ትግራይ፡ የመቀለ ከተማ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች?

አቶ አታኽልቲ ኃይለሥላሴ

የፎቶው ባለመብት, ATAKLTI HAILESSELASE/FB

የምስሉ መግለጫ, አቶ አታኽልቲ ኃይለሥላሴ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከሾማቸው ኃላፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት የመቀሌ ከተማ ከንቲባ አቶ አታኽልቲ ኃይለሥላሴ በከተማዋ የተለያዩ የመሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ መጀመራቸውን ለቢቢሲ ገለጹ።

ግጭቱን ተከትሎ ለሳምንታት ተቋርጠው የነበሩት የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የጤናና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ መጀመራቸውን የገለፁት ከንቲባው፤ የባንክ አገልግሎት ግን በሁለት ቀን ውስጥ የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅት አጠናቀው አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ሲሉ ተናግረዋል።

ባንኮች ከዚህ ቀደም በወረቀት አገልግሎት የሰጡበት አሰራር ስለነበር እርሱን ወደ ሲስተም ውስጥ እስኪያስገቡ ድረስ የአገልግሎት መስጫ ጊዜው መዘግየቱንም አብራርተዋል።

በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል የጸጥታ ኃይሎችና በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ለ40 ቀናት ያህል በክልሉ የኤሌትሪክ፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል።

በእነዚህ ጊዜያት በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የስልክ፣ መብራት፣ ኢንተርኔት ባንክና የመሳሰሉት ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወሳኝ የሆኑ አገልግለቶች ከሥራ ውጪ ሆነው ነበር።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከአንድ ወር በላይ ከሥራ ገበታቸው ርቀው የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ከሰኞ ታህሳስ 05/2013 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ባቀረበው ጥሪ መሰረት፣ በርካታ ግለሰቦች ወደ ሥራ ገበታቸው የተመለሱ ቢሆኑም በየቢሮው በርካታ የወደሙ ነገሮች በመኖራቸው እነዚያን የማስተካከል እና የመመዝገብ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ከንቲባው ጨምረው አስታውቀዋል።

ከመቀለ አዲስ አበባ በአውሮፕላን ለሚደረግ ጉዞ በኢንተርኔት አማካይነት ትኬት ለመቁረጥ አሁንም እንደማይቻል የተጠየቁት ከንቲባው ከኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ጋር በተያያዘ ይህ መፈጠሩን ገልፀው ድርጅቱ የተለያዩ መፍትሄዎችን እያመቻቸ ነው ብለዋል።

ከአዲስ አበባ ትኬት በማስቆረጥ መገልገል እንዲሁም ከእሁድ ጀምሮ ከመቀለ በሚዘረጋ ሲስተም አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

አቶ አታኽልቲ ከከተማዋ ነዋሪ ጋር በየደረጃው እየተወያዩ መሆኑን አመልክተው፣ በየደረጃው የክፍለ ከተማ እና የቀበሌ ምክር ቤቶችንም እያቋቋሙ መሆኑን ተናግረዋል።

"በዋነኛነት የፀጥታው እንዲጠበቅ የምንፈልገው በማኅበረሰቡ ነው" ያሉት ከንቲባው፣ "ያ እስኪሆን ድረስ ግን የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ኃይል ከሚመለከተው የመስተዳድር አካል ጋር በመቀናጀት ፀጥታውን በማስከበር ላይ ነው" ብለዋል።

በከተማዋ አልፎ አልፎ ዘረፋ እንደሚስተዋል የተናገሩት ከንቲባው ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል የሚመደብበት እና ሕዝቡ ድጋፍ በሚፈልግበት ወቅት መረጃ የሚሰጥበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በዋነኛነት ከፀጥታ አካሉ እና በኅብረተሰቡ መካከል እንደ ድልድይ ሆነው እንዲያገለግሉ ከኅብረተሰቡ ውስጥ በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው እና ማኅበረሰቡ እኛን ሊጠብቁን እና ሊከላከሉ ይችላሉ ብሎ ላመነባቸው ወጣቶች በጎ ቃደኞች ምልመላ ተደርጎ ገለጻ በመሰጠት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

"እስካሁን ድረስ በየዕለቱ መልካም የሚባል ለውጥ እየታየ ነው" የሚሉት ከንቲባው የንግድ ቤቶች፣ የመንግሥት የአገልግሎት ተቋማት እንዲሁም የሰዎች እንቅስቃሴ ወደ መደበኛው ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን አስረድተዋል።

በመቀለ ከተማ የመንግሥት ወታደሮች በወሰዱት የሕግ ማስከበር እርምጃ ተገድለዋል ስለተባሉ የከተማዋ ነዋሪዎች የተጠየቁት አቶ አታኽልቲ፣ እርሳቸው ይህንን ኃላፊነት የተረከቡት በቅርቡ መሆኑ እና ከተረከቡበት ቀን አንስቶም ከዝርፊያ እና አለመግባባት ጥቆማዎች ውጪ የሞት መረጃ እንዳልመጣላቸው ጠቅሰው በተሻለ የክልሉን ፀጥታ የሚያስተባብሩ አካላት በጉዳዩ ላይ ምላሽ ቢሰጡ ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ስልካችን ይጠለፋል የሚል ስጋት እንዳላቸው በተመለከተ ተጠይቀውም በዚህም ጉዳይም መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የፌደሬሽን ምክር ቤት የክልሉ አስተዳደር እንዲፈርስ ከወሰነ በኋላ የተሰየመው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሥራው ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል።

ክልሉን ያስተዳድር በነበረው ህወሓትና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ለወራት ከዘለቀ በኋላ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ በክልሉ ልዩ ኃይል ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ለሳምንታት የዘለቀ ወታደራዊ ግጭት መካሄዱ ይታወሳል።

በዚህም ወቅት የስልክ፣ የመብራትና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ለሳምንታት ተቋርጠው የቆዩ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ መቆጣጠሩን ተከትሎ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ክልሉ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተገልጿል።

በትናንትናው ዕለትም በአዲግራትና ውቅሮ ከተሞች ተቋርጦ የነበረው የመብራት አገልግሎት መመለሱን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል በማኅበራዊ ድረገፁ ላይ አስታውቋል።ድርጅቱ አክሎም የሽሬ፣ አክሱምና አድዋ ከተሞች ኃይል እንዲያገኙም እየሰራ መሆኑንና በጥቂት ቀናት ውስጥ የኃይል አቅርቦቱ ሥራ እንደሚጀምር ይጠበቃል።