ትግራይ ፡ የመቀለው አይደር ሆስፒታል የሕክምና መገልገያ እያለቀበት መሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, MU
በመቀለ ከተማ የሚገኘው አይደር ሪፈራል ሆስፒታል አስፈላጊ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶች እያለቁበት እንደሆነ ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል አስታወቀ።
በግጭቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ሕክምና እየሰጠ ያለው ሆስፒታሉ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
በአካባቢው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ ተገልጿል።
ያሳለፍነው ቅዳሜ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት መቀለን እንደተቆጣጠረ እና ሦስተኛው ምዕራፍ ዘመቻ ምዕራፍ እንደተጠናቀቀ መናገራቸው አይዘነጋም።
የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ግን ትግሉን እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ቀይ መስቀል ምን አለ?
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር እንዳለው፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አምቡላንሶች በግጭቱ ሳቢያ የተጎዱና ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ወደ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል እያጓጓዙ ነው።
ሆስፒታሉን የጎበኙ የድርጅቱ ባልደረቦች "80 በመቶው ታካሚዎች በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። ሌሎች ሕክምናዎች ቆመው ለድንገተኛ አደጋ ብቻ አገልግሎት እየተሰጠ ነው" ብለዋል።
የማኅበሩ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኃላፊ ማሪያ ሶልዳድ "ቁስል ለመስፋት የሚውል መገልገያ፣ ጸረ ተህዋሰ መድኃኒት፣ የህመም ማስታገሻ እና ሌሎችም መድኃኒቶች በአሳሳቢ ሁኔታ እያለቁ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የሞቱ ሰዎችን አስክሬን ማቆያ ፕላስቲክኮች እየጨረሱ መሆኑንም ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ማኅበሩ ምን ያህል ሰዎች እንደተጎዱና እንደሞቱ ምንም መረጃ አልሰጠም። ተጎጂዎቹ ወታደሮች ይሁኑ ሲቪሎች አልተገለጸም።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በትዊተር ገጻቸው፤ "በትግራይ እየተካሄደ የነበረው ወታደራዊ ዘመቻ ተገባዷል" ብለዋል።
በህወሓት ተይዘው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ማስለቀቅ እንደተቻለ እንዲሁም መከላከያ ሠራዊቱ በከተማዋ የሚገኘውን አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ ቁልፍ መሥሪያ ቤቶችን እንደተቆጣጠረም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህ የተካሄደው "ለንጹሀን ዜጎች ጥንቃቄ ተደርጎ ነው" ብለዋል።
ለሮይተርስ በጽሑፍ መልዕክት ያስተላለፉትና አሁን የት እንደሚገኙ ያልታወቀው የህወሓት መሪ በደብረጽዮን "ጭካኔው በትግላችን እስከመጨረሻው ድረስ እንድንገፋ ያበረታታናል" ብለዋል።
በክልሉ የቴሌቭዥን ጣቢያ የተላለፈ የህወሓት መግለጫ፤ "በደረሰው ድብደባ ንጹሀን ዜጎች ተገድለዋል፣ ተጎድተዋልም። እኛም ለጥቃቱ ምላሽ እንሰጣለን" ይላል።
ተንታኞች እንደሚሉት፤ ህወሓት ወደ ሽምቅ ውጊያ አምርቶ ሊሆን ይችላል።
የሰብአዊ ጉዳት ስጋቶች
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መቀለ ላይ ጥቃት ካደረሰ የጦር ወንጀል ሊፈጸም ይችላል ሲል አስጠንቅቆ ነበር።
የሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች መተላለፊያ አለማግኘታቸው እንዳሰጋውም ድርጅቱ አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ መንገድ እንደሚመቻች መግለጹ ይታወሳል። መንግሥት ንጹሀን ዜጎችን ለመጠበቅ ከተባበሩት መንግሥታት እንደሚተባበርም ተገልጿል።
ከትግራይ ክልል ወደ ሱዳን የገቡ ስደተኞች እንደተናገሩት፤ በክልሉ አዋሳኝ ድንበር ላይ የተሰማሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ስደተኞች ወደ ሱዳን እንዳያቋርጡ እያገዷቸው ነው።
ግጭቱ ከተከሰተ ወዲህ ከ40 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ተናግሯል።















