እውቁ ካሜራ ኦሊምፐስ ከ84 ዓመት በኋላ መመረት ቆመ

ኦሊምፐስ ካሜራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶግራፍ ምስሎችን በማንሳት ከሚታወቁ ምርጥ ካሜራዎች መካከል አንዱ የነበረው ኦሊምፐስ ካሜራ መመረት እንዳቆመ ኩባንያው አስታወቀ።

ኦሊምፐስ ልክ እንደ ኒከን፣ ሶኒና ካነን ሁሉ በመላው ዓለም እውቅ ካሜራ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል።

በዓለም ግዙፍ ከሚባሉ ካሜራ አምራቾችም አንዱ ነበር። ከ84 ዓመታት በኋላ የካሜራ ምርቱን የሚመለከተውን ክፍል ለጃፓኑ ኢንዱስትሪያል ፓርትነርስ መሸጡ ተሰምቷል።

ኩባንያው እንዳለው በዚህ ዘመን የካሜራ ቢዝነስ ምንም ሊያዋጣ አልቻለም።

ምክንያቱ ደግሞ ዘመናዊ ካሜራ የተገጠመላቸው ዘመናዊ ስልኮች ገበያውን ማጥለቅለቃቸው ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ምርት ላለማቆም በኪሳራ ሲንገታገት እንደነበረም ከኩባንያው ተገልጸዋል።

ይህ የጃፓን ኩባንያ የመጀመሪያውን ኦሊመፐስ ካሜራ ምርቱን ለገበያ ያቀረበው በ1936 እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ነበር።

ኩባንያው ከዚያ በኋላ ምርቱን እያሻሻለ አንድ ክፍለ ዘመን ሊያስቆጥር ጥቂት ዓመታት ሲቀሩት ነው በቃኝ ብሎ የካሜራ ምርቱን ለሌላ ድርጅት ያስተላለፈው።

"ለኦሊምፐስ ካሜራ በመላው ዓለም ልዩ ፍቅር አለ" ይላል የአማተር ፎቶግራፊ መጽሔት አርታኢ ኒጀል አተርተን።

በተለይ በ1970ዎቹ ኦሊመፐስ ካሜራ እነ ዴቪድ ቤይሌይ እና ሎርድ ሊችፊልድን በመሰሉ ዝነኛ ሰዎች ማስታወቂያ ይሰራለት ስለነበር በዓለም ደረጃ እውቅ ካሜራ ለመሆን አስችሎታል።

"በጊዜው በጣም ትንሽ፣ በጣም የሚያማምሩ፣ በጣም ብርሃን ያላቸውና አጓጊ ነበሩ" ይላል የፎቶግራፍ መጽሔት አርታኢው ኒጀል አተርተን።

የእጅ ካሜራዎች ገበያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በ84 ከመቶ ወድቋል።

ድርጅቱ የኦሊምፐስ ካሜራ ምርት ክፍሉን ለሌላ የጃፓን ኩባንያ ይሽጠው እንጂ ኦሊምፐስ እንደ ኮርፖሬሽን አልፈረሰም። ኦሊምፐስ ካሜራን የገዛው የጃፓን ኢንዱስትሪያል ፓርትነርስም ምርቱን መቼ እንደሚቀጥል ፍንጭ አልሰጠም።

ሆኖም ኦሊምፐስ ኮርፖሬሽን የዚህን ካሜራ ምርት ከ84 ዓመታት በኋላ ማምረት ቢያቆምም ሌሎች ሌንሶችን፣ ማይክሮስኮፖችንና ለሕክምና የሚያገለግሉ ኢንዶስኮፖችን ማምረቱን ይቀጥላል።

በኦሊምፐስ ካሜራ ምርት መቆምና ወደ ሌላ ኩባንያ መዛወር በርካታ የፎቶ ጥበብ ባለሞያዎች ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።