ኢትዮጵያ መሰረታቸውን ግብጽ ባደረጉ ቡድኖች የመረጃ መረብ ጥቃት ተሞከረብኝ አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መሰረታቸውን ከግብጽ ያደረጉ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ተቋማት የመረጃ መረብ መዋቅር ላይ ጥቃት ለማድረግ ሞክረው እንደነበር የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው እንዳለው በሦስት የተለያዩ ቡድኖች አማካይነት የተሞከረው የመረጃ መረብ ጥቃት በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናን ለመፍጠር ያለመ እንደሆኑ ገልጿል።
ተቋሙ እንዳለው የጥቃቱ ሙከራ ባደረጉት ቡድኖች ላይ ክትትል ሲያደርግ እንደቆየና በተለይ ባለፈው አርብና ቅዳሜ ከፍተኛ የመረጃ መረብ የጥቃት ሙከራዎች ማድረጋቸውንና በኤጀንሲው አማካይነት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልከቷል።
በዚህም የጥቃት ሙከራ የ13 የመንግሥት፣ 4 መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ድረ-ገጾች ኢላማ በማድረግ "ለማስተጓጎል ሙከራ" መደረጉን ገልጾ፣ ተቋማቱ እነማን እንደሆኑ ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ይህ የመረጃ መረብ ጥቃት ሙከራው የተደረገው 'ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ'፣ 'አኑቢስ ዶት ሃከር' እና 'ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ' በተባሉ መረጃ መረብ ሰርሳሪ ቡድኖች መሆኑን ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አመልክቷል።
ኤጀንሲው የጥቃቱ ኢላማ የነበሩት ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመንግሥት ተቋማት፣ የደኅንነት መስሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች ድረ-ገጽ ላይ መሆኑን ባወጣው መረጃ ገልጿል።
ጨምሮም በአገሪቱ ባሉ ተቋማት የመረጃ መረብ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሞክረዋል ያላቸው ቡድኖች ላደረጉት ሙከራ ኃላፊነቱን የመውሰዳቸውንና አላማቸውም ኢትዮጵያ እየገነባቸው ካለው ከህዳሴው ግድብ ጋር የተያያዘ ነው ብሏል።
ቡድኖቹ በዚህ ሙከራቸው ኢትዮጵያና ግብጽ ለመግባባት ካልቻሉበት የግድቡ የውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ በሁሉም አቅጣጫ ተጽእኖን በኢትዮጵያ ላይ ለማሳደር መሆኑን ኤጀንሲው አመልከቷል።
የመረጃ መረብ ጥቃቱ ኢላማ በነበሩት ተቋማት ላይ ጉዳት እንዳላደረሰ ገልጾ፣ ለዚህም ኤጀንሲው አስቀድሞ ቅድመ ዝግጅት በማድረጉ ጥቃቱን እንዳከሸፈ በመጥቀስ፤ ይህ ባይሆን ኖሮ ጥቃቱ በአገሪቱ ላይ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖሊቲካዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበር ገልጿል።
የመረጃ መረብ ጥቃቶች በተለያዩ አገራት ውስጥ በተለይ የደኅንነትና የፋይናንስ ተቋማትን ኢላማ በማድረግ የሚፈጸም ድርጊት ሲሆን የሚያደረውሰውም ጉዳት እጅግ ከባድ ነው።
እነዚህ ጥቃቶች የተለያዩ ፍላጎቶችን ለማስፈጸም በግለሰቦች፣ በተደራጁ ቡድኖች፣ በተቋማት እንዲሁም በመንግሥታት አማካይነት ይፈጸማል።
ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ተቋማት ላይ ተሰነዘረ የተባለው የመረጃ መረብ ጥቃት መነሻው ከግብጽ መሆኑንና ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ፍላጎትን ለማስፈጸም መሆኑን ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አመልክቷል።












