ትኩረት ያልተሰጠው የሴቶች አልኮል አዘውታሪነት እና በጉበታቸው ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት

ወይን የያዘ ብርጭቆ የያዙ ሰዎች እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በ31 ዓመቴ አልኮል መጠጣት ካላቆምኩ ልሞት እንደምችል በሐኪሞች ተነገረኝ።

በጣም ነበር የደነገጥኩት። ምክንያቱም በየቀኑ አልጠጣም ነበር። ብቻዬን ጠጥቼም አላውቅም። የምጠጣው በማኅበራዊ ግንኙነቶች ወቅት ከወዳጅ ጓደኛ ጋር መጠጣት ደስ ስለሚለኝ እንጂ የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ ስለሆንኩ አልነበረም።

በእርግጥ ከአስራዎቹ መጨረሻ እስከ ሃያዎቹ መጨረሻ ድረስ ባለው ዕድሜዬ ምን አልባት ጠጪ ልባል እችላለሁ። ነገር ግን ምንም የተለየ ነገር አይሰማኝም ነበር። ምክንያቱም በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችም ተመሳሳይ ነገር ነበር የሚያደርጉት።

አሁን ላይ ግን መዘዝ አምጥቶብኛል።

እናት የሆንኩት በቅርቡ ነው። ሁልጊዜ ድካም ይሰማኝ ነበር፤ እናም ምን እንደሆንኩ ለማወቅ ለምርመራ ሐኪም ጋር ሄድኩ። የደም እና የጉበት ምርመራ እንዳደርግ ተነገረኝ።

ሌሎችም ተጨማሪ ምርመራዎች ከተደረጉልኝ በኋላ ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ የተከሰተ ‘ሊቨር ፋብሮሲስ’ (የጉበት ጠባሳ) እንዳለብኝ ተረጋገጠ። ይህ ምን አልባት ከአልኮል መጠጥ ልማዴ የተነሳ ያጋጠመኝ ሊሆን ይችላል።

የምርመራው ውጤት ከተነገረኝ በኋላ ልጄን ይዤ በድንጋጤ ወደ ቤት ነበር ሄድኩት። በእርግጥ ይህ በእኔ ላይ ደርሶ ይሆናል፤ ነገር ግን ለዚህ የተዳረኩት እኔ ብቻ ላልሆን እንደምችል እያሰብኩ ነበር።

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከመጠጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ሞቶች መመዝገብ ከተጀመረበት ከአውሮፓውያኑ 2001 ጀምሮ በአልኮል መጠጥ ብቻ የሚከሰቱ ሞቶች ቁጥር ጨምሯል።

ይህ ችግር በአብዛኛው በወንዶች ላይ የሚታይ ቢሆንም በተለይ ጎልማሳ የሆኑ ወንዶች እና ከ45 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ በሚከሰት የጉበት በሽታ እየሞቱ እንደሆነ ከአውሮፓውያኑ 2001 እስከ 2022 ያሉ አሃዞችን የያዘው የብሔራዊ ስታትስቲክስ ቢሮ ሪፖርት ያስረዳል።

የቢቢሲ ጋዜጠኛዋ ሃዜል ማርቲን

የፎቶው ባለመብት, Daniel Taylor-Sweet / BBC

የምስሉ መግለጫ, የቢቢሲ ጋዜጠኛዋ ሃዜል ማርቲን የአልኮል መጠጥ እንድታቆም ተነግሯታል።

በአንድ ጊዜ የምንጠጣው መጠጥ በየተወሰነ ጊዜ ከምንጠጣው ተመሳሳይ መጠን ካለው መጠጥ በበለጠ ጉዳት ያስከትላል።

በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የባለሙያዎች ቡድን የተሠራ አዲስ ጥናት በአንድ ጊዜ ከመጠን በላይ መጠጣት በጉበት ላይ አራት እጥፍ ጉዳት እንደሚያስከትል አመልክቷል።

ከመጠን በላይ መጠጣትን ስናስብ ወደ አእምሯችን የሚመጣው፣ ሰዎች ከመጠጥ ቤት ሰክረው እየተንገዳገዱ ሲወጡ እና በየመንገዱ ላይ ሲወድቁ ነው። ሆኖም ከመጠን በላይ መጠጣት ለዚህ ከሚዳርገው የአልኮል መጠጥ መጠን ያነሰ ሊሆንም ይችላል።

በዩኬ ከመጠን በላይ መጠጣት ለሴቶች በአንድ የመጠጥ ጊዜ ከስድስት ዩኒት (60 ሚሊ ሊትር) በላይ የተጣራ አልኮል የመጠጣት ያክል ነው። ይህም በሁለት ትላልቅ ብርጭቆ ወይን እንደመጠጣት ይታሰባል። ለወንዶች ደግሞ ስምንት ዩኒት ወይም ከዚያ በላይ።

በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ ሆስፒታል አማካሪ የሆኑት ሄፓቶሎጂስት (የጉበት ስፔሻሊስት) ደቢ ሻውክሮስ በ40ዎቹ እና 50ዎቹ የሚገኙ በተለያዩ ሙያ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን ያክማሉ።

“እነዚህ ሴቶች በአንድ ጊዜ የተለያየ ሥራ የሚሠሩ ናቸው። ምን አልባት አዲስ ቤተሰብ መሥርተው ይሆናል። ሱሰኛ አይደሉም ግን እንደ ልማድ ብዙ ይጠጣሉ” ይላሉ።

ሄፓቶሎጂስት [የጉበት ስፔሻሊስት] ደቢ ሻውክሮስ የመመርመሪያ መሣሪያ አንገታቸው ላይ አድርገው በሆስፒታል ኮሪደር ላይ ቆመው
የምስሉ መግለጫ, ፕሮፌሰር ደቢ ሻውክሮስ እንደሚሉት በጉበት በሽታ ተይዘው ሕክምና የሚከታተሉ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ ነው።

እኔ በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ባልሆንም ሐኪሟ የሚሉት እኔንም ሊገልጸኝ ይችላል።

ወጣት እያለሁ በአንድ ምሽት ከመጠን በላይ ሊባል የሚችል አልኮል በቀላሉ እጠጣ ነበር። ሕክምና እስከ ማደርግ ድረስ ግን ይህ ያጋጥመኛል የሚል ስጋት አልነበረኝም።

የደም ምርመራዬ ውጤት ጤናማ እንዳልሆነ ሲረጋገጥ፣ የአልትራሳውንድ እና የጉበት ምርመራ (ፋይብሮስካን) ወዳደረኩበት ወደ ግላስጎው ኒው ቪክቶሪያ ሆስፒታል ተላኩኝ።

ይህ ሁሉ የሆነው ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።

ፋይብሮስካን የጉበትን ጥንካሬ የሚለካ የአልትራሳውንድ ምርመራ ነው። በደም ውስጥ ያለ የኦክስጂን መጠን ሰባት ኬፒኤ ወይም ከዚያ በታች ሲሆን ጤናማ ይባላል፤ የእኔ 10.2 ነበር።

ይህም የከፋ ጠባሳ እንዳለ ነው የሚያመልከተው። ካልተቆጣጠርኩት እና መጠጣት ካላቆምኩ ወደባሰ የጉበት ጠባሳነት (ሲሮሲስ) ሊያድግ ይችላል።

ሕክምና በአውሮፓውያኑ 2024 ዓመት የካቲት ወር ላይ ሲሆን፣ አማካሪዬ ዶክተር ሹረን ዳታ ከአልኮል መጠጥ ራሴን ካቀብኩ ጠባሳው ሊያገግም እንደሚችል ነግረውኛል።

ሃዜል ከጓደኛዋ ጋር እየተሳሳቁ። ሁለቱም ቁጭ ብለው በእጃቸው የመጠጥ ጣሳ ይዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Rachel Adam

የምስሉ መግለጫ, ሃዜል (ከጓደኛዋ በግራ በኩል) ለማኅበራዊ ግንኙነት ስትል መጠጣት የጀመረችው በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል እያለች ሲሆን መጠጣቷ ችግር እንዳልነበረው ነበር የሚሰማት።

በጊዜ ወደ ሕክምና በመሄዴ በጣም ዕድለኛ እንደሆንኩ ነበር የተሰማኝ።

ሐኪሞች በሽታዬን የደረሱበት ይሰማኝ የነበረውን የሰውነት ድካም መንስኤን ለማወቅ ባደረጉት ምርመራ እንጂ ከጉበት በሽታ ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች ብዙውን ጊዜ የሚያሳዩት የመጀመሪያ ምልክት የላቸውም።

የጉበት በሽታቸው መጨረሻ ደረጃ ላይ ከደረሰ አስር ሰዎች ሰባቱ መድማት፣ የፈሳሽ አለመውጣት፣ የዓይን ቀለም መለወጥ ያሉ ምልክቶች ታይቶባቸው ሆስፒታል እስከሚገቡ ድረስ ምን እንዳለባቸው አያውቁም።

የሰሜን ዌልስ ነዋሪ በሆነችው በ39 ዓመቷ ኤማ ጆንስ ላይ የሆነውም ይኸው ነው። ከእርሷ ጋር የተገናኘነው የጉበት ንቅለ ተከላ ካደረገች ከ15 ወራት በኋላ ነበር።

ኤማ እንደኔ ስኬታማ ሥራ እና ደስ የሚል ማኅበራዊ ሕይወት ያላት እና ለማኅበራዊ ግንኙነት ስትል የምትጠጣ ነበረች።

ሆኖም የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ ተጥሎ በነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ወቅት ነገሮች በአስከፊ ሁኔታ ተለወጡባት። በቀን ሦስት ጠርሙስ ወይ ትጠጣ ነበር።

ኤማ ከጋዜጠኛ ሃዜል ጋር ስታወራ
የምስሉ መግለጫ, ኤማ በሕይወት በመቆየቷ እድለኛ እንደሆነች ትናገራለች።

ከዚያም የመጨረሻ ደረጃ የጉበት በሽታ እንዳለባት ወዳወቀችበት ሆስፒታል ገባች። በሕይወት ለመቆየት ከ36 ሰዓታት ያነሰ ጊዜ ነበር የተሰጣት።

በተዓምር ግን ስድስት ወራትን በከፋ ሕመም ውስጥ አልፋ ስትፈልገው የነበረውን ንቅለ ተከላ አደረገች።

የኤማ የማገገም ሁኔታ በሒደት ላይ ያለ ሲሆን ሕይወቷን ለዘላለሙ ለውጦታል። በሕይወት ዘመኗ ሁሉ መድኃኒት መውሰድ ይጠበቅባታል። በሽታ የመከላከል አቅሟ ተዳክሟል። ሰውነቷ በሽታዎችን በቀላሉ መዋጋት አይችልም።

ሆኖም በሕይወት አለች። ደኅና ናት። ከነበረችበት አንጻር አሁን ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ትናገራለች። ቁርጠኝነቷ እና አዎንታዊ አመለካከቷ የሚጋባ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

የጂን ሰዓት (‘ጂን ኦ ክሎክ’)

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ቢሮ የቅርብ ጊዜ መረጃ ከአውሮፓውያኑ 2018 ወዲህ ዕድሜያቸው ከ39 እስከ 45 ዓመት የሆኑ ሴቶች ሞት ምክንያት ከሆኑ ሦስት ዋና ዋና መንስኤዎች አንዱ የጉበት በሽታ ነው።

በሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ የመጠጥ እና የመድኃኒት አጠቃቀም ባህል ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ፊዮና ሜሻም “የሚጠጡ ሴቶች ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ [10 ዓመት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ] እጥፍ ሆኗል” ይላሉ።

ፕሮፌሰሯ በጥናታቸው በ1990ዎቹ እና በ2000ዎቹ የአልኮል ኢንደስትሪው ብዙ ሴት ጠጪዎች ያልነበራቸው ሲሆን፤ ኢንደስትሪዎቹ የፌሚኒዝም እንቅስቃሴን፣ የሴቶች አቅም መጎልበትን እና ነጻነትን እንደ የመነገጃ መሳሪያ ተጠቅመውታል ይላሉ።

አክለውም እንደ አልኮፖፕስ (ከአራት እስከ ስድስት በመቶ የአልኮል መጠን ያላቸው ጣፋጭ አልኮል) እና ሌሎች ዓይነት ምርቶችን ሴቶችን ዒላማ አድርገው ለተጠቃሚዎች ማቅረባቸውን አመልክተዋል።

እነዚህ ልምዶችም ለወጣት ሴቶች የመጠጥ ባህልን አውርሰዋል ይላሉ ፕሮፌሰሯ።

“አሁን ላይ የወጣቶች የአልኮል ፍጆታ በፍጥነት እየቀነሰ ቢሆንም በ30ዎቹ፣ በ40ዎቹ እና 50ዎቹ የዕድሜ ክልል ባሉት ላይ ባህሉ እንደቀጠለ ነው” ብለዋል።

የግላስኮው ካሊዶኒያን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ካርሎ ኢምስሌ በአልኮል መጠጥ ኢንደስትሪዎች ዘንድ አሁንም ተመሳሳይ አካሄድ እንዳለ ያምናሉ።

አሁን ላይ ሴቶች ከአድካሚ ቀን በኋላ ዘና የሚሉበት እና ራሳቸውን የሚጠብቁበት መንገድ ተደርጎ እንደ ፕሬስኮ (የጣልያን ወይን)፣ የጂን ሰዓት እና የወይን ሰዓት እያሉ እንዲጠጡ ይገፋፋሉ።

የአልኮል ኢንደስትሪን የሚወክለው ፖርትማን ግሩፕ በበኩሉ በዩኬ በወንዶች እና በሴቶች ዘንድ ከአልኮል መጠጥ ጋር የተያያዘ የጉበት በሽታ መጨመር አሳሳቢ ቢሆንም ሁልጊዜም አልኮል ሕጋዊ ምርት መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል ብሏል።

ተቋሙ ጨምሮም የአሠራር ደንቡ በተለየ መልኩ ፆታን መሠረት ያደረገ ግብይትን አይከለክልም፤ ነገር ግን አልኮል አምራቾች ምርቶቻቸውን በኃላፊነት ለገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው አስቀምጧል ብሏል።

በመሆኑም በልክ መጠጣትን ለማስተዋወቅ እና ኃላፊነቱን ያልተወጣ የአልኮል ኢንደስትሪን ተጠያቂ የማድረግ ጥረቱን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።