አሜሪካ "ቻይና የኢንተርኔት ምስጢሬን ልትመዘብር" ትችላለች አለች

የአሜሪካ ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካና ሆንግ ኮንግን የሚያገናኘው ከውቂያኖስ ስር የተዘረጋው የኢንተርኔት መስመር ከቻይና በኩል ለሚኖር የመረጃ ምዝበራ ያጋልጠኛል ስትል አሜሪካ ላትፈልገው እንደምትችል ተገለጸ።

የኢንተርኔት ሥርጭት ገመዶች የሚያልፉት በብዛት በውቅያኖስ ሥር ነው። አሜሪካና ሆንግኮንግን በኢንተርኔት የሚያገናኘው ገመድም በፓስፊክ በኩል ተዘርግቶ ነበር።

ይህ ረዥም ርቀት የተዘረጋው የኢንተርኔት ገመድ ሥራ እንዲጀምር ከአሜሪካ መንግሥት ፍቃድ ማግኘት ይኖርበታል።

አሜሪካ ከዚህ በኋላ ቻይና መረጃ ልትሰርቀኝ ስለምትችል በዚያ ውቅያኖስ ሥር የሚያልፍ የኢንተርኔት ገመድ ይቅርብኝ ብላለች።

ዘ ፓስፊክ ላይት ኬብል ኔትወርክ የተሰኘው ይህ የኢንተርኔት ገመድ ዝርጋታ በጉጉልና በፌስቡክ ኩባንያዎች ይደገፍ የነበረ ሲሆን የኢንተርኔት ፍጥነትን ከፍተኛ ለማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደነበር ታምኖበት ነው ወደ ሥራ የተገባው።

ሆኖም ቲም ቴሌኮም በሚል የሚጠራውና የአሜሪካ መንግሥት ያቋቋመው ልዩ ኮሚቴ ይህንን ከአሜሪካ ወደ ሆንግ ኮንግ የተዘረጋውን የኢንተርኔት ገመድ መስመር ሊያጸድቀው አልፈለገም።

ስጋቱ ደግሞ ቻይና በዚያ የሚያልፈው የኢንተርኔት መረጃን ትሰርቀናለች የሚል ነው።

ይህ ክስተት ቻይናና አሜሪካ እያደረጉት ያለው የንግድ ጦርነት በባሕር ውስጥም መቀጠሉን አመላካች ነው ተብሏል።

በባሕር ስር የሚያልፍ የኢንተርኔት ገመድ ለደኅንነት ስጋት ነው በሚል እንዲቀር ሲደረግ ይህ የአሜሪካ ውሳኔ በዓለም የመጀመርያው ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በባሕር ውስጥ የሚዘረጉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ገመዶች ኢንተርኔትን ያቀባብላሉ።

ይህ በፓስፊክ ውቅያኖስ ሊያልፍ የነበረው የኢንተርኔት የባሕር ውስጥ ገመድ በጉግል፣ በፌስቡክና በሌሎች ኩባንያዎች ሲደገፍ የነበረ ፕሮጀክት ነው። የተጀመረውም በየ2016 እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ነበር።

ጉጉል እንዳለው ዝርጋታው 12 ሺህ 800 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ነበር።

"በሌላ ቋንቋ ይህ መስመር ቢዘረጋ ለ80 ሚሊዮን ሆንግ ኮንጋዊያን በከፍተኛ ጥራት ከሎስ አንጀለስ አቻዎቻቸው ጋር የቪዲዮ ጥሪ በተመሳሳይ ሰዓት ማድረግ የሚያስችላቸው አቅም ይኖረው ነበር" ብሏል ጉግል።

ይህ መስመር ከአሜሪካና ከሆንግ ኮንግ ሌላ አሜሪካንን ከታይዋንና ከፊሊፒንስ የሚያገናኝም ተቀጽላ ገመድ ነበረው ተብሏል።

የውስጥ ለውስጥ ገመድ ዝርጋታው ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች የፈሰሰበት እንደነበር ተዘግቧል።