የአልጀሪያዋ ቁንጅና አሸናፊዋ ከድጃ ቤን ሃሙ ዘረኝነት እንደማይበግራት ገለፀች

የፎቶው ባለመብት, Miss Algerie
በቅርቡ የአልጀሪያን የቁንጅና ንግስትነት የተቀዳጀችው ከድጃ ቤን ሀሙ በቆዳዋ ቀለም ምክንያት እየደረሰባት ያለው ዘረኝነት እንደማይበግራት ተናገረች።
"በሚተቹኝ ሰዎች ምክንያት ወደ ኋላ አልልም፤ አይበግረኝም" በማለት ከድጃ ቤን ሀሙ ለአልጀሪያው ዜና ወኪል ቲኤስኤ ተናግራለች።
በፌስቡክና ትዊተር በመሳሰሉ ማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ጠቆር ስላለው ቆዳ ቀለሟ፣ አፍንጫዋና ከንፈሯ የተለያዩ ስድቦችንና ፌዞችንም እያስተናገደች ነው።
በሰሜናዊቷ አፍሪካዊቷ ሃገር አልጀሪያ ቆዳቸው ትንሽ ጠቆር ያሉ ሰዎች ዘረኝነትና መድልዎ ይደርስባቸዋል።
አልጀሪያን ጨምሮ በተለያዩ የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ውበት ከቆዳ ቀለም መቅላት (መንጣት) ጋር በከፍተኛ ሁኔታ ይያዛል።
ከደቡባዊ አድራር አካባቢ የመጣችው ከድጃም በበኩሏ በማንነቷ እንዲሁም ውድድሩን በማሸነፏ እንደምትኮራ ተናግራለች።
"ህልሜን በማሳካቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ በመጣሁበት ግዛት አድራርም ተከብሬያለሁ" ያለችው የቁንጅና ውድድር አሸናፊዋ አክላም " እኔ ከመጣሁበት አካባቢ ያሉ ሴቶችም መወዳደር ከፈለጉ እንዲሳተፉ አበረታቸዋለሁ" ብላለች።
የፋሽን መፅሄቱ ቮግ እንደዘገበው በአውሮፓውያኑ 2005 ካሸነፈችው ናሲማ ሞካዴም በኋላ ከድጃ ስታሸንፍ ሁለተኛዋ ጥቁር ሴት ናት።
ከድጃ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በተካሄደው ቁንጅና ውድድር ከማሸነፏ በፊት 20 ዙሮችን አልፋለች።
የሚተቿት ግለሰቦች አልጀሪያን አትወክልም በማለት ሲሆን ነገር ግን በማህበራዊ ሚዲያ ብዙዎች ድጋፋቸውን አሳይተዋል። ከድጃም በበኩሏ "ሰዎች ሳያውቁ ዳኝነት መስጠት ተገቢ አይደለም። በጥቁርና በነጭ መካከል ልዩነት የለም" ብላለች።
የቁንጅና ውድድሩ አዘጋጆች በበኩላቸው ዘረኝነት የተሞላው የግለሰቦች አስተያያት አፀያፊ እንደሆነ ተናግረዋል።












