የምግብ ብክነትን ለማስቀረት መተግበሪያ በናይጄሪያ

"ለማንኛውም ሰው ለማንኛውም ልጅ ያለምግብ የማይታመን ነው። አቅልንም ያሳጣል።"
"አስታውሳለሁ ልጅ እያለሁ ምግብ ስላልነበረ በቀን ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ጥሩ ምግብ የምበላው።"
የኦስካር ኢፖኒሞ ጥረት የልጅነት ርሃብ ያቀጣጠለው ነው። አባቱ በህመም ምክንያት ሥራ መስራት ባለመቻሉ ቤተሰቡ በሙሉ ተርቦ ነበር።
አሁን ግን በናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ የሚገኘው ይህ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ሥራ ፈጠሪ ለዚህ የምግብ አቅርቦት የኢፍትሃዊነት ችግር ምላሽ አለው።
ቾውበሪ የተሰኘ እና ሰዎችን መጨረሻው የቆሻሻ ገንዳ ሊሆን ከሚችል ምግብ ጋር የሚያገናኝ መተግበሪያ ባለቤት ነው። እስካሁን መተግበሪያው 35 በሚሆኑ በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና በናይጄሪያ በሚገኙ ሌሎች ተቋማት ተቀባይነትን አግኝቷል።
በአቡጃ በሚገኝ አንድ ሱፐር ማርኬት ውስጥ ያለ አንድ የሽያጭ ረዳት በስንዴ ዱቄት ከተሞላው መደርደሪያ ወደ ሱቁ ጋሪ እየጫነ ነው። የቾውበሪ መተግበሪያን በመጠቀም ምርቱን በቅናሽ ዋጋ ለገዛው ስሪፍቲ ስላየር ለተባለው ግብረሰናይ ድርጅት እያዘጋጀ ነው።
ቅናሽ የተደረገባቸው ምርቶች
በአንደኛው መተላለፊያ ቆመን እያለ ኦስካር ቴክኖሎጂው እንዴት እንደሚሰራ ሊያሳየኝ ታብሌቱን አወጣ።
"በዚህ መተግበሪያ ውስጥ ነጋዴዎችን የአገልግሎት ጊዜያቸው ሊጠናቀቅ የተቃረቡ ምርቶቻቸውን በተመለከተ መረጃ እንዲያስቀምጡ የሚረዳቸው የአሰራር ሥርዓት ወይም ሲስተም አለን" በማለት ያብራራል ኦስካር።
"እነዚህ ምርቶች የአገልግሎት ጊዜያቸው እየተገባደደ በመሆኑ በነጋዴዎቹ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ተደርጎባቸዋል። ምግቦቹ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሲያልፍ በነጋዴዎቹ እንደዋዛ ሊጣሉ ይችሉ የነበሩ ናቸው። በእኛ የአሰራር ሥርዓት ምክንያት ግን ኪሳራቸውን ሊያድኑ የሚችሉበት መንገድ አላቸው።"
"በተመሳሳይ ሰዓት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምግቡን በርካሽ ዋጋ በመውሰድ የሚያሰራጩት ተጨማሪ ምግብ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።"

ይህ ሱፐር ማርኬት ቾውበሪ የተባለውን መተግበሪያ መጠቀም የጀመረው ያኔ የዛሬ ሁለት ዓመት ወደ ሥራ እንደገባ ነበር።
"ከእኛ ጋር የሚሰሩት አንዳንድ ሱቆች ከዚህ በፊት ይጥሉት ከነበረው እስከ 80 በመቶ የሚደርስ ምግብ ማዳን እንደቻሉ ይናገራሉ" ይላል ኦስካር።
በተባበሩት መንግሥታት የተሰራ ጥናት እንደሚያመለክተው በመላው ዓለም ለምግብነት ከሚመረተው ምግብ አንድ ሦስተኛው ይጠፋል ወይም ይጣላል።
ይህም በየዓመቱ 1ነጥብ 3 ቢሊዮን ቶን ይሆናል። የተባበሩት መንግሥታት አሃዝ አክሎም ምንም እንኳን በቂ ምግብ በዓለም ላይ ቢኖርም ከዘጠኝ ሰዎች አንዱ ጾሙን እንደሚያደር ይጠቁማል።
የኦስካር ችግሩን የመገንዘብ አቅም በታችኛው ረድፍ ላይ የሚገኙትን እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የመድረስ ተልዕኮው ማጠንጠኛ ነው።
"እነዚህ ሰዎች ዘመናዊ ስልኮች ባይኖሯቸውም ከመተግበሪያው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወሳኝ ናቸው" ይላል ኦስካር።

ስሪፍቲ ስላየር የቾዉበሪ መተግበሪያን በመጠቀም ለምግብ ስርጭት መርሃ-ግብራቸው ቅናሽ የተደረገባቸውን ምርቶች ከሚገዙት በርካታ ግብረ ሰናይ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።
መርሃ ግብራችው የሚደገፈው የተለገሳቸውን ልባሽ ጨርቆች በመሸጥ ነው። ነገር ግን የስሪፍቲ ስላየር መስራች ልጅኦማ ንዊዙ እንደሚሉት ቾውቤሪ የድጋፍ መጠናቸውን ከፍ እንዲል አድርጎላቸዋል።
"ምገባውን የጀመርነው በ40 ሰዎች ነበር፤ ነገር ግን የማህበረሰቡ ቁጥር ማሻቀቡን ቀጠለ። አሁን እነሱን እና በአቅራቢያው የሚገኙ ማህበረሶችን ጨምሮ ወደ 200 ያህል ሰዎች በየሳምንቱ እሁድ እንመግባለን" ይላሉ።
"የምንመግባቸው ሰዎች ቁጥር እያደገ ሲመጣ ወጪያችንን ለመቀነስ አማራጭ መንገዶችን መፈለግ ጀመርን። ከቾውበሪ ጋር አብሮ የመስራት መልካሙ ነገርም ምግብን በምንፈልገው ብዛት ማግኘት ማስቻሉ ነው።"
የተባበሩት መንግሥታት አሃዝ እንደሚያሳየው በናይጀሪያ ከ14 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር አለባቸው።
የምግብ ዋስትናን የሚያቀነቅነው ሼሁ ሙሳ ያርአድዋ ፋውንዴሽን ውስጥ ዳይሬክተር አማራ ንዋንክፓ እንደሚሉት ርሃብ ዋነኛው ችግር ነው።
"እኔ እንደማስበው በምግብ አቅርቦት እና ተደረሻነት የገጠመን ችግር ለፈጠራ ሰዎች መልካም አጋጣሚን ሆኖላቸዋል። ከችግሩ ለመውጣት ከፈጠራ ውጪ ምንም አማራጭ የለንም" ይላሉ አማራ።

የምገባ መርሃ ግበር በሚካሄድባት ከአቡጃ ወጣ ብላ በምተገኘው ፕያካሳ በተሰኘችው አነስተኛ እና በተራሮች በተከበበችው ከተማ ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት። "ብዙውን ጊዜ ጉዳዩን በተመለከተ ስሜታዊ እሆናለሁ። በቀላል ሀሳብ ሰዎችን በትክክለኛው መንገድ መድረስ እንደሚቻል ቀልቤ ይነግረኛል። ግን ስሜቴ የተደበላለቀ ነው" ብሏል።
ከእርሱ ጋር ለጉብኝት በሄድንበት ወቅት በዋናነት ሴቶች እና ህጻናት የሆኑ 50 ያህል ሰዎች ለምሳ ተሰልፈው ነበር። እንደተነገረን ለአብዛኞቹ ይሄ የሳምንቱ ትልቁ የምግብ ጊዜያቸው ሊሆን ይችላል።
ኦስካር እንደሚለው "ችግሩ ማስፋቱ ላይ ነው። ሥራችን ለመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ተቋርጦ የሚቆየው እዚያ ላይ ነው። በረጅሙ ጉዞ ውስጥ አለሁበት። የምግብ እሴት ሰንሰለት እስካለ ድረስ መቼውንም ቢሆን በአካባቢው የምግብ ዝውውሩ ይቀጥላል።"
የምግብ ብክነት ከፍተኛ ችግር ነው፤ ይህ ሥራ ፈጣሪም ለዚህ ቀላል መፍትሄ ዓለም አቀፍ ምኞቶች አሉት።
አንድ ጊዜ በናይጀሪያ እና በአህጉረ አፍሪካ ተጽዕኖ ማሳደር ከጀመረ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎችን ህይወት መቀየሩን እንደሚቀጥል ተስፋ ሰንቋል።
ይህ የቢቢሲ ተከታታይ መሰናዶ የተዘጋጀው ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።
#bbcinnovators












