ግዙፉ የቆዳ ቅባት አምራች ዩኒሊቨር ‹‹ጥቁር ቆዳዎ ፈካ እንዲልልዎ..!››የሚለው ማስታወቂያው ተቃውሞ ገጠመው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግዙፉ የውበት እቃዎች አምራች ዩኒሊቨር በመላው ዓለም ተወዳጅ የሆኑለትን ‹‹ፌይር ኤንድ ላቭሊ›› ስምና የማስታወቂያ ሐሳብ ሊቀይር እንደሆነ ይፋ አድርጓል።
የምርቱን ስም ለመቀየር የተገደደው በደረሰበት ተቃውሞ ነው፡፡
ኩባንያው ከምርቱ ስም ጀምሮ ‹‹ፌይር ኤንድ ላቭሊ››የተሰኙ ምርቶቹ ላይ ‹‹ቆዳዎ ፈካ እንዲልልዎ…›› የሚለው አባባል ዘረኝነት ነው በሚል ተቃውሞ ቀርቦበለታል፡፡
‹‹ማስታወቂያው ውስጠ-ወይራ ነው፡፡ ጥቁር ቆዳ አስቀያሚ፣ ነጣ ያለ ቆዳ ደግሞ የውበት አክሊል ተደርጎ እንዲታሰብ የሚያበረታታ ነው›› በሚል ነው ቀይር የተባለው፡፡
በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የፈረሙበት የተቃውሞ ሰነድ የደረሰው ይህ ግዙፍ ኩባንያ ተወዳጅ የሆኑለትንና ሰፊ ገበያ የነበራቸውን የፌይር ኤንድ ላቭሊ ምርቶቹን ስም ለማስተካከል ቃል ገብቷል፡፡
ከምርቶቹ ስም ባሻገር ‹‹ነጣና ፈካ ያለ ቆዳ›› የሚለውን አባባል በኢሲያና በአፍሪካ ገበያዎች ላይጠቀም ቃል ገብቷል፡፡
‹‹እውነት ነው፣ ማስታወቂያዬ ዉበት ፈካ ያለ ቆዳ ብቻ እንደሆነ የሚያመላክት መንፈስ አለው፤ ስለዚህ እቀይራለሁ›› ብሏል፡፡
ኩባንያውን ይህን እርምጃ እንዲወስድ 18ሺህ ሰዎች የተቃውሞ ፊርማ አኑረዋል፡፡
ከተቃዋሚዎች አንዷ ለሚዲያ እንደተናገረችው ‹‹ይህ ኩባንያ በዘረኝነት ውስጥ ገንዘብ ሲያጋብስ ነው የኖረው፤ ጥቁር ቀለምን ሲያንኳስስ ነው የኖረው፣ ዉበት ቅላት ብቻ እንደሆነ ውስጥ ውስጡን ሲሰብከን ነው የኖረው›› ብላለች፡፡
ሌላ ተቃዋሚ ደግሞ ‹‹ድርጅቱ ጥቁር በመሆናችን ውብ ለመሆን እንደማንመጥን ነበር ለዘመናት የሚነግረን›› ብላለች፡፡
የዩኒሊቨር ፕሬዝዳንት ሰኒ ጄን ከዚህ በኋላ ምርቶቻችን ሁሉንም የቆዳ ቀለም ያማከሉና አካታች እንዲሆኑ እንጥራለን፤ የቆዳ ቀለም ብዝኃነትን እናደንቃለን ብለዋል፡፡
ዕውቋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የመብት ታጋይ ፑርና ቤል ታዲያ ይህ የኩባንያው ምላሽ አስቆጥቷታል፡፡
ፑርና ዩኒሊቨር በይቅርታ ብቻ ነገሩን አድበስብሶ ማለፉ የሚያንገበግብ ነው ብላለች፡፡
እንደርሷ አመለካከት ኩባንያው ያጋበሰው ትርፍ ከዘረኝነት የተገኘ በመሆኑ ካሳ መክፈል ይኖርበታል፡፡ ምርቶቹም ከእንግዲህ በጭራሽ ወደ ገበያ መውጣት የለባቸውም፡፡
‹‹ኩባንያው በዘመናት ያደረሰው ጉዳት ቁሳዊ አይደለም፡፡ የሚሊዮን ጥቁሮችን ስሜት ጎድቶታል፤ ይቅርታ ብቻ ብሎ ማለፉ ያንገበግበኛል›› ብላለች ፑርና ቤል፡፡
የጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ የግፍ መገደልን ተከትሎ በተቀጣጠለ የጸረ ዘረኝነት ተቃውሞ በርካታ ግዙፍ ኩባንያዎች ለነበራቸው መጥፎ የረዘኝነት ታሪክ ሳይቀር ይቅርታ እየጠየቁ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ሁለት የእንግሊዝ ግዙፍ ኩባንያዎች ከባሪያ ንግድ ጋር በተሳሰረ መጥፎ ታሪካቸው ጥቁሮችን ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ባለፈው ሳምንት ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሥመ ጥር ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው ኢትን ኮሌጅ የመጀመርያውን የትምህርት ቤቱን ጥቁር ተመራቂ ናይጄሪያዊ ደራሲ ላይ ላደረሰው ስውር የዘር ጥቃት በይፋ ይቀርታ መጠየቁ አይዘነጋም፡፡


















