የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማሕበር በዳንሻ አካባቢ አምቡላንሶቹ በታጣቂዎች መመታታቸውን ገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Red cross
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ከሁመራ ዳንሻ ባለው መስመር ሶስት አምቡላንሶች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተኩስ ተከፍቶባቸው ጉዳት እንደደረሰባቸው ገለፀ።
ዶ/ር ሰለሞን አሊ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰብዓዊ ዲፕሎማሲ እና የግንኙነት ጉዳዮች ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በጥቃቱ አምቡላንሶቹ በጥይት ቢመቱም በበጎ ፈቃደኞቹ እና በሠራተኞቹ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሰሜን ጎንደር በኩል የአምቡላንስና የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ለመስጠት ከጥቅምት 24 ጀምሮ ከ10 በላይ አምቡላንሶችን ማሰማራቱን ዶ/ር ሰለሞን ለቢቢሲ ጨምረው ገልፀዋል።
በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ ለወራት በውዝግብ ውስጥ የቆዩት የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል አስተዳደር ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ወደ ግልጽ ጦርነት መግባታቸው ይታወሳል።
በአሁኑ ሰዓት ወደ ጦርነት የተሸጋገረው በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መስተዳደር በኩል የነበረው ቅራኔ እየተባባሰ የመጣው ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት እንደማይካሄድ ከታወቀ በኋላ በትግራይ የተናጠል ምርጫ በመደረጉ ሳቢያ ነው።
ይህንንም ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫውን ሕገወጥና ተፈጻሚነት የሌለው እንደሆነ መወሰኑን ተከትሎ ማዕከላዊው መንግሥት ከክልሉ መስተዳደር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያካሂድና የበጀት ድጋፍ እንዳይሰጥ ከወሰነ በኋላ ነገሮች እየተካረሩ መሄዳቸው ይታወሳል።
ምክር ቤቱ ስልጣኑን የሕገ መንግሥት ትርጉም በመስጠት ማራዘሙ ሕገ መንግሥታዊ መሰረት እንደሌለውም የትግራይ ክልል ይጠቅሳል።
በፌደራልና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ ከ20 በላይ በጎ ፈቃደኞችንም በማሰማራት ወደ ሆስፒታል ለማመላለስ እና የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ በመስጠት መሰማራታቸውን ዶ/ር ሰለሞን ገልፀዋል።
ማሕበሩ በአካባቢው ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት 24 ጀምሮ አምስት አምቡላንሶችን በመመደብ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ እየሰጠ፣ እንዲሁም ሕክምና ወደሚያገኙባቸው ሆስፒታሎች እያመላለሰ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አስረድተዋል።
ዶ/ር ሰለሞን በግጭት ቀጠናው እስካሁን ድረስ ለምን ያህል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ሕክምና እንደሰጡ ተጠይቀው የተጠናቀረ መረጃው እንደሌላቸው ገልፀዋል።
ማህበሩ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በአካባቢው በሚገኙ አራት ሆስፒታሎች የሚያደርስ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሰለሞን፣ የባሰ ጉዳት የገጠማቸውን ደግሞ ወደ ጎንደር ሆስፒታል እንደሚያመላልሱ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሰሜን ወሎ ቆቦ አካባቢም በጎ ፈቃደኞቹን አምስት አምቡላንሶችን እንዲሁም ሁለት ትልልቅ ድንኳኖችን በማሰናዳት በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር በትግራይ ክልል የጤና ቢሮውን ጨምሮ 100 ያህል አምቡላንሶች እንዳሉት ጨምረው ተናግረዋል።
ከክልሉ የቀይ መስቀል ቢሮ ጋር የስልክ መስመር በመቋረጡ ምክንያት እንደማይገናኙ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በመላ አገሪቱ ከ550 በላይ አምቡላንሶች እንዳሉት ኃላፊው ይናገራሉ።












