በቻይና የቢሊየነሮች ዝርዝር ጃክ ማ 3ኛ ሆነ

ቻይናዊው ኮሊን ሁዋን

ቻይናዊው ኮሊን ሁዋን ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ተራ የጉግል መሥሪያ ቤት ሰራተኛ ነበር፡፡ ፒንዶዶ የሚባል የድረገጽ የገበያ ጉሊት ፈጠረና ከተራ ሰራተኝነት ወደ ሚሊየነርነት፣ ከሚሊየነርነት ወደ ቢሊየነርንት ተመነደገ፡፡

አሁን ኮሊን ሁዋን ሐብቱ 45.4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ብሏል የባለጸጎችን ምስጢር የሚያወጣው ፎርብስ መጽሔት፡፡

ይህ ማለት ኮሊን ሁዋን ከአሊባባው ጌታ ጃክ ማን በአንድ ደረጃ በልጧል ማለት ነው፡፡

በሌላ ቋንቋ ከቻይናዊው ቁጥር አንድ ቢሊየነር የቴንሳ ፈጣሪ ፖኒ ማ ሲሆን ቀጥሎ የፒንዶዶው ኮሊን ሁዋን ይከተልና ጃክ ማ ሦስተኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ሚስተር ሁዋን መጀመርያ በማይክሮሶፍት ተለማማጅ ሰራተኛ ሆኖ ነበር የገባው፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ጉጉል መስሪያ ቤት ገብቶ በመሐንዲስነት ሦስት ዓመት ቆየ፡፡

በ2016 የጦመረው አንድ ጽሑፍ ‹‹ እነዚያ በጉግል መስሪያ ቤት የቆየሁባቸው 3 ዓመታት እጅግ ወሳኝ ነበሩ›› ብሎ ነበር፡፡

ፎርብስ እንደሚለው የፒንዶዶ የድረ ገጽ ገበያ ተፈላጊነት ጣሪያ በመንካቱ ነው ሚስተር ሁዋን የአሊባባውን ጃክ ማንን ሊበልጠው የቻለው፡፡

ሚስተር ሁዋን ፒንዶዶን የፈጠረው በፈረንጆቹ በ2015 ነበር፡፡

ይህ የኮሮና ወረርሽኝ የዚህን የድረገጽ ኦንላይ ገበያ ድርሻ በከፍተኛ ሆኔታ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡

ምክንያቱም ቀድሞ በዚህ ገጽ በአንድ ቀን የነበረው ገበያ 50 ሚሊዮን አካባቢ ሲሆን አሁን ግን 65 ሚሊዮን አልፏል፡፡

ፒንዶዶ ከሌሎች የኦንላይን ጉሊቶች የሚለይበት አንዱ መንገድ ሰዎች እየተደራጁ ሰብሰብ ብለው አንድ እቃ መግዛት መቻላቸው ነው፡፡ ይህን ካደረጉ የዕቃው ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንስላቸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ደንበኞች በድረገጹ ጌም መጫወት ይችላሉ፤ የገበያ ኩፖንም ይሸለማሉ፤ በኩፖኑ ደግሞ የሚፈልጉትን እቃ እንዲገዙበት ያስችላቸዋል፡፡

አሁን ዓለምን እየመሩ ያሉ ቢሊየነሮች በብዛት ገቢያቸው ከኦንላይን ግብይት ጋር እየተሳሰረ መጥቷል፡፡

ፎርብስ ባወጣቸው የቅርብ ጊዜ መረጃዎች የዓለም ቁጥር አንዱ ባለጸጋ የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ ሲሆን ሐብቱ $162.2 ቢሊዮን ደርሶለታል።