ትራምፕ እንዳይታተም ባሉት መጽሐፍ ይፋ የሚደረጉ 6 ምስጢሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጆን ቦልተን ከፍተኛ የደኅንነት አማካሪያቸው ነበሩ። ድንገት ሥራ ለቀቁ። ዶናልድ ትራምፕ "እሱ ሥራውን ለቆ እንዳይመስላችሁ፤ እኔ አባርሬው ነው" አሉ።
እኚህ የቀድሞው የዶናልድር ትራምፕ ከፍተኛ የደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ከሰሞኑ "ዌር ኢት ሃፕንድ" የተሰኘ መጽሐፍ ጽፈዋል።
ከማተሚያ ቤት ግን አልወጣም መጽሐፉ። ለሕዝብ እንዳይሰራጭ ክስ ተከፍቶበታል።
መጽሐፉ ዶናልድ ትራምፕ በብዙ አገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ከአገር መሪ የማይጠበቅ የግንዛቤ ከፍተት እንዳለባቸው ያጋልጣል እየተባለ ነው።
ተቺዎች ስለምን ትራምፕ በተከሰሱበት ወቅት መጥቶ አልመሰከረም ሲሉ ደራሲውን ጆን ቦልተንን ይጠይቃሉ።
ዶናልድ ትራምፕ ያን ጊዜ ጆን ቦልተንን "ጅላ ጅል ሽማግሌ" እንዲሁም "ብቃት የሌለው" ሲሉ ወርፈዋቸው ነበር።
ለማንኛውም ዋይት ሐውስ መጽሐፉ ወደ ሕዝብ እንዳይሰራጭ በተቻለው እየደከመ ቢሆንም ትልልቅ ሚዲያዎች ግን የመጽሐፉ ቅጂ እጃቸው ሳይገባ አልቀረም።
የአሜሪካ ሚዲያ ከመጽሐፉ ውስጥ 6 ዋና ዋና ጉዳዮች ያሏዋቸውን እንዲህ አስቀምጠዋል።
1.ትራምፕ በድጋሚ ለመመረጥ ቻይናን "ተባበሪኝ" ብለዋት ነበር
ቦልተን በመጽሐፋቸው ውስጥ ትራምፕና የቻይናው አቻቸው ሺ ዢን ፒንግ በጂ-20 የበለጸጉ አገሮች ስብሰባ ላይ መገናኘታቸውን ያወሱና በዚያ ስብሰባ ላይ ትራምፕ ሺን እኔ እንድመረጥ እርዳኝ እንዳሏቸው ያወሳሉ።
ትብብሩ ደግሞ የአሜሪካ ገበሬዎች የሚያመርቱትን ሶያ አተር እና ስንዴ ቻይና በብዛት ብትገዛ የአሜሪካ ገበሬዎች ትራምፕን እንደሚመርጠተ በማስረዳት ነበር።
2.ቻይና ሙስሊሞችን የምታግትበን ማጎርያ ትራምፕ አሞካሽተዋል
ቻይና በሺንጃንግ ክልል ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሙስሊሞችን ማጎርያ ካምፕ ውስጥ እያስገባች የራሷን ርዕዮተ ዓለም ታጠምቃቸዋለች።
ባለፈው ረቡዕ ትራምፕ ይህ አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሰው የቻይና ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል።
ሆኖም ግን ቦልተን ባጋለጡት ምስጢር የቻይናው መሪ ገና ማጎርያውን ለመገንባት ሲያስቡ ስለዚህ እቅዳቸውና ስለ ግንባታው ጠቃሚነት ለዶናልድ ትራምፕ አማክረዋቸው ነበር። ትራምፕ በጣም አሪፍ ነገር ነው ብለው በጉዳዩ እንዲገፉበት አበረታቷቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
3.ዶናልድ ትራምፕ ከ2 ጊዜ በላይ መመረጥ ይፈልጋሉ
በአሜሪካ ሕገ መንግሥት አንድ ፕሬዝዳንት ከሁለት ጊዜ የሥልጣን ዘመን ቆይታ በኋላ መመረጥ አይችልም። ቦልተን በመጽሐፋቸው እንዳጋለጡት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ጋር በነበራቸው አንድ ስብሰባ የአሜሪካ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻልና እርሳቸው ከ2 ጊዜ የሥልጣን ዘመን በላይ እንዲያገለግሉ እንደሚፈልግ ነግረዋቸዋል። ይህ የአሜሪካዊያን ፍላጎት የእርሳቸውም ፍላጎት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
4.ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ኪንግደም የኑክሌየር ጦር መሣሪያ እንዳላት አያውቁም ነበር
ብሪታኒያ ከአሜሪካና ከሶቭየት ኅብረት ቀጥላ የአቶውሚክ መሣሪያን የሞከረች ሦስተኛዋ አገር እንደሆነች ይታወቃል። ይህም በ1952 እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ ግን ዩናይትድ ኪንግደም ኑክሌየር አላት ሲባሉ ተገርመው ነበር።
በ2018 አንድ ስብሰባ ከያኔዋ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ጋር ሳሉ አንድ ባለሥልጣን "የኑክሌር ኃይል ባለቤት ብሪታኒያን" ብሎ ሲጠቅስ ትራምፕ ቀበል አድርገው፣ "እንዴ! ምን ትቀልዳለህ! ብሪታኒያ ኑክሌየር አላት እንዴ?" ብለው ጠይቀዋል።
ቦልተን እንደሚሉት ዶናልድ ትራምፕ በወቅቱ እንደዚያ ያሉት ቀልድ ለመፍጠር አልነበረም፤ የምርም አያውቁ ኖሯል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
5.ፊንላንድ የራሺያ አካል ነበር የምትመስላቸው
ቦልተን ይህን ሲያስረዱ፣ በአንድ ወቅት የራሺያውን ፑቲንን በፊንላንድ ዋና ከተማ ሄልሲንኪ ከማግኘታቸው በፊት ዶናልድ ትራምፕ ፊንላንድ የራሺያ አካል ናት ወይስ ራሷን ችላ አገር ሆናለች ብለው ጠይቀዋቸዋል።
6.በትራምፕ የማያሾፍ የዋይት ሐውስ ሠራተኛ የለም
ቦልተን በመጽሐፋቸው ትራምፕ በገዛ ቤተመንግሥታቸው ውስጥ እንዴት ያሉ መቀለጃ እንደሆኑ ያስረዳሉ። ቦልተን ራሳቸው ሥራ ሲጀምሩ የያኔው የፕሬዝዳንት ቢሮው ኃላፊ ጆን ኬሊ እንዳስጠነቀቋቸው አስታወሰዋል። "የሥራ ቦታ እንዳይመስልህ፣ ሁሉም ነገር ቀልድ ነው፤ አንተም ታየዋለህ" ብለዋቸው ነበር።
በዶናልድ ትራምፕ ላይ ማሾፍ የተለመደ እንደሆነ ሲያብራሩ አሁን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፔዮ ሳይቀሩ የትራምፕ ወዳጅ ይምሰሉ እንጂ በአንድ ወቅት ፕሬዝዳንት ትራምፕን "ይሄ ደደብ ሰውዬ…" እንዳልዋቸው መስክረዋል።
ቦልተን ባልተሰራጨው መጽሐፋቸው ከዚህም በላይ በርካታ ያልተሰሙ ጉዳዮችን አጋልጠዋል ይላሉ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን።












