"በፓርቲዎች ምዝገባ ወቅት የህወሓትም ጉዳይ ይታያል" ምርጫ ቦርድ

ሶሊያና

የፎቶው ባለመብት, NEBE

በትግራይ የተካሄደውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ አመራሮቹ በሕግ እየተፈለጉ የሚገኙት የህወሓት ጉዳይ በቅርቡ ከሚካሄደው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ጋር የሚታይ መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

በአገሪቱ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ የፌደራል መንግሥቱ "ሕግ የማስከበር" ባለው ዘመቻ ከትግራይ ክልል አስተዳዳሪነት የተወገደው የቡድኑ አመራሮች የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው እየተፈለጉ መሆናቸው ይታወቃል።

የቦርዱ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሶልያና ሽመልስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት ሊካሄድ ከታቀደው ምርጫ በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እንደ አዲስ የሚታይ ስለሚሆን የህወሓት ጉዳይም አብሮ እንደሚታይ አመልክተዋል።

በዚያ ጊዜም "የእያንዳንዱን ፓርቲ ምዝገባ የማጽደቅ ሂደት ይታያል። ይሄ ፓርቲ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል? እየተባለ ምዝገባ ላይ ያሉ ፓርቲዎች እየታዩ ስለሆነ የህወሓትም ጉዳይ ከዚያ አንጻር ይታያል" ብለዋል።

ነገር ግን ቦርዱ ህወሓትን በተመለከተ እስካሁን ውሳኔ ላይ እንዳልደረሰ የገለጹት ሶልያና፤ "በአደባባይ ደረጃ ህወሓት በአመጻ ተግባር ላይ ተሰማርቷል ሲባል እንሰማለን። በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ደግሞ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገበ ፓርቲ እንዲህ ያለ አመጽ ላይ መሰማራት የለበትም የሚሉ ንግግሮች እንዳሉ እናውቃለን። የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እንደ አዲስ እየታየ ስለሆነ የህወሓትም ጉዳይ ይታያል" ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አገራዊውን ምርጫ ግንቦት መጨረሻ ወይም ሰኔ መጀመሪያ አካባቢ ለማካሄድ እቅድ የያዘ ሲሆን፤ 50 ሚሊዮን ያህል መራጮች ድምጽ ይሰጡበታል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ 50 ሺህ 900 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚኖሩ ተነግሯል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ካለፈው ዓመት ወደ 2013 ዓ.ም የተሸጋገረው ምርጫ፤ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ሲባል አካላዊ ርቀት እንዲጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲደረግና ሌሎችም የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ከዚህ በፊት ግንቦት ላይ አስፈላጊ ወረቀት ያላስገቡ 27 የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰረዛቸው ይታወሳል።

ሶልያና ሽመልስ እንዳሉት፤ ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ አስፈላጊ ሰነዶችን አስገብተው ትክክለኛ መሆን አመሆኑ እየተጣራ ያለ ሲሆን በሌሎችም መሰል ሂደቶች ላይ ያሉ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 78 ናቸው።

አያይዘውም "የትኞቹ ፓርቲዎች አስፈላጊውን መስፈር አሟልተዋል የሚለው እስኪጸድቅ እየተጠበቀ ነው" ብለዋል።

የምርጫ ቦርድ አርማ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ

የምርጫ ጊዜ ሂደት ሰሌዳውን በተመለከተ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞ ያልቀረበ ሲሆን በፓርቲዎች በኩል በዋናነት የተነሱ ጥያቄዎች ከጸጥታ እና ከአባላቶቻቸው ደኅንነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ሶልያና አመልክተዋል።

"ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው መካሄድ አለበት ነው ያሉት። ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ስጋት ይሆናል ያሉት ሁለት ነገር ነው። አንዱ የአገሪቱ የጸጥታ ችግር ነው። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ቢሯቸው እንደሚዘጋ እና አባሎቻቸው ችግር እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል።"

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታ ካላቸው ለቦርዱ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ተጠይቆ፤ 11 ፓርቲዎች የሚገጥማቸውን ችግር ለቦርዱ ማሳወቃቸውን ሶሊያና ጠቅሰው፤ ቦርዱም ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ያስፈልጋል ብሎ ለመንግሥት ማሳወቁን ገልጸዋል።

በየክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የሚገጥማቸውን ችግር በተመለከተ ከገዢው ፓርቲ፣ መንግሥትና ምርጫ ቦርድ ጋር የሦስትዮሽ ውይይት የሚካሄድበት አሠራር መዘርጋቱን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

"ፓርቲዎች ችግር ገጥሞናል ባሉት ጉዳይ ላይ ለክልል አስተዳደር፣ ለፖሊስ ኮሚሽን ወይም ሌላ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ቦርዱ ያሳውቃል" ሲሉም የመስሪያ ቤታቸውን ሚና አስረድተዋል።

የአገሪቱን የጸጥታ ጉዳይ በተመለከተ፤ ቦርዱ የመንግሥትን የምርጫ ጸጥታ እቅድ እንዲያሳውቀው የጠየቀ ሲሆን፤ በእራሳቸው በኩል ደግሞ በምርጫ ወቅት ደኅንነት እንዲረጋገጥ፤ ችግር የሚፈጠርበት ቦታ ደግሞ ሪፖርት የማድረጊያ አሠራር እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ማስተላለፊያ ሥርዓት መዘርጋቱን ተገልጿል።

በቅርቡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባሎቻቸው መታሰራቸውን፣ ቢሮዎቻቸው መዘረፋቸውን ጠቅሰው፤ በምርጫው ለመሳተፍ አስቸጋሪ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።

እነዚህን የመሰሉ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በተመለከተ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ቅሬታ ያቀረቡባቸውን አካላት ከመጠየቅ የዘለለ ሚና መጫወት እንደማይችል ዳይሬክተሯ ሶሊያና አስረድተዋል።

"አቤቱታ ሲቀርብ ተጠያቂውን አካል በዝርዝር አስቀምጡ እንላለን። ከዚያ እኛ ያንን አካል እንጠይቃለን። የማስጸምና የማዘዝ ሥልጣን ባይኖረንም ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥረት እናደርጋለን" በማለት አቤቱታዎች ከተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ እንደሚቀርቡም አመልከተዋል።

ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበት አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ የጤና ችግር በሆነው የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ 2013 ዓ.ም እንዲዘዋወር መደረጉ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በየአምሰት ዓመቱ በምታካሂደው ምርጫ ለፌደራልና ለክልል ምክር ቤቶች ውክልና የግልና የፖለቲካ ፓርቲ እጩዎች የሚወዳደሩ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በተካሄዱት ምርጫዎች ነጻነት ላይ በርካታ ትችቶች ሲቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ቃል ከገቡባቸው ጉዳዮች መካከል ነጻና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ሲሆን፤ ለዚህም በስደት ላይ በቆዩት የቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪና ታዋቂ የሕግ ባለሙያ በሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራ ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ እንዲቋቋምና የሕግ መሻሻያዎችን በማድረግ አውንታዊ እርምጃዎች ታይተዋል።

በዚህ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ስድስተኛውን ዙር ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ምርጫዎች ተለየ ይሆናል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ እየተጠበቀ ነው።