ትግራይ ፡ በአሥመራ ከተማ ከባድ ፍንዳታ መሰማቱን ነዋሪዎች ገለጹ

አሥመራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኤርትራ ዋና ከተማ አሥመራ ትናንት አርብ ምሽት ላይ ከባድ የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱን የከተማዋ ነዋሪዎችና ሌሎች ምንጮች ተናገሩ።

ቢቢሲ በአሥመራ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን በመጠየቅ እንዳረጋገጠው ፍንዳታው የተሰማው ምሽት ላይ ሲሆን ነገር ግን በየትኘው የከተማዋ ክፍል ላይ እንደተከሰተ እርግጠኛ አይደሉም።

በከተማዋ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም ምሽት 2 ሰዓት 24 ደቂቃ አካባቢ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ በከተማዋ መሰማቱን አመልክቶ የፍንዳታው መነሻም ከከተማዋ ውጪ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።

በተጨማሪም የፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ እንደዘገበው የተሰማው የፍንዳታ ድምጽ ከኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ተሰነዘ የሮኬት ጥቃት እንደሆነ አመልክቷል።

በአሥመራ ከተማ ስለተሰማው ከባድ ፍንዳታ ምንነትና ከክስተቱ ጋር ስለሚያያዙ ሌሎች ነገሮች የኤርትራ መንግሥት ባለስልጣናት እስካሁን የሰጡት ምንም መግለጫ የለም።

ቢቢሲ ትናንት ምሽት ከክስተቱ በኋላ ያነጋገራቸው የአሥመራ ከተማ ነዋሪዎችም ፍንዳታው በትክክል የት አካባቢ እንደተከሰተ እንደማያውቁ ገልጸው ነገር ግን ከከተማዋ ውጪ ሳይሆን እንዳልቀረ ግምታቸውን ገልጸዋል።

አሥመራ ውስጥ ከሁለት ሳምንታት በፊት ኅዳር 05/2013 ዓ.ም ተመሳሳይ ከባድ ፍናዳታ መከሰቱ የሚታወስ ሲሆን ይህም ከትግራይ ክልል የተተከሰ ሮኬት መሆኑና ለጥቃቱም የትግራይ ኃይሎች በይፋ ኃላፊነቱን መውሰዳቸው አይዘነጋም።

ከዚህ ጥቃት አንድ ቀን ቀደም ብሎም በሰሜን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በሚገኙት የባሕርዳርና የጎንደር ከተሞች ላይ ተመሳሳይ የሮኬት ጥቃቶች ተፈጽሞ ነበር።

ኤርትራ ቀደም ሲል ስለተሰነዘረባት የሮኬት ጥቃት እስካሁን በይፋ ግልጽ ያለ መግለጫ ሳትሰጥ የቆየች ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ ድርጊቱ የህወሓት መጥፎ ተግባር እንደሆነ ጠቅሰው ትኩረት የሚሰጠው እንዳልሆነም ጽፈው ነበረ።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የትግራይ ልዩ ኃይል በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰነዘሩን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የአገሪቱ መከላከያ ኃይል በክልሉ አመራሮችና ታጣቂዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዛቸው ይታወሳል።

በትግራይ በፌደራል መንግሥቱና በክልሉ ኃይሎች መካከል ለሳምንታት የዘለቀው ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የህወሓት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ኤርትራ የኢትዮጵያ ሠራዊትን እየደገፈች ነው በማለት ሲከስሱ የቆዩ ሲሆን፤ ኤርትራ ግን ጉዳዩ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ እጇ እንደሌለበት ገልጻለች።

የህወሓት አመራሮች ከዚህ ቀደም በአሥመራ ከተማ ላይ ሰነዘርን ባሉት የሮኬት ጥቃት ወቅት እንደተናገሩት በግጭቱ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አካባቢዎችን የጥቃታቸው ኢላማ እንደሚያደርጉ አመልክተው ነበር።

ከሃያ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተካሂዶ ከነበረው ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረው ህወሓት እና በኤርትራ መንግሥት መካከል የነበረው ቁርሾ አስካሁን ድረስ ዘልቋል።