የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር በስብሰባ ምክንያት ሰርጋቸውን ለ3ኛ ጊዜ ሰረዙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በመጪው ሳምንት የሚካሄደው የአውሮጳ ኅብረት ስብሰባ ነው የሙሽሪት ጠቅላይ ሚኒስትሯን ሰርግ ያስተጓጎለባቸው፡፡
በሐምሌ 17 እና 18 የሚካሄደው የአውሮጳ ኅብረት ስብሰባ በኮቪድ-19 የማገገምያ በጀት ላይ ስለሚወያይ ከዚህ ጉባኤ መቅረትና ሰርግ መደገስ ለጠቅላይ ሚኒስትሯ አልተዋጠላቸውም፡፡
ይህ ስብሰባ ወረርሽኙ ከተሰከሰተ በኋላ መሪዎች ለመጀመርያ ጊዜ በአካል ተገናኝተው የሚወያዩበት ጉባኤ ነው የሚሆነው፡፡
ወ/ት መቲ ፍሬድሪክሰን እጮኛቻውን ቦ ቴንግበርግን ድል ባለ ሰርግ ለማግባት የቆረጡት ቀን ደግሞ ከዚህ ወሳኝ ስብሰባ ጋር ተገጣጥሞባቸዋል፡፡
በፌስቡክ ገጽ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ባሰፈሩት መልእክት ‹‹የዴንማርክን ጥቅም ማስቀደም አለብኝ›› ብለዋል፡፡
ዴንማርክ በወረርሽኙ ለተጎዱ የአውሮጳ ኅብረት አባላት ማገገምያ ገንዘብ መስጠት የሚለውን ሐሳብ የምትቃወም አገር ናት፡፡
ዴንማርክ ብቻ ሳትሆን ስዊድን፣ ኦስትሪያና ኔዘርላንድስ ይህን 750 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ በወረርሽኙ እጅግ ለተጎዱ የአውሮጳ አባል አገሮች መስጠት አግባብ አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ ለአባል አገራት የሚሰጡ ማገገምያ ገንዘቦችም ቢሆን የሚመለሱ መሆን ይኖርባቸዋል ይላሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራ ውሳኔ ይተላለፍበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ወሳኝ ስብሰባ የሚደረገው በብራስልስ ነው፡፡
የሰርግ ዕለታቸው በዚህ የብራስልስ ስብሰባ የተስተጓጎለባቸው የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ወ/ት መዲ ፍሬድሪክሰን በፌስቡክ ሰሌቻው ላይ የሚከተለውን ጽፈዋል፡፡
"ይህን ድንቅ የሆነውን እጮኛዬን የማገባበት የመሞሸሪያዬን ዕለት በጉጉት እየጠበቅኩት ሳለ የብራስልሱ ስብሰባ ለቅዳሜ እንዲሆነ ተወሰነ፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ እጮኛዬ ይህን ይረዳል፤ ታጋሽም ነው፡፡"
የወ/ት ፍሬድሪክሰን እና የአቶ ቦ የሰርግ ሥነ ሥርዓት በፖለቲካ ኩነቶች ሲስተጓጎል ይህ ለ3ኛ ጊዜ ነው፡፡












