'ትሁቱ' እና 'ሐይማኖተኛው' ጀነራል አዲሱ የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ማን ናቸው?

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተመራጩ ፕሬዝዳንት ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ

ዛሬ የሥልጣን መንበራቸውን በቃለ መሐላ የሚረከቡት የ52 ዓመቱ የቡሩንዲው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ በብዙዎች ዘንድ "ትሁት" እና "ሐይማኖተኛ" እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ወዳጃቸውና የትግል አጋራቸው ሟቹ ፕሬዝደናት ፒየር ንኩሩንዚዛ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ውስጥ "ከፍተኛ ተጽዕኖ" የነበራቸው ጀነራል ሆነው ቆይተዋል።

በብዛት 'ኔቫ' በመባል የሚታወቁት ሜጀር ጀነራል ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1968 በማዕከላዊ ቡሩንዲ በምትገኘው የአገሪቱ የፖለቲካ ማዕከል ጊቴጋ ግዛት ውስጥ ነው የተወለዱት።

በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አሸንፈው ወደስልጣን መጥተው የነበሩት የሚልቺየር ንዳዳዬ ግድያን ተከትሎ በ1993 (እአአ) የእርስ በርስ ጦርነት ሲቀሰቀስ ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ በቡሩንዲ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሕግ ተማሪ ነበሩ።

በወቅቱ ልክ እንደ ቀድሞው ፕሬዝዳንት ሁሉ እሳቸውም በዋና ከተማዋ ቡጁምቡራ ውስጥ በሁቱ ተማሪዎች ላይ ከተፈጸመው ግድያ ተረፈዋል። ከዚህ በኋላም ሸሽተው ከአገራቸው በመውጣት በቱትሲዎች የሚመራውን መንግሥት ከሚፋለሙት አማጺያን ጋር ተቀላቀሉ።

ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ የቀድሞው መሪ ፒየር ንኩሩንዚዛ ወደስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ደጋፊያቸው በመሆን ታንዛኒያ ውስጥ በመንግሥትና በአማጺያኑ መካከል የሠላም ንግግር በሚደረግበት ጊዜ በቅርበት አብረዋቸው ይሰሩ ነበር።

አማጺያኑ ከመንግሥት ጋር የስልጣን መጋራት ስምምነት ላይ ሲደርሱ ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ የቡሩንዲ ጦር ምክትል ኤታማዦር ሹም ሲሆኑ ንኩሩንዚዛ ደግሞ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኑ።

ከዚያም ንኩሩንዚዛ የፕሬዝዳንትነት ቦታውን ሲይዙ እሳቸው የፕሬዝዳንቱ ወታደራዊ አማካሪ ከመሆናቸው ጥቂት ቀደም ብሎ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርም ሆነው ነበር።

ከአስር ዓመት በኋላም ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ የገዢው ፓርቲ ዋና ጸሐፊ በመሆን እስከዚህ ዓመት ድረስ ቆይተው ባለፈው ወር የተካሄደው ምርጫ ሲቃረብ ንኩሩንዚዛ የፕሬዝዳንትንቱን ቦታ እንዲይዙ እጩ አደረጓቸው።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት የስድስት ልጆች አባት ሲሆኑ የሮማ ካቶሊክ ዕምነት ተከታይ ሲሆኑ ሟቹ ንኩሩንዚዛ ይከተሉት የነበረውና "እግዚአብሔርን ማጉላት" የሚሉትን የፖለቲካ አመለካከት እንደሚያራምዱ ይነገርላቸዋል።

አዲሱ ፕሬዝዳንት ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ ዛሬ ሐሙስ በመሪነት የሚረከቧት ቡሩንዲ በዲፕሎማሲው መስክ የተገለለችና ከለጋሾች ጋር ያላት ግንኙነትም የሻከረ ነው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ በስልጣን ዘመናቸው በተቃዋሚዎቻቸው፣ በጋዜጠኞችና በመብት ተከራካሪዎች ላይ በሚወስዱት ጠንካራ እርምጃ በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሲከሰሱ ቆይተዋል።

ቡሩንዲ የኮሮናቫይረስ ስጋት ያጠላባት ስትሆን ሟቹ ፕሬዝዳንት ግን ችግሩን ሲያቃልሉት ቆይተዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በንኩሩንዚዛ ላይ የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ በሺህዎች የሚቆጠሩ የቡሩንዲ ዜጎች በጎረቤት አገራት ውስጥ ወደ ሚገኙ የስደተኛ ካምፖች ፈልሰዋል።

ዛሬ የቡሩንዲ መሪነት መንበርን የሚረከቡት ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ የሚመሰርቱት አዲስ መንግሥት ከዚህ በፊት ታጥፎ የነበረውን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታን ወደነበረበት ይመልሳል ተብሎ ይጠበቃል።