በርካታ የኬንያ መንግሥት ድረ ገጾች ጥቃት ደረሰባቸው

የመረጃ መረብ ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያ መንግሥት የመረጃ መረብ ደኅንነት ባለሙያዎች በበርካታ የሃገሪቱ መንግሥት ተቋማት ድረ ገጾች ላይ ሰኞ እለት የተፈጸመውን ጥቃት ለመቆጣጠር ጥረት እያደርጉ ነው።

በዚህም የተወሰኑት ድረ ገጾች ወደ መደበኛ ሥራቸው የተመለሱ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ችግር እንደገጠማቸው ምልክት እየሰጡ ነው።

በመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች 18 የሚደርሱ በኬንያ መንግሥት የሚተዳደሩ ድረ ገጾች ኢላማ ሆነው መጠለፋቸውና ገጽታቸው እንዲለወጥ መደረጉ ተነግሯል።

የተጠለፉት ድረ ገጾች ሲከፈቱ ኩርድ ኤሌክትሮኒክ ግሩፕ የተባለው የጥቃት ፈጻሚዎቹ አርማ በትልቁ የሚታይ ሲሆን የድረ ገጹ ጽሁፎችም በፍጹም አይነበቡም።

ጥቃት ከተፈጸመባቸው ድረ ገጾች መካከል የመንግሥት ክፍያዎችን የሚያከናውነው እና የኬንያ መንግሥት ገቢዎች ባለስልጣን ይገኙበታል።

የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ሳይረስ ኦጉና ጥቃቱን ተከትሎ እንደተናገሩት የሃገሪቱ የመረጃ መረብ ሥርዓት ደኅንነቱ እንደተጠበቀ መሆኑን ተናግረው፤ የማንኛውም ግለሰብ መረጃም ለጥቃት እንዳልተጋለጠ አረጋግጠዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ ከ24 ሠዓታት በኋላ አንዳንዶቹ ድረ ገጾች ወደ መደበኛ ሥራቸው የተመለሱ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በመንግሥት የመረጃ መረብ ደኅንነት ባለሙያዎች ቡድን አስፈላጊው የደኅንነት ሥራ እየተሰራላቸው መሆኑን የሚገልጽ ጽሁፍን እያሳዩ ነው።

ጥቃቱን እንደፈጸመ የተነገረለት የመረጃ መረብ ሰርሳሪ ቡድን 'ኩርድ ኤሌክትሮኒክ ግሩፕ' ድረ ገጽ ላይ እንደሰፈረው የቡድኑ ተግባር ጥቃት የሚፈጸምባቸውን ድረ ገጾች በመጥለፍ በቀዳሚ ገጾቻቸው የሚታዩ መረጃዎችን ማበላሸትና በሌላ መቀየር ነው።

ይህንን ጥቃት በተመለከተ ቡድኑ ምን ዓላማ ይዞ እንደፈጸመው ግልጽ የሆነ ነገር የለም። ይህ በኬንያ መንግሥት ተቋማት ላይ የተፈጸመው የመረጃ መረብ ጥቃት የኬንያ መንግሥት ከዜጎቹ አስፈላጊ መረጃዎች በዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ የማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ ባለበት ወቅት ነው።

ይህንን ተከትሎም በኬንያዊያን ዘንድ ግላዊ መረጃቸው ምን ያህል በመንግሥት ደኅንነቱ ተጠብቆ ይቆያል የሚለው ስጋት ተፈጥሮባቸዋል።

ሴሪያኑ የተባለው በኬንያ የሚገኝ የመረጃ መረብ ደኅንነት በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው ባለፈው ዓመት የመጨረሻ አራት ወራት ውስጥ ብቻ ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡ የመረጃ መረብ ስጋቶች በኬንያ ውስጥ ተለይተዋል። ሪፖርቱ አክሎም ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ የመረጃ መረብ ስጋቶች ኬንያን 286 ሚሊዮን ዶላርን አስወጥቷታል።