አጋርዎ ከዚህ በፊት ጥቃት ፈፅሞ እንደሆነ የሚያሳየው መዝገብ

ባቻይና በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃትን የሚመለከት ሕግ የወጣው ከአራት ዓመት በፊት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ባቻይና በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃትን የሚመለከት ሕግ የወጣው ከአራት ዓመት በፊት

ምሥራቅ ቻይና ውስጥ የምትገኝ አንዲት ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ ትዳር ከመመሥረትዎ በፊት ወደ አንድ መስኮት ብቅ ብለው አንድ ጥያቄ መጠይቅ ይኖርብዎታል።

ወደ ትዳር አብሬው ወይ አብሬያት የምገባው ግለሰብ ከዚህ በፊት ጥቃት ፈፅሞ ያውቅ ይሆን? የሚለውን ለመጠየቅ።

ይዉ የተሰኘችው ከተማ ከትዳር በፊት የአጋራቸውን ባሕሪ በውል ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች አንድ መስኮት አዘጋጅታለች። መስኮቱ ከሚቀጥለው የአውሮፓውያኑ ወርሃ ሐምሌ ጀምሮ ለተጠቃሚዎች ክፍት ይሆናል።

'ዘ ፔፐር' የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው የትዳር ዓለምን መቀላቀል የሚሹ ጥንዶች አንድ ቅፅ ይሰጣቸውና ይሞላሉ። ይህን ቅፅ ተከትሎ አጋራቸው ከዚህ በፊት ሌላ ሰው ላይ ጥቃት ፈፅሞ እንደሆነ ያሳያል። ጥቃቱ የተፈፀመው ቤተሰብ ላይም ሆነ የፍቅር ጓደኛ ላይ፤ ይፋ ይሆናል ተብሏል።

ጥንዶች የእጮኛቸውን የኋላ ታሪክ ማወቅ ከፈለጉ የአጋራቸውን መታወቂያ ቁጥር እና ግላዊ መረጃዎች ማቅረብ ብቻ ነው የሚጠብቅባቸው።

አንድ ሰው በዓመት ሁለት ጊዜ የአጋሩን የኋላ ታሪክ ማወቅ ይችላል።

የከተማዋ የሴቶች ፌዴሬሽን አባል የሆኑት ዡ ዳንይንግ እርምጃው እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ። ይህ ሥርዓት መዘርጋቱ የቤት ውስጥ ጥቃት ለሚደርስባቸው ሰዎች ጥሩ መፍትሄ ነው ይላሉ።

ለጋዜጣው አስተያየታቸውን የሰጡት ዡ የቤት ውስጥ ጥቃት የሚመዘገብበት ማሕደር ከፍርድ ቤቶችና ኬሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተገኙ መረጃዎቸን ይጠቀማል ይላሉ።

ማሕደሩ ላይ የሚገኘው የጥቃት አድራሾች የኋላ ታሪክ ከ2017 ጀምሮ የተሰበሰበ ነው።

የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ሃን ጂን ሰዎች ማንን እንደሚያገቡ ማወቅ አለባቸው፤ ይህ ደግሞ ግላዊ መብታቸው ነው ይላሉ።

ቻይናውያን የሕጉን መፅደቅ ተከትሎ በማኅበራዊ የመገናኛ መድረኮች ላይ አድናቆታቸውን እየገለፁ ነው። በቻይናውያን ዘንድ ታዋቂ በሆነው ዌቦ በርካታ ቻይናውያን ሕጉ ወደ ሌሎችም ከተማዎች እንዲስፋፋ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የሚያጋልጥ ሌላ መስኮት መከፈት አለበት የሚሉም በርካቶች ናቸው።

ቻይናውያን የቤት ውስጥ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎች ለሕግ ይቅረቡ ሲሉ መወትወት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

ከ2001(እአአ) በፊት ቻይና ውስጥ አካላዊ ጥቃት ለፍቺ ምክንያት አይሆንም ነበር። የቤት ውስጥ ጥቃትን ወንጀል ያደረጉ ሕጎች የፀደቁት ደግሞ መጋቢት 2016 ላይ ነበር።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ መከልከላቸው ለቤት ውስጥ መበራከት ምክንያት ሆኗል እየተባለ ይነገራል። ቻይና ውስጥም በዚህ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የቤት ውስጥ ጥቃት በእጥፍ መጨመሩን ከፖሊስ የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ባለፈው ወር ቻይና ባለትዳሮች ከመፋታታቸው በፊት 30 ቀናት ወስደው እንዲያስቡበት የሚል ሕግ ማርቋን ተከትሎ ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉ ሰዎች ለፍቺ ለማመልከት ይከብዳቸዋል የሚል ፍራቻ አለ።

የ30 ቀናት የማሰቢያ ጊዜ የሚጠይቀው ሕግ ከ2021 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ይህ ሕግ አይመለከታቸውም ተብሏል።