ኮሮናቫይረስ፡ የሜዳ ቴኒሱ ኮከብ ሰርቢያዊው ጆኮቪች በኮቪድ-19 ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሰርቢያዊው የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ጆኮቪች 33 ዓመቱ ሲሆን በቤልግሬድ አንድ የቴኒስ ውድድር አሰናድቶ ነበር ሰሞኑን፡፡ ውድድሩ የተሰናዳው ሁለት ዓላማ አንግቦ ነበር፡፡
አንደኛው በደቡም ምሥራቅ አውሮጳ የሚገኙ ቴኒስ ተጫዋቾች ከውድድር ርቀው ስለነበር ለቀጣይ ውድድር እንዲዘጋጁ ለማድረግ ሲሆን ሁለተኛው የሚገኘው ገቢ ከኮሮና ጋር በተያያዘ የሚውል ለበጎ አድራጎት እንዲሰጥ ነበር፡፡
ይህ ውድድር ገና ከመጀመሩ ታዲያ አሳዛኝ ዜና አጋጥሞታል፡፡
ቢያንስ አራት የሚሆኑ ዕውቅ የቴኒስ ተጫዋቾች በኮሮና መያዛቸው ታውቋል፡፡ ከነዚህም መሐል ክሮሺያዊው ቦርና ኮሪክ እና ሰርቢያዊው ቪክተር ትሮይኪ እንዲሁም ቡልጋሪያዊው ግሪጎር ዲሚትሮቭ ይገኙበታል።
‹‹ይህንን የቴኒስ ውድድር ያሰናዳሁት ከቅን ልቦና ተነስቼ ነበር፡፡ ሁሉንም የጤና መመርያዎች ለመከተል ሞክረናል፡፡ ይህ አሳዛኝ ዜና በመምጣቱ ከልብ አዝናለሁ›› ብሏል ቾኮቪች፡፡
የእንግሊዙ እውቅ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች አንዲ ሙሬይ በበኩሉ ‹‹ይህ ለኛ ትልቅ ትምህርት ነው›› ሲል ትዊተር ሰሌዳው ጽፏል፡፡
ይህንን ውድድር በዚህ ወቅት ማሰናዳት አደጋ ሊኖረው ይችላል የሚል ሐሳብ ቀድሞውንም ሲንጸባረቅ ነበር፡፡
የቴኒስ ውድድሩ በጆኮቪች ሐሳብ አመንጪነት ሲሰናዳ እውቅ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቾች ራሳቸውን ከውድድር በማራቃቸው እንደ ማነቃቂያ ሊሆናቸው ይችላል፤ በዚያውም የበጎ አድራጎት ሥራ ይሆናል በሚል ነበር፡፡
ጆኮቪች በድረገጹ እንደጻፈው መጀመርያ ቤልግሬድ እንደደረሰ በኮሮና መያዙ ይፋ የተደረገው ኖቫክና ቤተሰቡ ነበር፡፡ ሆኖም ምንም ምልክት አያሳይም ነበር፡፡
ይህ በሰርቢያ የተሰናዳው ውድድር 4ሺህ ሰዎች ታድመውታል፡፡ ሜዳ ቴኒስ ተጫዋቾችም ከውድድር በኋላ መሸታ ቤት ሲደንሱ የሚያሳይ ፎቶ ወጥቷል፡፡
በመጀመርያው ቀን ውድድር የቡልጋሪያው ዲሚትሮቭ ከክሮሺያው ኮሪክ ጋር ቅዳሜ እለት ተጫውተው ነበር፡፡
ጆኮቪች ከዚህ ቀደም የኮሮናቫይረስ ክትባት ቢኖር እንኳ ክትባቱን ለመወጋት ፍቃደኛ እንደማይሆን በትዊተር ገጹ በመጻፉ የሴራ ንድፈሐሳብ አራማጆች ክትባቱ በቢልጌትስ የተቀነባበረ ስለመሆኑ እንደ አንድ ማስረጃ የርሱን ጽሑፍ ሲያጋሩ ነበር፡፡
ሚስቱ ጄሌና ከዚህ ቀደም ኮሮናቫይረስ የመጣው በ5ጂ ቴክኖሎጂ ነው የሚል ይዘት ያለው ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ማጋራቷ ሲታይ ቤተሰቡ በወረርሽኙ ምንነት ላይ ጥርጣሬ እንደነበረው እንዲገመት በር ከፍቷል።














