ትግራይ ፡ ተዘግቶ የቆው የሠሜን ኢትዮጵያ የአየር ክልል ለበረራዎች ክፍት ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአንድ ወር በፊት በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ተዘግቶ የነበረው የሠሜን ኢትዮጵያ የአየር ክልል ለዓለም አቀፍና ለአገር ውስጥ በረራዎች ክፍት መደረጉን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ለቢቢሲ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ወሰንየለህ ሁነኛው (ኮሎኔል) ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከአንድ ወር በላይ ተዘግቶ የነበረው "በትግራይ ክልል በኩል የአየር ክልል ከሰኞ ታህሣሥ 5/2013 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ" ክፍት እንደተደረገ ገልጸዋል።
በዚህም በሠሜን የኢትዮጵያ የአየር ክልል ውስጥ የሚያቋርጡ የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የበረራ መስመሮች ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን አመልክቶ፤ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አውሮፕላን ማረፊያዎች በረራዎችን ለማስተናገድ የተፈቀደላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ወሰንየለህ ሁነኛው (ኮሎኔል) ለቢቢሲ እንደገለጹት የአየር መስመሩ ዝግ ሆኖ በቆየባቸው ሳምንታት ውስጥ በረራዎች የተከለከለውን የአየር ክልል በመተው ሌሎች መስመሮችን ሲጠቀሙ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በሠሜን ኢትዮጵያ ለሚያቋርጡ ማናቸውም የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የበረራ መስመሮች የአየር ክልሉ ለበረራ አገልግሎት ዝግ መሆኑን ለዓለም አገራት ያስታወቀው ጥቅም 25/2013 ዓ.ም ነበር።
ይህም የሆነው በሠሜናዊ የኢትዮጵያ ክፍል በትግራይ ክልል ውስጥ የአገሪቱ ፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ኃይሎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ በጀመረ በተከታዩ ቀን ነበር።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከደኅንነት ጋር በተያያዘ የበረራ መስመሩ ለማንኛውም በረራ መዘጋቱን ባሳወቀበት ጊዜ "ማሳሰቢያ ተላልፎ በረራ የሚፈጽም ማንኛውም አውሮፕላን እንዳይኖር" በማለት በጥብቅ ማሳሰቡ ይታወሳል።
ድርጅቱ በሠሜን ኢትዮጵያ ያለው የበረራ መስመር መዘጋቱን ካሳወቀ ከሁለት ቀናት በኋላ ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም ደግሞ በትግራይ ክልል የሚገኙት የመቀለ፣ የሽሬ፣ የአክሱምና የሁመራ አውሮፕላን ማረፊያዎች ለማንኛውም የበረራ አገልግሎት ዝግ መሆናቸውን ማሳወቁ ይታወሳል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ምሽት በአገሪቱ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ በህወሓት በሚመሩት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ ወታደራዊ ግጭቶች ከመካሄዳቸው በተጨማሪ የፌደራሉ መንግሥት በወታደራዊ ኢላማዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን መግለጹ ይታወሳል።
በተጨማሪም ሮኬቶችን ጨምሮ የከባድ መሳሪያዎች በወታደራዊ ግጭቱ ወቅት ጥቅም ላይ መዋላቸው ተነገረ ሲሆን፤ የህወሓት ኃይሎችም ከትግራይ ክልል ውጪ በባሕር ዳርና በጎንደር ከተሞች የሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ኢላማ በማድረግ የሮኬት ጥቃት መሰንዘራቸውን ገልጸው ነበር።
የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረው ከህወሓት ኃይሎች ጋር ለሦስት ሳምንታት በዘለቀው ተከታታይ ወታደራዊ ዘመቻ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በርካታ ከተሞችን ከተቆጣጠረ በኋላ የክልሉን መዲና መቀለን ኅዳር 19/2013 ሲይዝ ወታደራዊው ዘመቻ ማብቃቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መግለጻቸው ይታወሳል።
ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ሳምንት በክልሉ ውስጥ አለ ባለው ወታደራዊ ግጭት ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ ለተረጂዎች ለማቅረብ እንደተቸገረ ገልጾ ነበር።












