ፓኪስታን በተጭበረበረ 'መንጃ ፈቃድ' አውሮፕላን ያበረሩ ፓይለቶቿን እያደነች ነው

የፓኪስታን ኣለም አቀፍ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፓኪስታን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ 150 አውሮፕላን አብራሪዎችን መንጃ ፈቃዳቸውን ሰርዞባቸዋል፡፡

የፓኪስታን አቪየሽን ሚኒስትር ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ይፋ እንዳደረጉት አብዛኛዎቹ የንግድ አውሮፕላን የሚያበሩ የአውሮፕላን 'ሾፌሮች' የማብረሪያ ፈቃዳቸው የተጭበረበረ ነው፡፡

ይህ የማጥራት ዘመቻን የቀሰቀሰው ባለፈው ወር በፓኪስታን 97 ሰዎችን ጭኖ ይበር የነበረ አውሮፕላን ለማረፍ ሲቃረብ በካራቺ መከስከሱን ተከትሎ ነው፡፡

በዚህ አደጋ ከ2 ተሳፋሪዎች ውጭ በሙሉ አልቀዋል፡፡

የመከስከሱ ምክንያት ሲፈተሸም የአብራሪው ብቃት ማነስ እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡

የአቪየሽን ሚኒስትሩ ለፓኪስታን ፓርላማ ሲናገሩ የትራፊክ ተቆጣጣሪውና አብራሪው በአደጋዊ ጊዜ የበረራ መመሪያዎችን ቸል ብለው ነበር ብለዋል፡፡

እንዲያውም አውሮፕላን አብራሪዎቹ ቤተሰቦቻቸው በኮሮናቫይረስ ተይዘው ስለነበር በዚያ ጉዳይ ላይ ወሬ እያወሩ በተዘናጉበት ወቅት ነው አውሮፕላኑ ሊከሰከስ የቻለው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

የአቪየሽን ሚኒስትሩ ጓላም ሳርዋር ካን አውሮፕላኑ የተከሰከሰበትን ምክንያት የመጀመርያ ዙር የምርመራ ውጤት ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት ፓኪስታን ውስጥ የአውሮፕላን መንጃ ፈቃድ ካላቸው 860 ፓይለቶች 260 የሚሆኑት ፍቀዳቸው ወይ የተጭበረበረ ነው ወይም ፈተና ያለፉት ኮርጀው እንደሆነ ደርሰንበታል ብለዋል፡፡

የፓኪስታን አየር መንገድም በበኩሉ ከ434 ፓይለቶቹ ውስጥ 150ዎቹ የተጭበረበረ የአብራሪነት ፈቃድ እንደያዙ ደርሶበታል፡፡

‹‹በአስቸኳይ የበረራ መንጃ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ወስነናል›› ብለዋል ቃል አቀባዩ ለሮይተርስ

በዚህም የተነሳ በርካታ በረራዎች ሊስተጓጎሉ እንደሚችሉ ተሰግቷል፡፡