በቄለም ወለጋ ዞን አምፊሎ ወረዳ ሸበል ቀበሌ ነዋሪዎችን ምን አፈናቀላቸው?

ምዕራብ ኦሮሚያ

በቄለም ወላጋ ዞን አምፊሎ ወረዳ ሸበል ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ሰዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በጋምቤላ ክልል 03 የሚባለው አካባቢ መጠለላቸውን ለቢበሲ ተናግረዋል።

በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኘው የመኖሪያ አካባቢያቸው እንደተፈናቀሉ የሚናገሩት እነዚህ ነዋሪዎቹ አሁን ተመልሰው በተጠለሉበት ስፍራ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውንም ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት በቀበሌያቸው ሸበል፣ በተከሰተው ግጭት የተነሳ የአምስት ሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ ወደ ጋምቤላ ክልል እንደሸሹ የሚናገሩት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ነዋሪ "አሁን ደግሞ የመንግሥት ኃላፊዎች በጉልበት ወደ መኖሪያ ቀያችን መልሰውናል" ይላሉ።

የሁለት ልጆች አባት የሆነውና ሸራ ወጥሮ በጋምቤላ 03 እንዳለ የተናገረው ሌላ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ግለሰብ በበኩሉ አሁንም ቢሆን በፍርሃት እንደሚኖር ተናግሮ ወደ መኖሪያ አካባቢው የተመለሰው ያለው ሁኔታ ስለሚያሰጋው መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ቅዳሜ ጠዋት ሸበል ውስጥ ከፍተኛ ተኩስ ሰሲማ ደንግጠን ተበታተንን" ያሉት ወደ ቀያቸው ከተመለሱት መካከል አንዱ ናቸው።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መሸሽ መጀመራቸውን በመግለጽ "የመንግሥት ወታደሮች የሚሉት ተኩሱ የተከፈተው የሸኔ ታጣቂዎች ላይ ነው። እኛ ወደ ጫካ የሸሸነው ተኩሱን ሰምተን ነው" ነው ብለዋል።

ቡና ጫካችን ውስጥ ሆነን ስንሰማ በዚህ ተኩስ የተነሳ አምስት ሰዎች መሞታቸውን ሰምተናል በማለት የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

ይህንን ፈርተን በእግራችን ወደ ጋምቤላ አቅንተናል ያሉት ነዋሪው ችግሩ በተከሰተበት ዕለት ሁሉም ነዋሪዎች ደንግጠው መሸሻቸውን ይናገራሉ።

"ተኩስ ሲከፈት እየሞተ ያለው ሰላማዊ ሰው ነው" በማለት እያጋጠመ ነው ያሉትን ለቢቢሲ ገልጸዋል። "ስለዚህ በነጻነት መኖር ስላለቻልን ወደ ጋምቤላ ተሰድደናል" ሲሉም ያክላሉ።

በእግራችን ሰባት ሰዓት ተጉዘን ነው ጋምቤላ የገባነው የሚሉት እኚህ ግለሰብ ለሊቱን ተጉዞ በነጋታው ጋምቤላ 03 የሚባለው አካባቢ የደረሰ መኖሩንም ያስረዳሉ።

ጋምቤላ ያሉ ነዋሪዎችና የክልሉ መንግሥት ተቀብለዋቸው 03 የሚባል አካባቢ በማስፈር እንደረዷቸውም ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች ምግብ እያቀረቡላቸው እንደነበር የተናገሩት እኚህ ግለሰብ ከቀይ መስቀል እርዳታ እንዲያገኙም እንዳስተባበሩላቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ግለሰቡ እንደሚገልጹት በ03 አካባቢ ለስድስት ቀናት ከቆዩ በኋላ ከዞኑና ወረዳው የመጡ የመንግሥት ኃላፊዎች እንዳወያይዋቸው ይገልፃሉ።

"ችግራችንን ካስረዳን በኋላ እነርሱ ግን መመለስ አለባችሁ በማለት በስድስት መኪና 120 የሚሆን ሰው በመጫን ወደ ስፍራው መልሰውናል።"

ተመልሰውም ቢሆን ተመሳሳይ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን በመግለጽ፣ አንመለስም ያሉ እና ጋምቤላ ክልል ውስጥ የቀሩ መኖራቸውን አክለው ተናግረዋል።

ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሸሽተው ጋምቤላ ውስጥ ተጠልለው መቅረታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው ግለሰብ፤ እነዚህ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው የሚመጡ ባለስልጣናት እንዳያገኟቸው በመስጋት በሰዎች ቤት ሸሽተው እንዳሉ ይናገራሉ።

በጋምቤላ ለመቅረት የወሰኑት ለሕይወታቸው በመፍረታቸው መሆኑን የሚገልጹት ግለሰቡ አሁንም አዛውንቶች፣ ሴቶች፣ እናቶችና ሕጻናት በችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወደ ጋምቤላ የተሰደዱትን ሲረዱ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው የክልሉ የግብርና ሠራተኛ ተፈናቃዮቹ አሁን ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ይናገራል።

ተፈናቅለው የመጡ ሰዎችን የአካባቢው ባለስልጣናት መጥተው እንደሚወስዷቸው የሚያናገሩት እኚህ ግለሰብ 03 አካባቢ እንዲቆዩ አድርገን ገንዘብ፣ ምግብ፣ መጠለያ እንዲረዱ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ።

የመንግሥት አካላት ከወረዳና ከዞን ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በስፍራው በመገኘት እንዳወያይዋቸው የሚገልጹት እኚሁ የጋምቤላ ነዋሪ እንያዛለን በሚል ፍራቻ ያልተሳተፉ መኖራቸውን በመግለጽ የተሳተፉት ግን መመለሳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አሁን ጋምቤላ የቀሩት በየስፍራው ተበታትነው መሆኑን በመግለጽ ይህም ለመርዳት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ገልፀዋል።

ግለሰቦቹ ተበታትነው የሚገኙት የመንግሥት ኃላፊዎች መጥተው ይወስዱናል በሚል ፍራቻ መሆኑንም ጨምረው ያስራሉ።

የአንፊሎ ወረዳ ጸጥታ እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታሁን ሻምቢ በቀበሌው ችግር ተከስቶ እንደነበር አረጋግጠው፣ ወደ ጋምቤላ ተፈናቅለው የነበሩ በሙሉ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው መመለሳቸውንና ሕይወታቸውን መቀጠላቸውን ይናገራሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ አንድም በጋምቤላ የቀረ ተፈናቃይ የለም።

"ተጠልሎ ወደ ነበሩበት 03 አካባቢ ሄደን አነጋግረናቸው ወደ ቀያቸው መልሰናቸዋል" የሚሉት አቶ ጌታሁን ያፈናቀላቸው የሸኔ ወታደር መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ኃላፊው የተወሰደው እርምጃ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንጂ ሕዝቡን ለመጉዳት አይደለም በማለት "ተኩስ ነበር በተኩስ መካከል ሰዎች ይጎዳሉ ነገር ግን የሞቱ ሰዎች መኖራቸውንም ሆነ ምን ያህ ሰው እንደሞተ የምናውቀው ነገር የለም" ብለዋል።

ለኃላፊው ሕዝቡ ያለበትን የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት እንደወሰደ እርምጃ አንዳለ ተጠይቀው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።