭስ ማተር' በሚለው እንቅስቃሴ ዙርያ አስተያየት ለጥፌ አንዱ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? 'አንቺ ለዚህ አስተያየትሽ መደፈር ነበረብሽ' አለኝ። ከዚያ በኋላ ነው ሰዎችን "መደለትና መቦለክ" የጀመርኩት። ነገሩ መጀመርያ አካባቢ ያስፈራኝ ነበር። ኋላ ላይ ግን እየለመድኩት መጣሁ።"
አሊሻ ይህን ታድርግ እንጂ ለሰዎች ምላሽ መስጠት አንዳንድ ጊዜ ነገሩን ደጋግመው እንዲያስቡት እንደሚያደርጋቸው ነግራኛለች።
"ለምሳሌ እንደዚያ የሰደበኝ ቀን ከምቦልከው ጠንካራ ምላሽ ብመልስለት ወደቤቱ ሲመለስ ቢያንስ ነገሩ እየከነከነው ይሄድ ነበር" ብላ ተቆጭታለች።
ካሲያ ዊሊያምስ ሌላኛዋ ወዳጄ ናት።
ካሲያ ባሏ ዘረኝነት ብዙ ጊዜ ያጋጥመዋል። ይህን ስለምታውቅ ፌስቡክ ላይ ማንኛውም ዘረኛ ሰው ሲያጋጥማት በቻለችው ሁሉ ትፋለማቸዋለች።
"ቸል ልላቸው አልችልም፤ ብዙ ሰዎች ምላሽ ከሰጠኋቸው በኋላ አመስግነውኛል። ነገር ግን ሁሉም ሰዎች እንደዚያ ናቸው ማለት አይቻልም። አንዳንዶች ምላሽ ስትሰጫቸው የሚሆኑትን ነገር ስታይ ጊዜሽን ማጥፋትሽ ያናድድሻል።"
ዶ/ር ዌስት በዚህ ረገድ ምክር አላቸው።
"ለአንድ ሰው ለዘረኛ አመለካከት ምላሽ ሲሰጥ ያንኑ ምሽት ዘረኝነታቸውን እርግፍ አድርገው እንዲተዉ ከጠበቃችሁ ሞኞች ናችሁ። በኢንተርኔት አንድ ሁለት ስለተባባላችሁ የሚለወጥ ነገር የለም። ነገር ግን ከዚያ በኋላ የሆኑ ሰዎች እነርሱ በሚጽፏቸው ነገሮች ስሜታቸው እንደሚጎዳ ማሰብ ይጀምራሉ።"
ማቲው ኮሊንስ ደግሞ "ዘረኝነት በእኛ ይብቃ!" ወይም "ኖትሄት" የተባለ የጸረ ዘረኝነት ተቋም መሪ ነው።
ዘረኝነት ከፍርሃትና ከግንዛቤ ማነስ የሚመነጭ ነገር ነው ይላል።
ለምሳሌ ዘረኞች የብላክ ላይቨስ ማተርን እንቅስቃሴ ሲመለከቱ 'እኔ የሌለኝን ነገር እነርሱ እንዴት ይኖራቸዋል?' በሚል ነው መተናኮስ የሚጀምሩት።
እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች እነርሱን የሚያጠፋቸው ስለሚመስላቸው ይፈራሉ ይላል።
ማቲው እንደሚለው ማኅበረሰቡ ጠንካራ አመራር ይሻል። የእነዚህን ሰዎች ፍርሃት ሊገፍላቸው የሚችል ከእነርሱ ከእራሳቸው የወጣ ብዙ አመራር ቢኖር ነገሩ ጥሩ መልክ እየያዘ ይመጣ ነበር።
"የጥቁር መብት ላይ ስንሰራ በርካታ ተቃውሞ እንደሚመጣብን መረዳት አለብን። የሚለው ማቲው እንቅስቃሴው ለብዙዎች የፍርሃት ምንጭ ነው። ዘረኛ ነጮች የሚያስቡት እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች በተፋፋሙ ቁጥር ከእነርሱ ድርሻ የሆነ ነገር እየተወሰደባቸው እንደሆነ ነው" ሲል ያብራራል።
ይህን ሁሉ ሐሳብ ተቀብዬ፣ አሰላስዬ አውጥቼና አውርጄ ወደ ፌስቡኬ አመራሁ።
አሁንም ያ ዘረኛ ጓደኛው ጸያፍ ነገር ጽፏል። በአንድ ጥቁር ጓደኛዬ የፌስቡክ ጽሑፍ ሥር በጥቁሮች ላይ ለማላገጥ የሞከረውን ነገርም ተመለከትኩ።
ልቤ ደከመብኝ። ተሰላቸሁ፤ ከዚህ ሁሉ ለምን አልገላገልም አልኩ። ያቺን ቁልፍ ተጫንኳት፡፡ "Unfriend!" ከጓደኝነት አሰናበትኩት።
[የዚህ ጽሑፍ አሰናጅ ቼሪ ዊልሰን ናት። በሼፊልድ ጋዜጠኝነት አጥንታለች። ከቤተሰቧ ወደ ዩኒቨርስቲ በመግባት የመጀመርያዋ ናት።]












