ሕጻናትን በኢንስታግራም ሊሸጡ የነበሩ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሁለት ሕጻናትን በኢንስታግራም ለመሸጥ ሲያግባቡ የነበሩ ሦስት ሰዎች ኢራን ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የቴህራን ፖሊስ ሹም ብርጋዲየር ጄኔራል ሁሴን ራሂሚ እንደተናገሩት ከሕጻናቱ አንዱ ገና ከተወለደ 20 ቀን አልሞላውም። ሌላኛዋ ልጅ 2 ወሯ ነበር።
ሕጻናቱን ሊሸጡ የነበሩት ሰዎች ልጆቹን በ500 ዶላር ገዝተዋቸው በኢንስታግራም በኩል በ2 ሺህ ዶላር ሊሸጧቸው ሲሉ ነው የተያዙት።
ከአንድ ሕጻን ከ1 ሺህ 500 እስከ 2ሺ ዶላር ለማትረፍ አስበው ነበር ተብሏል እነዚህ ግለሰቦች።
በቁጥጥር ከዋሉት ውስጥ አንዱ የሕጻናት ነጋዴ እንደተናገረው ልጆቹን ያገኛቸው እጅግ ድሀ ከሆኑ ቤተሰቦች ነበር። እየሸጧቸው የነበረውም የተሻለ ኑሮ ሊያኖራቸው ለሚችል የተደላደለ ቤተሰብ ነው።
ብርጋዲየር ጄኔራል ራሂሚ ለኢራን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ሕጻናቱ ለገበያ ስለመቅረባቸው በኢንስታግራም ማስታወቂው መውጣቱን በሰሙ ጊዜ ክትትል ጀምረዋል።
ራሂሚ እንዳሉት ወደ 15 ገጽ ከሚሆን የሽያጭ ስምምነት ወረቀት ውስጥ የእምቦቀቅሎቹን ፎቶግራፍና የደላሎቹን ምሥል ማግኘታቸውን፣ ከዚያም ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
አሁን ጨቅላዎቹ ለሕጻናት ተንከባካቢ ድርጅት ተሰጥተዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው እኛ ሕጻናቱ የተሻለ ሕይወት እንዲያገኙ በሚል ያደረግነው ነው ብለው ድርጊታቸውን ቅዱስ ተግባር አድርገው ተከራክረዋል።
በኢራን እንዲህ ዓይነቱ ዜና ሲሰማ ይህ የመጀመርያ አይደለም።
በዚህ ዓመት መባቻ ለምሳሌ ጎርጋን በሚባል አውራጃ አራት ሴቶችና አንድ ወንድ በድህነት ውስጥ ያሉ እርጉዞችንና አራሶችን እያፈላለጉ ልጅ ለመግዛት ሲደራደሩ በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር።
በርካታ ኢራናዊያን በተለያዩ ምክንያቶች ልጅ ለመውለድ ያላቸው ፍላጎት በመቀነሱ ምክንያት በአገሪቱ አዲስ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር እያሽቆለቆለ መሆኑን መንግሥት አሳወቋል።
ይህም በሕዝብ ብዛቷ ላይ ተጽእኖን እያደረሰ በመሆኑ በመንግሥት የሕክምና ተቋማት ውስጥ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እንዳይሰጥ በቅርቡ አዟል።












