የሩሲያ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች የኮቪድ-19 ክትባት ምርምርን ኢላማ ማድረጋቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያዊያን የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች [ሃከርስ] የኮሮናቫይረስ ክትባት ለመስራት እየጣሩ ያሉ ተቋማትን ኢላማ ማድረጋቸውን የብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎት ቡድን አስጠነቀቀ።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የመረጃ መረብ ደኅንነት ማዕከል፤ መረጃ መንታፊዎቹ ከሞላ ጎደል "የሩሲያ የደኅንነት አገልግሎት አካል" እንደሆኑ በመምሰል እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁሟል።
ቡድኑ ከኮቪድ -19 ክትባት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለመስረቅ በኮምፒዩተሮች፣ በመረጃ ቋት አሊያም የኮምፒዩተር መረቦች ላይ ጉዳት ለማድረስ ሆነ ተብሎ የተሰራ ሶፍትዌር መጠቀሙን ተቋሙ አስታውቋል።
በተቋሙ የኦፕሬሽኑ ዳሬክተር ፖል ቺቸስተር ድርጊቱን "አስቀያሚ" ብለውታል።
ይህ የደኅንነት ተቋሙ ማስጠንቀቂያ የወጣው በዩናይትድ ኪንግደም፣ በካናዳና በአሜሪካ የመረጃ መረብ ደኅንት ተቋማት አማካይነት ነው።
መረጃ መንታፊዎቹ 'ኤፕቲ29' የተባለ ቡድን አካል መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን 'ዘ ዳክስ' ወይም 'ኮዚ ቤር' በመባል ይታወቃሉ።
እነዚህ ቡድኖች ተጋላጭ የሆኑ የኮምፒዩተር ሥርዓቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመጠቀም፤ ከተጠቁ ማሽኖች መረጃዎችን ለመጫንና ለማውረድ የሚያስችሉ 'ዌልሜስ' እና 'ዌልሜል' የተባሉ ማልዌር ሶፍትዌሮችን ተጠቅመዋል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ግለሰቦች በማታለል ወደ ኮምፒውተር ሥርዓቶች የመግቢያ የይለፍ አድራሻዎችን እንዲሰጧቸው በማድረግ በተለያዩ መንገዶች ጥቃቱን እንደሚፈጽሙ ተገልጿል።
እንዱሁም ለግለሰቦች ከታወቀ ሰው የተላከ በማስመሰል የኢሜል መልዕክቶችን በመላክ እንዲሁም ለተለያዩ ወገኖች በተለይ የተዘጋጁ ማታለያዎችንም በመጠቀም ለሚፈጽሙት የመረጃ መረብ ጥቃት አመቺ የሆኑ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ተጠቁመወል።
"በዚህ ዓመት ኤፒቲ29 የተባለው ይህ ቡድን በካናዳ፣ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም በኮቪድ -19 ክትባት ላይ የሚሰሩ በርካታ ድርጅቶችን ኢላማ ያደረገ ሲሆን፤ ከምርምሩ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የአዕምሯዊ ንብረቶችን ለመስረቅ የታሰበ ሊሆን ይችላል" ብሏል ይህንኑ በተመለከተ ከመረጃ ደኅንነት ቡድኑ የወጣው ሪፖርት።
ነገር ግን ሪፖርቱ የተሰረቁ መረጃዎች ስለመኖር አለመኖራቸው በግልጽ የጠቀሰው ነገር የለም።
















