"ጥቁረቴን ለማስለቀቅ ስል ቆዳዬን እፈገፍገው ነበር"

የፎቶው ባለመብት, Karishma Leckraz/Anusha/Sabrina Manku
ሴቶች ቆንጆ ብቻ እንዲሆኑ ብቻ በሚጠበቅባት ዓለም ውብ ሆኖ ለመገኘት የማይከፈል መስዋዕትነት የለም። ውበት ወይም ቁንጅና ምንድን ነው? ማኅበረሰቡ የፈጠረው አይደለም ወይ የሚለውን መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብን ስናጤነው ውበት የሞትና ሽረት ጉዳይ ለምን ሆነ? የሚለው ጥያቄ ግራ ያጋባል።
በጥንታዊት ቻይና ሴቶች እግር ትንሽ መሆን አንድ የውበት መገለጫ በመሆኑ እግራቸው እንዲታጠፍና እንዲሰበርም ይገደዱ ነበር።
በዓመታት ውስጥ ማኅበረሰቡ በቻይና እንደሚደረገው እጅና እግር ተጠፍሮ እግር ባይሰበርም ባለንበት ዓለም ማስታወቂያዎች፣ ፊልሞች፣ ሙዚቃዎች በተለያ መንገድ ተፅእኖን ያሳርፋሉ።
የጎን አጥንትን ከማስወጣት ጀምሮ፣ ከንፈር፣ ጡትና የተለያየ የአካል ክፍልን ለማስተካከል ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው።
የቁንጅና እሳቤ ኢ-ፍትሃዊ ከሆነው አባታዊ ሥርዓት ጋር ብቻ ሳይሆን ከዘረኝነትም ጋር በፅኑ የተቆራኘ እንደሆነ ተችዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
ከዚህም ውስጥ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚፈስበት ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሆነው የቆዳ ማንጫ ምርቶች ይገኙበታል። ነጭ የቆዳ ቀለም የበላይ ነው በሚል እሳቤም በርካቶች ቆዳቸውን ለማንጣት ፊታቸውን ለጉዳት የሚያጋልጥ ቅባቶችን ይጠቀማሉ።
በማንኛውም መንገድ ፊትን ለማንጣትም የሚታገሉ በርካቶች ናቸው።
"በየቀኑ ገላዬን ስታጠብ የመጀመሪያ ሥራዬ ጥቁረቴ እንዲለቅ በሚል ቆዳዬን መፈግፈግ ነበር" ትላለች ካሪሽማ ሌክራዝ።
ማኅበረሰቡ ቆንጆ ነሽ የሚለውን እንዲያጎናጽፋትም ብዙ መስዋዕትነት ከፍላለች። ቆዳዋን ከመፈግፈግ ጀምሮ ቆዳ ሊያነጡ የሚችሉ ቅባቶችንም መጠቀም የጀመረችው ገና በ13 ዓመቷ ነው።
"ነጭ የቆዳ ቀለም ቢኖረኝ ቆንጆ እንደምሆን ይሰማኝ ነበር" ትላለች።
"ብዙዎች ልቅም ያልኩ ቆንጆ እንደሆንኩ ይነግሩኛል። ነገር ግን በአሳፋሪ ሁኔታ ቆዳዬ ጥቁር ነው" ትላለች የ27 ዓመቷ ካሪሽማ ከቢቢሲ ሬድዮ ዋን ኒውስ ቢት ጋር ባደረገችው ቆይታ።

የፎቶው ባለመብት, Karishma Leckraz
የቆዳ ቀለሟ እንዲነጣ ቅባት ያስጀመሯትም ቤተሰቦቿ ናቸው። የመጥቆሯ ነገር በቤተሰቦቿ ዘንድም ተቀባይነት ስላልነበረው እንድትነጣ ወይም ፈካ ብላ እንድትታይ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።
"በባህላችን ዘንድ ስር የሰደደ ጉዳይ ነው። አንድ ሰው ቆንጆ የሚባለው ነጭ የቀለም ቆዳ ሲኖረው ነው" ትላለች።
ካሪሽማ ባህሌ የምትለው ነጭ የቆዳ ቀለም ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠውን የደቡብ እስያን እይታ ነው።
ከቆዳ ቀለም ማንጣት ጋር ተያይዞ ስሙ የሚጠራው 'ፌር ኤንድ ላቭሊ' አምራቹ ዩኒሊቨር ነው።
በነጭ ፖሊስ በግፍ የተገደለውን የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ በተፈጠረው ተቃውሞና የዘር ውይይት ግዙፉ የውበት እቃዎች አምራች ዩኒሊቨር ስምና የማስታወቂያ ሃሳቡን እንዲቀይር ተገዷል።
ኩባንያው "ነጣና ፈካ" ያለ ቆዳ የሚለውን አባባል በእስያና በአፍሪካ ገበያዎች ላይጠቀም ቃል ገብቷል።
ጋብቻ ፈላጊ ጥንዶችን የሚያገናኘው ሻዲ የተባለው በእስያ ተቀማጭነቱን ያደረገ ድረገፅም እንዲሁ "የቆዳ ማፍኪያ" የሚለውን አገላለጹን አስወግዷል።
"ፀሐይ ላይ ብዙ አትቀመጪ"
እንደ ካሪሽማ ሳብሪና ማንኩም ስለ ጥቁረቷ አሉታዊ ነገሮችን ከቤተሰቦቿ አንደበት በተደጋጋሚ ስትሰማ ነው ያደገችው።
"ህፃን ሆኜ የበለጠ እንዳትጠቁሪ ፀሐይ ላይ አትቀመጪ እባል ነበር" የምትለው የ23 ዓመቷ ሳብሪና፤ አገላለጹ በተለይም በፑንጃቢ ቋንቋ ሲሆን ደግሞ የበለጠ ጨለምተኛ ትርጉም እንዳለውና "መንፈስንም ስብርብር" የሚያደርግ እንደሆነ ገልፃለች።

የፎቶው ባለመብት, Sabrina Manku
ቆዳዋን ፈካ የሚያደርግ ቅባትንም እንድትጠቀም ያደረጓት ገና የአስር ዓመት ታዳጊ እያለች ሲሆን ለስምንት ሰዓታት ያህል ያለማቋረጥ ተጠቅማዋለች።
የቤተሰብ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ ስለቆዳ ቀለም ያለው አመለካከት ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚፈጥርም ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ላላቸው ህንዳውያን ፈታኝ መሆኑንም ይናገራሉ።
ለአኑሻ ትምህርት ቤት እያለች አቻዎቿ በቆዳ ቀለሟ ላይ ይሰጡት የነበረው አስተያት ስሜቷን እንደጎዳውና ለራሷ ያላትን እይታ በዓመታት ውስጥ እንዳሽቆለቆለው ትናገራለች።
"አብዛኛውን ጊዜ ቀላ ካለ የቆዳ ቀለም ካላቸው ሰዎች ጋር የማይሆን አይነት ውድድር እገባ ነበር" የምትለው አኑሻ "ትምህርት ቤት ውስጥ ታዋቂ የሆኑትም ሆነ የተሻለ ቦታ የሚሰጣቸው የተለየ ምክንያት ኖሮ ሳይሆን በቆዳ ቀለማቸው ነበር። ነጣ ያሉት ከፍ ያለ ስፍራን ይይዛሉ" ትላለች።
ይህም ሁኔታ ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳደረባት አኑሻ ከአቻዎቿ ጋር ፎቶ መነሳትን እርም ብላ አቆመች። ራሷንም በተወሰነ መልኩ መጥላት ጀመረች።
"በፎቶው ላይ እኔ ጠቁሬ መታየት አልፈለግኩም" በማለት የተሰማትን ስሜት ትገልጸለች።
የቆዳ ቀለም የእርከን ደረጃ በደቡብ እስያ
የቆዳ ቀለም የእርከን ደረጃ (ከለሪዝም) በተመሳሳይ ሕዝብ (ማኅበረሰብ) ውስጥ የቆዳ ቀለምን መሰረት በማድረግ የሚመድብ የጭቆና መንገድ ነው።
ቆዳን ቀለም መሰረት ያደረገ የበላይነት ከቅኝ ግዛት ጋር በፅኑ የተቆራኘ እንደሆነም አጥኚዎች ይናገራሉ "ቆዳቸው ነጭ የሆኑት እንግሊዛውያን ህንድን በቅኝ ግዛት ገዝተዋታል" የሚሉት የሰብዓዊ መብትና ህግ አጥኚዋ እንዲሁም በደቡብ እስያ ያለውን መድልዎ ያጠኑት ዶ/ር ሪቱሙብራ ማኑቬ ናቸው።
"ይህም ሁኔታ ቆዳው ፈካ ወይም ነጣ ያለ ማኅበረሰብ የበላይ ነው የሚለው ስሜት እንዲሰፍን መሰረት ጥሏል" ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ በህንድ የሰፈነው ሕዝብን በደረጃ የመመደብ ሥርዓት እንዲሁ ቆዳቸው ነጣ ያለ ሰዎች በማኅበረሰቡ የተሻለ ቦታ እንዲሰጣቸው አድርጓል።
ቆዳቸው ጥቁር የሆኑ ሰዎች በመደቡ የመጨረሻ ስፍራን የያዙ ሲሆን እነሱን መንካትም እንደ አስነዋሪና አስጠያፊ ሁኔታ ይታያል።
"በህንድ ባለው የማኅበረሰብ ግንኙነት መዋቅር ከፍተኛ ስፍራ ያላቸው የቆዳ ቀለማቸው ነጣ ያሉ ናቸው። በጋብቻ ውስጥ ራሱ አስፈላጊ ከሚባሉ መስፈርቶች አንዱ የሙሽሪት የቆዳ ቀለሟ ነጣ ማለት ነው" በማለት ያለውን ያስረዳሉ።
በተለይም የቆዳ ማፍኪያ (ማንጫ) ቅባቶች በገበያው ላይ መግነንም የቆዳ ቀለም መንጣት በአሁኗ ህንድ ተቋማዊ በሆነ መልኩ ተቀባይ እንዲኖረው አድርጓል። ባለው ባህልም ነጣ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎችን ከፍተኛ ስፍራ እንዲሰጣቸው አድርጓቸዋል።
"በጥንት ጊዜ የነበሩ ተቋማትን ብናይ ለምሳሌ የነፃነት ታጋዮች የቆዳ ቀለማቸው ምንም ስፍራ የሚሰጠው አልነበረም" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Sabrina Manku
"ታዋቂ ሰዎችን አርአያ አደረግኩ"
ለሳብሪና የቆዳ ቀለም ማንጣት ከቤተሰቦቿና በተጨማሪ ውሳኔዋ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳረፈባት የህንድ ፊልም ኢንዱስትሪን የሚመሩት የቦሊውድ ተዋናዮች እንደሆኑ ትናገራለች።
"ታዋቂ ተዋናዮች የሚያደርጓቸውን ሁሉ እከታተለሁ እናም እነሱ አርአያ ሆነውኛል" ትላለች።
የቦሊውድ ተዋናዮች የቆዳ ቀለምን የሚያነጡ ምርቶችን በማስተዋወቅም በከፍተኛ ሁኔታ የሚተቿቸው አሉ።
"የቆዳ ቀለማችን ጠቆር ላልነው እነዚህን ምርቶች መጠቀም ቆዳችንን ፈካ እንደሚያደርገውና ልዩነት እንደሚያመጣ እናምናለን። ምክንያቱም ታዋቂ ሰዎች ብለውታልና" በማለትም ታስረዳለች።
አንዳንዶችም ማስታወቂያዎች ላይ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላት ሴት ማንም ሳይፈልጋት ይቀርና እነዚህን የቆዳ ማንጫ ምርቶችን ስትጠቀም ወንዶች በውበቷ ሲሳቡም ያሳያሉ።
የቆዳ ቀለም ማንጣት ሁኔታ በማስታወቂያዎች ብቻ የተወሰነ አይደለም።
"በፊልሞችም ላይ እንዲሁ የቆዳቸው ቀለም ፈካ ያሉ ሰዎች የበለጠ ውብ ተደርገው ይሳላሉ። እኔም በቴሌቪዥን የማያቸውን ሰዎች የበለጠ መምሰል ፈለግኩ" በማለትም ሳብሪና ታስረዳለች።
"አሁንም የቆዳ ማንጫ ቅባት እጠቀማለሁ"
ካሪሽማና ሳብሪና የቆዳ ማንጫ ምርቶች ካላቸው የጎንዮሽ ጉዳት ጋር በተያያዘና በዓመታት ውስጥም ጥቁር የቆዳ ቀለማቸውን በፀጋ በመቀበላቸው ምርቶቹን መጠቀም አቁመዋል።
የአኑሻ ጉዞ ግን የተለየ ነው።
በዓመታት ውስጥ ቤተሰቧና ማኅበረሰቡ የቆዳ ማንጫ ምርቶችን እንድትጠቀም ከፍተኛ ተፅእኖ ቢያሳርፉባትም በአሁኑ ሰዓት ግን እነዚህን ምርቶች ለመጠቀሟ ምክንያቷ ሌላ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Anusha
"የቆዳ ማንጫ ምርቶችን የሚጠቀም ሰው ሁሉ በቋሚነት ቆዳው እንዲነጣ ይፈልጋል ማለት አይደለም። ምርቶቹ ቆዳን መገርጣትን በማስቀረት የታደሰ ፊት ይሰጣሉ" ትላለች።
አኑሻ ሜካፕ ለመጠቀምም እነዚህ ምርቶች አመቺ መሆናቸውንም ታስረዳለች።
ሆኖም በህፃንነቷ እነዚህን ምርቶች እንድትጠቀም ባትደረግ ኖሮ ባሁኑ ወቅት ዘወር ብላ ልታያቸው እንደማትችል አልደበቀችም።
ቤተሰቧም ሆነ ማኅበረሰቡ ያሳደረባት ተፅእኖ እንዲህ በቀላሉ ትቷት የሚሄድ አልሆነም።
በቅርብ ጊዜያት የቆዳን ቀለም መሰረት ያደረገ የማኅበረሰብ የደረጃ አመዳደብም ሆነ እነዚህን ምርቶች በተመለከተ ውይይቶች መኖራቸውን ካሪሽማ ትናገራለች።
"ከቤተሶቦችም ጋር ግልፅና ተገቢ በሆነ መንገድ መነጋገር ጀምረናል" ትላለች።
በመላው ዓለም "ፌይር ኤንድ ላቭሊ" በሚለው ምርቱ ታዋቂ የሆነው ዩኒሊቨርም ሆነ ሎሬል ስምና የማስታወቂያ ሃሳባቸውን ቢቀይሩም ለሳብሪና ይህ በቂ አይደለም።
"የምርቶቹን ስም መቀየር ምርቶቹን ከገበያ አያጠፋቸውም። የቆዳ ማንጫ ምርቶቹ ገበያ ላይ እንዳሉ እናውቃለን። ምርቶቹ ናቸው መወገድ ያለባቸው" ትላለች።
ካሪሽማ በበኩሏ "ወደ ልጅነቴ መመለስ ብችል፤ ለህፃኗ እኔ እንዲህ አይነት የቆዳ ማንጫ ምርቶችን አትጠቀሚ፤ አቁሚ እላት ነበርም" ብላለች።
"የቆዳሽ ቀለም ውበት ነው እላት ነበር። ጥቁረትሽ ሜላኒን የተሰኘው ንጥረ ነገር ማሳያ እንደሆነም አስረዳት ነበር" በማለት አጠቃልላች።












