ኮሮናቫይረስ፡ ኢራን ከአሜሪካ ቀረበላትን የህክምና እርዳታ አልቀበልም አለች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
የኢራን ሐይማኖታዊ የበላይ መሪ አገራቸው የኮሮናቫይረስን ለመዋጋት ለምታደርገው ጥረት ከአሜሪካ የቀረበላትን እርዳታ የመስጠት ጥያቄ እንደማይቀበሉት አሳወቁ።
አያቶላህ አሊ ሃሚኒ በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር ላይ እንዳሉት አሜሪካ የኢራን "ከሁሉ የባሰች ጠላት" ናት በማለት ቀደም ሲል አሜሪካ ለወረርሽኙ መከሰት ተጠያቂ ናት ሲሉ አንዳንድ የቻይና ባለስልጣናት ያቀረቡትን የሴራ ትንተና ክስ ጠቀስ አድርገዋል።
"ይህ ክስ ምን ያህል እውነተኛ መሆኑን አላውቅም ነገር ግን እየተነገረ ነው፤ ታዲያ አእምሮው በትክክል የሚሰራ ሰው መድሃኒት ይሰጡኛል ብሎ እምነት ይጥልባቸዋል?" ሲሉ የጠየቁት ሃሚኒ "ስለዚህም የምትሰጡን መድሃኒት ቫይረሱን የበለጠ ለማስፋፋት የምትጠቀበት መንገድ ነው" ሲሉ አሜሪካንን ከሰዋል።
መሪው ጨምረውም ምንም ማስረጃ ሳያቀርቡ "የኮሮናቫይረስ የኢራናዊያንን የዘረመል መረጃ በተለያዩ መንገዶች በመውሰድ በተለየ ሁኔታ ለኢራን የተሰራ ነው" ሲሉ ጣታቸውን አሜሪካ ላይ ቀስረዋል።
ሌሎች የኢራን ባለስልጣናትም አሜሪካ በአገራቸው ላይ የተጣሉትን ከባድ ማዕቀቦች ለማንሳት ፈቃደኛ ሳትሆን በዚህ ጊዜ እርዳታ ልስጥ ማለቷን አስመሳይነት ሲሉ ወርፈዋታል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ኢራን ክፉኛ በበሽታው ከተጠቁት አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ አገራት መካከል 21,600 ሰዎች በበሽታው የተያዙባት ቀዳሚ አገር ሆናለች።
እስካሁንም በበሽታው ምክንያት የሞተዋል ተብለው በይፋ የተነገረ ኢራናዊያን አሃዝም 1,685 ደርሷል። ነገር ግን በበሽታው የተያዙና የሞቱ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ከተጠቀሰው ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።
በሽታውን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የፈረንሳይ ድንበር የለሽ ሐኪሞች የበጎ አድራጎት ቡድን ዛሬ ኢስፍሃን በምትባለው የኢራን ግዛት ውስጥ ባለ 50 አልጋ የድንገተኛ ህክምና ማዕከል አቋቁሟል።
ኢራን ከምዕራባዊያን ጋር እየተካረረ ባለ ፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ ባለችበት ሁኔታ ከብሪታኒያና ከጀርመን በተጨማሪ ፈረንሳይ የህክምና እርዳታ ድጋፍ እያበረከቱ ይገኛሉ።












