በአሜሪካ 20 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ሳይያዙ አልቀረም

የፎቶው ባለመብት, AFP
ምንም እንኳ አሜሪካ በኮቪድ-19 የተያዙብኝ ዜጎች 2 ሚሊዮን ተኩል ብቻ ናቸው ብትልም ምናልባት እውነተኛው ቁጥር ከዚህ በብዙ ሊልቅ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከላዊ መሥሪያ ቤት (ሲዲሲ) እንዳስቀመጠው እውነተኛው ቁጥር አሁን ከሚባለው በአሥር እጥፍ ሊልቅ ይችላል፡፡
ይህም ማለት በአሜሪካ በአሁን ሰዓት 20 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል እንደማለት ነው፡፡
ይህ መረጃ የወጣው ከአሜሪካ ትልልቅ ግዛቶች አንዷ የሆነችው ቴክሳስ የእንቅስቃሴ ገደብ መላላቱን ለጊዜው እንዲቆይ ከወሰነች በኋላ ነው፡፡
ምክንያቱ ደግሞ በቅርብ ቀናት በርካታ ሰዎች በቫይረሱ በመያዛቸው የሆስፒታል አልጋዎች እጥረት ስለገጠመ ነው፡፡
ለጊዜው አሜሪካ በይፋ ተይዘውብኛል የምትላቸው ዜጎቿ 2 ሚሊዮን ተኩል ገደማ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ከ122ሺ በላይ ነው፡፡
ነገር ግን ከሰሞኑ የደቡብና የምዕራብ አሜሪካ ግዛቶች ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወረርሽኙ እያዳረሳቸው ነው፡፡
የዋሺንግተን ዩኒቨርስቲ የሟቾች ቁጥር በጥቅምት ወር 180 ሺህ ይደርሳል ሲል የተነበየ ሲሆን ምናልባት አሜሪካዊያን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በሥነ ሥርዓት መጠቀም ከጀመሩ ግን የሟቾች ቁጥር በጥቅምት መጨረሻ 146 ሺህ ብቻ ይሆናል ብሏል፡፡
ግምቱ ለምን ተጋነነ?
የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከላዊ መሥሪያ ቤት ሲዲሲ ዳይሬክተር ዶ/ር ሮበርት ሬድፊልድ እንደተናገሩት ከእስከዛሬው ልምድ በመነሳት አንድ ሰው መያዙ ሲረጋገጥ ቢያንስ 10 ሰዎችም አብረው መያዛቸው ይገመታል፡፡
ይህም የሚሆነው ምርመራ ቅድሚያ የሚያገኙ ዜጎች ምልክት የሚያሳዩት ብቻ ስለነበሩና ቫይረሱ ኖሮባቸው ነገር ግን ምርመራ ያላደረጉ በርካታ ሰዎች መኖራቸው እርግጥ በመሆኑ ነው፡፡
‹‹ስለዚህ በዚህ ስሌት መሰረት ምናልባት በመጋቢት፣ ሚያዝያና ግንቦት ባደረግነው የምርመራ ዘመቻ ከጠቅላላ ተያዦቹ 10 ከመቶውን ብቻ ይሆናል የደረስንበት›› ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሬድፊልድ እንደሰጉት ከሆነ ከአሜሪካ ጠቅላላ ሕዝብ ውስጥ ከ5 እስከ 8 ከመቶው በቫይረሱ ሊጠቃ ይችላል፡፡
‹‹ወደ ክረምቱ እየገባን ስለሆነ ርቀትን መጠበቅ፣ ጭምብል ማጥለቅና እጅን ደጋግሞ መታጠብ እጅግ እጅግ ወሳኝ ነው ብለው አበክረው አስገንዝበዋል ዶ/ር ሬድፊልም፣ ሕዝባቸውን፡፡

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቴክሳስ ምን እየሆነ ነው?
ቴክሳስ በሯን ለመክፈት ቀዳሚ ከነበሩ ግዛቶች አንዷ ነበረች፡፡ አሁን ግን በድጋሚ በሯን እየዘጋች ነው፡፡
የግዛቷ ገዥ ሪፐብሊካኑ ግሬግ አቦት ወደተለመደው እንቅስቃሴ ለመመለስ የወሰነውን ውሳኔ ማዘግየታችን በጥንቃቄ ነገሮችን እንድናጤን የሚያደርገን ነው ብለዋል፡፡
ቴክሳስ ትናንትና ሐሙስ ብቻ በ24 ሰዓት ውስጥ 6ሺህ ነዋሪዎች በቫይረሱ ተይዘውባታል፡፡ 47 ሰዎች ደግሞ ሞተውባታል፡፡
በርካታ ሰዎች ወደ ሆስፒታል እየመጡ ስለሆነ የሆስፒታል አልጋ እጥረት ሊገጥም ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡
በቴክሳስ ውስጥ ሂውስተን፣ ዳላስ ኦስቲንና ሳን አንቶኒዮ አካባቢዎች ለቀዶ ጥገና ቀጠሮ የተያዘላቸው በሽተኞች ቀጠሯቸው እንዲሰረዝና አልጋ እንዲለቁ ተደርገዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ብቻ ምርመራ ከተደረገላቸው ነዋሪች 10 ከመቶ የሚሆኑት ላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡
ከቴክሳስ በተጨማሪ አላባማ፣ አሪዞና፣ ካሊፎርኒያ፣ ፍሎሪዳ፣ አይደሆ፣ ሚሲሲፒ፣ ሚዙሪ፣ ነቫዳ፣ ኦክላሆማ፣ ሳውዝ ኮሮላይና አና ዋዮሚንግ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አሻቅቧል፡፡
በአሜሪካ በአንድ ቀን ብዙ ቁጥር የተገኘው በሚያዝያ 24 ሲሆን 36 ሺህ 426 ሰዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ እንደነካቸው ተረጋግጦ ነበር፡፡
ከዚህ ዕለት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ትልቅ ቁጥር የተመዘገበው ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ሲሆን በአንድ ቀን 36,ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ኒውዮርክ፣ ኒውጀርሲና ኬኔቲኬት ግዛቶች ከሌሎች የአሜሪካ ክልሎች የሚመጡ ማንኛቸውም ዜጎች ለ14 ቀናት የጤና ወሸባ እንዲገቡ የሚያስገድድ መመሪያ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡
የአውሮጳ ኅብረት በበኩሉ በሩን ሲከፍት ከአሜሪካ ለሚመጡ እንግዶች ድንበሩን የሚዘጋበትን ሁኔታ እያጤነ ይገኛል፡፡
አሜረካ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎችም ሆነ በሟቾች ቁጥር በዓለም አንደኛ ስትሆን ብራዚል ትከተላለች፡፡ ሆኖም በቀን ውስጥ የሚመረመሩ ዜጎቿ ቁጥር ከሁሉም አገራት የላቀ ነው፡፡













