ትግራይ ፡ ቀይ መስቀል ከወር በኋላ መድኃኒቶችና ሌሎች ድጋፎችን መቀለ አደረሰ

አምቡላንሶች በግጭቱ ሳቢያ የተጎዱና ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ወደ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል እያጓጓዙ ነው

የፎቶው ባለመብት, MU

ቀይ መስቀል በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ ከአንድ ወር በኋላ የመጀመሪያውን የመድኃኒትና የእርዳታ አቅርቦት ወደ መቀለ ከተማ ማድረስ እንዳቻለ ገለጸ።

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው ሳቢያ ለሳምንታት መድኃኒቶችና መሠረታዊ የህክምና አቅርቦት ተቋርጦ ነበር። በዚህም ምክንያት መደበኛ ሥራቸውን ለማከናወን ከባድ ችግር ውስጥ የነበሩትን የህክምና ተቋማት ለመደገፍ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እና ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የተላኩ መድኃኒቶች እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ዛሬ መቀለ ደርሰዋል።

የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ባሰራጨው መግለጫ፤ በህክምና ተቋማት ውስጥ ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ በሰባት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች የተላከው ድጋፍ ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ መቀለ ከተማ የደረሰ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ እርዳታ እንደሆነ አመልክቷል።

በከተማዋ ላሉና ከከተማዋ ውጪ ለሚመጡ ህሙማን አገልግሎት የሚሰጠው የመቀለው አይደር ሪፈራል ሆስፒታል ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ባሉት ሳምንታት ውስጥ በነዳጅ እጦትና በመድኃኒቶች አቅርቦት መቋረጥ ምክንያት የጽኑ ህሙማንና የቀዶ ህክምና ክፍሎቹ አገልግሎት ለማቆም ተገደው እንደበር ተገልጿል።

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እንዳለው፤ ሆስፒታሉ ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን በርካታ ሰዎች ተቀብሎ የህክምና አገልግሎት ይሰጥ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ የከፋ ህመም ላለባቸውና መደበኛ ክትትል ለሚፈልጉ የስኳር በሽተኞች፣ የኩላሊት እጥበት ለሚደረግላቸውና ለወላዶች አገልግሎት በመስጠት የሚታወቅ የጤና ተቋም ሲሆን፤ ሆስፒታሉ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚገመቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ዋነኛው የጤና ተቋም ነው።

ከሳምንታት በፊት ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ባወጣው መግለጫ ከመድኃኒት፣ ከውሃ፣ ከኤሌክትሪክና ከሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች አንጻር የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ያለበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁሞ ነበር።

ሆስፒታሉ በእጁ ላይ የነበረውን አቅርቦት በመጠቀም "ለሳምንታት ያለ ተጨማሪ የመድኃኒት አቅርቦት፣ ያለ ውሃ እና መብራት በመቆየቱ ዶክተሮችና ነርሶች የትኞቹን አገልግሎቶች ትተው የትኞቹን እንደሚያስቀጥሉ ለመምረጥ በጣም ተቸግረው ነበር" ሲሉ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የአፍሪካ አህጉር ዳይሬክተር ፓትሪክ ዩሱፍ ተናግረዋል።

ከአንድ ወር በኋላ ዛሬ ቅዳሜ ለሆስፒታሉ የደረሰው አቅርቦት ሆስፒታሉ ለሚያከናውነው የነፍስ አድን ሥራ ከማገዙም በተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎቹ የነበረባቸውን ጫና እንደሚቀንስላቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በጣም አስፈላጊ የሆኑትን መሠረታዊ አቅርቦቶች ወደ መቀሌ በመላክ ከቀይ መስቀል በተጨማሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበኩሉን እንዳበረከተ የተጠቀሰ ሲሆን፤ መድኃኒቶቹና እርዳታው በመቀለ ከተማ ከሚገኘው አይደር ሆስፒታል ባሻገር በክልሉ ጤና ቢሮ እና በቀይ መስቀል መድኃኒት ቤት አማካይነት ለአገልግሎት ይቀርባል ተብሏል።

ዛሬ መቀለ ከተማ በቀይ መስቀል አማካይነት ከደረሰው የመድኃኒት አቅርቦት በተጨማሪ ብርድ ልብሶች፣ የፕላስቲክ መጠለያዎች፣ የማዕድ ቤት ቁሳቁሶች፣ አልባሳት እና ሳሙናዎች እንዲሁም የውሃ እና የንጽህና አገልግሎትን ለማግኘት የሚያስችሉ ቁሳቁሶች እንደደረሱ ተገልጿል።

በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በህወሓት ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በትግራይ ክልለ ውስጥ የእንቅስቃሴና የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው ሳቢያ የህክምናና የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት ለሳምንታት የመሠረታዊ አቅርቦቶች እጥረት አጋጥሟቸው ቆይቷል።

የክልሉ ዋና ከተማ በፌደራል ሠራዊቱ ቁጥጥር ስር ከገባች በኋላ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ወደ ክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እያቀረበ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።