ትግራይ ፡ የተባበሩት መንግሥታት የመብት ጥሰቶችን ለማጣራት ወደ ትግራይ ለመግባት ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሚሼል ባሽሌት በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው መሆኑን ገልጸው በክልሉ ሁሉም ሥፍራዎች ገደብ የለሽ የሰብዓዊ እርዳት እንዲሰራጭ ጥሪ አቅርበዋል።
ማክሰኞ ዕለት መግለጫ ያወጡት ኮሚሽነሯ ድርጅታቸው በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት በተሳተፉ ሁሉም ኃይሎች "የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞ ሊሆን እንደሚችል" የሚያሳዩ መረጃዎች በተደጋጋሚ እየደረሳቸው እንደሆነ አሳውቀዋል።
"ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ሕግ እና የሰብዓዊ መብት ሕግን የተመለከቱ ሰላማዊ ሰዎች በሚኖሩባቸው ቦታዎች ላይ የከባድ መሣሪያ ጥቃት መፈፀም፣ ሰላማዊ ሰዎችን ሆን ብሎ ማጥቃት፣ ሕግ የጣሰ ግድያና ሰፊ ዝርፊያ እንዳለ የሚጠቁሙ መረጃዎች ደርሰውናል" ይላል መግለጫው።
ኮሚሽነር ባሽሌት እንዳሉት ሁለት የሰብዓዊ እርዳታ ተልዕኮዎች ግጭት ወደተከሰተበት ክልል ታህሣሥ 12/2013 ዓ.ም መግባት መቻላቸውን ተናግረዋል። ነገር ግን በክልሉ አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች ያለው የመገናኛ መስመር መቋረጥ ገለልተኛ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።
በትግራይ ክልል ኃይሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል ግጭት የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ነበር።
ከግጭቱ መቀስቀስ በኋላ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል። በርካቶች ድንበር አቋርጠው ጎረቤት አገር ሱዳን በስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።
የመንግሥት ኃላፊነት
የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች መግባት እንዲችሉ ይመቻቻል ሲል ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በኅዳር ወር ላይ ከስምምነት ደርሶ ነበር።
ነገር ግን በትግራይ ክልል ያለው ግብረ ኃይል ቃል አቀባይ የሆኑት ሬድዋን ሁሴን በክልሉ የሰብዓዊ መብት እርዳታ የማመቻቸትና ጥሰቶችን የመመርመር ብቸኛው ኃላፊነት ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው ሲሉ ለጋዜጠኖች ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብት ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑት ሊዝ ቶርሴል ማክሰኞ ዕለት ከጄኔቭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "እስካሁን ወደ ክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ የተደረገው ጥረት 'የሚበረታታ' ቢሆንም ድርጅታችን ወደ ትግራይ ክልል ለመግባት ያልተገደበ መንገድ ማግኘት ይሻል" ብለዋል።
ቃል አባይዋ በክልሉ ያሉ ሰላማዊ ዜጎች በግጭቱ ምክንያት ተጎድተዋል፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ሊጣሩ ይገባልም ብለዋል።
ድርጅታችሁ ወደ ክልሉ ገብቶ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እስካሁን ማጣራት ችሏል ወይ ተብለው የጠየቁት ቃል አቀባይዋ፤ "እስካሁን ድረስ አልቻልንም። እኛም እያልን ያለነው እሱን ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
"አሁን ወደ ክልሉ ለመግባት ያለውን ክልከላ ከግምት ውስጥ በማስገባት እስካሁን ድረስ እያደረግን ያለነው የተለያዩ መረጃዎችን መሰብሰብ ነው። ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው ወደ ሱዳን የገቡ ስደተኞችን ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸዋል፤ ከርቀት ሆነን ሁኔታዎችን ተከታትለናል፤ አዲስ አበባም ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሰዎችን አናግረናል። ይህን ያደረግነው በክልሉ የተፈጠረውን ነገር የሚያሳየን መሠረት ይዘን ወደፊት ለመጓዝ ነው" ብለዋል።
ግጭቱ እንደቀጠለ የሚያመለክቱ ዘገባዎች
ቃል አቀባይዋ አሁንም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ግጭቱ እንደቀጠለ የሚያመለክቱ ዘገባዎች ደርሰውናል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በተደጋጋሚ በክልሉ ያለው ግጭት መቆሙን ተናግሯል።
"ግጭቱ እንደቀጠለ ነው እየተባለ ነው። በተለይ ደግሞ በሰሜን፣ ማዕከላዊና ደቡባዊ ትግራይ ባሉ አንዳንድ ሥፍራዎች" ብለዋል ቃል አቀባይዋ።
የመንግሥት ኃይሎች የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ 'በክልሉ ያለው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ተጠናቋል፤ የትግራይ ክልል ኃይሎች ተሸንፈዋል' ማለታቸው ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ማክሰኞ ዕለት ይህን የሚያጠናክር ሃሳብ ተናግረዋል።
"ትግራይ ክልል ውስጥ አሁንም ጦርነት ቀጥሏል የሚባለው ፍፁም ሐሰት ነው። እርግጥ ነው በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ጦርነት ተፋፍሟል" ብለዋል አምባሳደር ዲና።
በፌዴራል መንግሥቱ የተሾው አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በአንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ሥራ መጀመሩ ተዘግቧል።
በመቀለና በአንዳንድ የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎትና የኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ ጀምረዋል። ነገር ግን በሌሎች ሥፍራዎች አሁንም የመገናኛ መስመሮች እንደተቋረጡ ናቸው።
ይህም በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ሁኔታ በገለልተኛ ወገን ለማጣራት ሁኔታዎችን አስቸጋሪ አድርጓቸዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ ጥሪ
በግጭቱ ምክንያቱ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው አሳሳቢ ሆኗል።
ማክሰኞች ዕለት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽንና አጋሮቹ በትግራይ ክልል ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል የ156 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ጠይቀዋል።
የስደተኞች ኮሚሽን እንደሚለው ከ52 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሱዳን ተሰደዋል። ድርጅቱ 96 ሺህ የሚሆኑ ከግጭቱ በፊት በትግራይ ክልል ተጠልለው የነበሩ ኤርትራዊያን ስደተኞች ጉዳይም እንዳሳሰበው አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ወደ ሱዳን የስደተኛ መጠለያዎች የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም "የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የአስቸኳይ ጊዜ ሥራ ላይ ናቸው፤ ምክንያቱም አሁን ስደተኞቹ ያሉበት ቦታ ለዓመታት እንዲህ ዓይነት የስደተኞች ቁጥር አስተናግዶ አያውቅም" ብሏል።















