ኮሮናቫይረስ፡ ኮቪድ-19 ገና አልሰለቸንም- የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዓለም የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባትን ወደማግኘት እየተቃረበ ቢሆንም የኮሮናቫይረስ መከላከያዎችን ማላላት የለበትም ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው አሳሰቡ።
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የኮሮናቫይረስ አሁንም የዛሬ ስምንት ወር እንደነበረው አስጊ ወረርሽኝ መሆኑን እንደቀጠለ ነው ብለዋል።
በመላው ዓለም በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1.2 ሚሊዮን ደርሷል።
በፓሪስ እየተካሄደ ባለው የሰላም ጉባዔ ላይ "በኮቪድ-19 ታክቶን ይሆናል ነገር ግን እርሱ ገና አልሰለቸንም" ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም።
"የአውሮፓ አገራት እየታገሉ ነው ነገር ግን ስርጭቱን ለማቆም የተወሰዱት እርምጃዎች እንዲሁም ቫይረሱ ምንም ለውጥ አላሳየም" ሲሉም አክለዋል።
ከቅርብ ቀናት ወዲህ በኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ላይ የተሻሉ ግኝቶች እየታዩ መጥተዋል።
ሰኞ ዕለት ፋይዘር እና ባዮንቴክ እየሰሩት ያለው ክትባት በተደረገለት የመጀመሪያ ደረጃ ፍተሻ 90 በመቶ የመከላከል አቅም እንዳለው አረጋግጠናል ብለዋል።
ረቡዕ ዕለት ደግሞ የሩስያ ተመራማሪዎች የሰሩት የመከላከያ ክትባት 92 በመቶ ውጤታማ መሆኑን አስታውቀዋል።
ነገር ግን ሁለቱም ክትባቶች የሚደረግላቸውን የቁጥጥር ፍተሻ ማለፍ አለባቸው ተብሏል።
ዶ/ር ቴድሮስ ገና ደህንነቱ እና ውጤታማነቱ መፈተሽ ባለበት ክትባት ላይ መተማመን አደገኛ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።
"ክትባት በፍጥነት ያስፈልጋል፣ ነገር ግን እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ አንልም" ብለዋል።













