ለ50 ዓመታት ሳይፈታ የቆየውን የሒሳብ እንቆቅልሽ በቀናት ውስጥ የፈታችው ተማሪ

የፎቶው ባለመብት, University of Texas
አሜሪካዊቷ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ለ50 ዓመት የበርካቶችን አእምሮ የፈተነውንና ሳይፈታ የቆየውን የሒሳብ ቀመር በቀላሉ፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ፣ በትርፍ ሰዓቷ ፈትታዋለች።
ሊሳ ፒኪሪሎ ሦስተኛ ዲግሪዋን በዩኒቨርስቲ ኦፍ ቴክሳስ እየሰራች ነው።
ከዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሯ ካሜሮን ጎርደን ጋር እያወራች በነበረበት ወቅት እግረ መንገዷን ለወሬያቸው ማጣፈጫ በሚል የሰራችውን የሒሳብ ስሌት፣ ያቃለለችውን የሒሳብ ቀመር አነሳች።
"መጮህ ጀመረ 'እንዴት በጣም ደስተኛ አልሆንሽም?'" እንዳላት ፒኪሪሎ በኳንታ ለሚታተመው የሳይንስ ዜናን የሚሰራጨው ድረገጽ ተናግራለች።
"እብድ ነው የሆነው" በማለትም የነበረውን ሁኔታ ያስታወሰችው።
ወይዘሪት ፒኪሪሎ ሦስተኛ ዲግሪዋን ሳትይዝ የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያሰጣት የሒሳብ ቀመር 'ኮንዌይ ኖት ፕሮብሌም' ይሰኛል።
ኮንዌይ ኖት ፕሮፕሌም (Conway knot problem) በብሪታንያዊው ሒሳብ ሊቅ ጆን ሆርቶን ኮንዌይ በ1970 የተቀመረ ነው። ፒካሪሎ ግን ስለዚህ መልመጃ የሰማችው ለመጀመሪያ ጊዜ እአአ በ2018 በአንድ ሴሚናር ላይ መሆኑን ታስታውሳለች።
ፕሮፌሰር ጎርደን "ምን ያህል እድሜ ጠገብ ዝነኛ የሒሳብ መልመጃ መሆኑን ያወቀች አይመስለኝም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የወይዘሪት ፒኪሪሎ ሥራ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የታተመ ሲሆን እርሷም ይህንን የጥያቄ ጎምቱ፣ የመልመጃዎች አውራ በመፍታቷ በማሳቹሴት ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝታለች።
"የኮንዌይ ኖት መልመጃ ለረዥም ዓመታት በሒሳብ ሊቃውንት ሊፈታ ሳይችል ቆይቷል" ያሉት ስፔናዊው ተመራማሪ ያቬር አራማዮና ናቸው።
ይህ የሒሳብ ቀመር እንደምን ያለ ነው?
ሒሳባዊ ቋጠሮ (Mathematical knots) የአንድ የሒሳብ ዘርፍ ሲሆን የሚመደብበትም ክፍል ቶፖሎጂ ይሰኛል።

በቀላል ቋንቋ፣ ቶፖሎጂ የሚያጠናው ቁሶች ቅርጻቸውን ሲቀይሩ፣ ሲጎብጡ፣ ሲጠመዘዙ እና ሲወጠሩ-ነገር ግን ሳይሰበሩ እንዴት ያለ ጠባይ እንደሚያሳዩ ነው።
ኖት ቲዎሪ (የጥልፍልልፎሽ ኀልዮት) የቶፖሎጂ አንዱ ዘርፍ ነው።
ከእውኑ ዓለም ምሳሌዎች በተጻራሪው፣ ሒሳባዊ ቋጠሮ መጨረሻዎቹ የተሳሰረ ነው። በእርግጥ ቀላሉ ቋጠሮ የቀለበት ቅርጽ አለው፤ እናም ሊዋሃድ አይችልም።
ነገር ግን የበለጠ ውስብስብ ይሆናል፤ ይህም አንዱ በአንዱ ላይ ሲጠላለፍና ሲቆላለፍ ነው።
ይህንን በቀላሉ ለማስረዳት ገመድን ማሰብ በቂ ነው የሚሉት ማሪታኒያ ሲልቬሮ ናቸው። በሴቪሊ ዩኒቨርስቲ የሒሳብ ሊቅ የሆኑት እኚህ ምሁር "የጥልፍልልፎሽ ኀልዮት በአንድ ገመድ ላይ የሚከሰትን ቅርጽ አልባነት ያጠናል" ሲሉ ያክላሉ።
"በሌላ ቋንቋ፣ ገመዱን እንዴት አድርገን እንደምንጠመዝዝ፣ እንደምናጎብጠው፣ እንደምናጥፈው፣ እንደምንጨምቀው. . .ገመዱን ለመቁረጥ የማናደርገው ነገር ማለት ነው። ያ ክልክል ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቶፖሎጂ ታዲያ በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች ውስጥ ቁልፍ ቦታ አለው። የምጣኔ ሃብት ገበያዎችን እንዲሁም የዲኤንኤ ሞሎኪውልስን ቅርጽ ለማጥናት ይውላል።
የኮንዌይ ኖት
ከኖት ፕሮብሌም ጀርባ ያለው ሰው ጆን ሆርቶን ኮንዌይ በሚያዚያ ወር በተወለደ በ82 ዓመቱ በኮሮናበቫይረስ ምክንያት ሞቷል።
ሊቨርፑል የተወለደው ይህ የሒሳብ ሊቅ በዘርፉ ምሁራን ዘንድ ተወዳጅ እንደነበር ይነገርለታል።

የፎቶው ባለመብት, Denise Applewhite/Princeton University
ወይዘሪት ፒኪሪሎ 11 ጊዜ የተጠላለፈን የኮንዌይ ኖት ነው ተመሳሳዩን በመስራት "አቻ ጥልፍልፍ" መፍታት የቻለችው።
እርሷ በአቻነት የሰራችው ጥልፍልፎሽን የእውቁን የሒሳብ ሊቅ የ50 ዓመት ሚስጥር ለመፍታት ተጠቀመችበት።
"ቀን ቀን ለመስራት አልፈልግም ነበር፤ ያ ለሒሳብ የሚመች አይመስለኝም. . . ልክ የቤት ሥራ እንደተሰጠኝ በማሰብ ቤት ወስጄ ነው የሰራሁት" ብላለች።
ወይዘሪት ፒኪሪሎ በአሜሪካ ማይን በምትባል ገጠራማ ስፍራ ተወልዳ ያደገች ሲሆን ሒሳብን ያጠናችው በቦስተን ኮሌጅ ነው።














