ከኮሮና ያገገሙት የ114 ዓመቱ አዛውንት ሕክምናቸውን ጨርሰው ቤታቸው ገቡ

የካቲት 12 ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, Yekatit 12 Hospital Medical College

ከኮሮናቫይረስ አገግመው ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ለተጨማሪ ሕክምና ተልከው የነበሩት የ114 ዓመት አዛውንት ሕክምናቸውን ጨርሰው መውጣታቸውን በየካቲት ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሊያ ፋንታሁን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ዶ/ር ሊያ በየካቲት ሆስፒታል ለግለሰቡ ሕክምና ሲያደርጉ እንደነበር ለቢቢሲ ገልፀው፣ ግለሰቡ ያለ መሳሪያ ድጋፍ መተንፈስ በመቻላቸውና የነበሩባቸውን ኢንፌክሽኖች በመታከማቸው ከሆስፒታል መውጣታቸውን ገልፀዋል።

ግለሰቡ እድሜያቸው 114 ይሆናል ተብለው የተጠየቁት ዶክተሯ " የ114 ዓመት አዛውንት ናቸው። ልጆቻቸውም የልጅ ልጆቻቸውም አብረዋቸው አሉ" ሲሉ መልሰዋል ዶ/ር ሊያ ፋንታሁን።

የልጅ ልጃቸው ቢንያም ልኡልሰገድም ለቢቢሲ እንደገለፀው አያቱ እድሜያቸው 114 ነው።

ሳል ይዟቸው መኖሪያ ሠፈራቸው በሚገኘው ጤና ጣብያ ሲታከሙ እነደነበር ገልጾ ከእርሳቸው በተወሰደው ናሙና ኮቪድ-19 እንዳለባቸው በመታወቁ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል መግባታቸውን ይናገራል።

ግለሰቡ በቅድሚያ በኤካ ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግላቸው የቆዩት ለአስራ አራት ቀን ነው። ከዚያም በሕክምናው ጋር በተያያዘ ኢንፌክሸን ስለነበረባቸው ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ተዘዋውረው ነበር።

ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ በየካቲት ሆስፒታል የጀመሯቸውን አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችና ኦክስጅን ይወስዱ እንደነበር ዶ/ር ሊያ አክለው ገልፀዋል።

የካቲት 12 ሆስፒታል ከገቡ ቀናት እንዳለፏቸው የገለፁት ዶ/ር ሊያ፣ ቀስ በቀስ ያለ መሳሪያ ድጋፍ መተንፈስ በመቻላቸው ወደ ቤታቸው ዛሬ መሸኘታቸውን ተናግረዋል።

የልጅ ልጃቸው ቢንያምም ዛሬ ተሽሏቸው ወደ ቤታቸው ገብተዋል ሲል ለቢቢሲ አረጋግጧል።

በኮሮናቫይረስ ተይዘው በአዲስ አበባ በሚገኘው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ የ114 የእድሜ ባለጸጋ ከበሽታው አገግመው መውጣታቸውን የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ያሬድ አግደው በፌስቡክ ገጻቸው ያስታወቁት ትናንት ነበር።

የ Facebook ይዘትን ይለፉት

የሚፈልጉት ይዘት የለም

በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.

የ Facebook ይዘት መጨረሻ

አዛውንቱ ለተጨማሪ ህክምና የካቲት 12 ሆስፒታል ገብተው ለአራት ቀናት ያህል ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን የተደረገው የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ 232,050 ሲሆን 5,175 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

81 ሰዎች ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ ህይወታቸው ሲያልፍ 1,544 ሰዎች ደግሞ ማገገማቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ይገልፃል።

በአሁን ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸው 3 ሺህ 548 ሰዎች ሲሆኑ 30 ሰዎች በፀና ታመው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ጨምሮ ያሳያል።

ኮሮና