ትግራይ ፡ ከባድ የሮኬት ፍንዳታ በኤርትራ መዲና አሥመራ መሰማቱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኤርትራዋ መዲና አሥመራ ከተማ አየር ማረፊያ አካባቢ ቅዳሜ ምሽት የከባድ መሳሪያ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ነዋሪዎችና ዲፕሎማቶች ለቢቢሲ አረጋገጡ።
ፍንዳታው የተሰማው ከአንድ በላይ ተወንጫፊ ሮኬቶች በአስመራ ከተማ ውስጥ መውደቃቸውን ተከትሎ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ስለደረሰ ጉዳትም ሆነ ስለምክንያቱ እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።
ሮኬቶቹ ከትግራይ ክልል እንደተወነጨፉ ሚዲያዎችና ዲፕሎማቶች ተናግረዋል።
አርብ ኅዳር 04/2013 ዓ.ም ምሽት በሰሜን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት በባሕር ዳርና በጎንደር አየር ማረፊያዎች ላይ ከትግራይ ክልል በኩል በተተኮሱ ሮኬቶች በተፈጸመ ጥቃት መጠነኛ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን ለዚህም ጥቃት የትግራይ ክልል ኃይሎች ኃላፊነት መውሰዳቸው ይታወቃል።
ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጋር ወታደራዊ ግጭት ውስጥ የገባው የትግራይ ክልልን የሚመራው ህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ ቴሌቪዥን ላይ ቅዳሜ ዕለት ቀርበው ተጨማሪ ጥቃቶች ሊፈጽሙ እንደሚችሉና ይህም በኤርትራ ውስጥ የሚገኙ የተመረጡ ኢላማዎች እንደሚጨምር አስጠንቅቀው ነበር።
የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በተደጋጋሚ የኤርትራ ኃይሎች የኢትዮጵያ መንግሥትን በመደገፍ ጥቃት እየፈጸሙባቸው መሆኑን የከሰሱ ሲሆን፤ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አቶ ዑስማን ሳልሕ ለሮይተርስ በሰጡት ቃል "በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አንገባም" ሲሉ ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያና ኤርትራ ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት ካደረጉ በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት ተፋጠው ከቆዩ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ሰላም አውርደው ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ።
በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መካከል ለወራት የዘለቀው ውዝግብና ፍጥጫ ከሳምንት በፊት ወደ ወታደራዊ ግጭት ተሸጋግሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸው ይታወቃል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለው በትግራይ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እስካሁን ድረስ ቢያንስ 17 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ግጭቱን በመሸሽ ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን ገብተዋል።
ኤርትራ ውስጥ የተከሰተው
የአሥመራ ከተማ ነዋሪዎች ቅዳሜ ምሽት ተደጋጋሚ ከባድ የፍንዳታ ድምጽ መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንድ ስማቸው ያልተገለጸ ዲፕሎማት "ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በርካታ ሮኬቶች በከተማዋ በሚገኘው አየር ማረፊያ አቅራቢያ መውደቃቸውን ነው" ሲሉ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ተናግረዋል።
የኤርትራ የዜና ድረገጽ የሆነው 'ተስፋ ኒውስ' በትዊተር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው፤ "በህወሓት ቁጥጥር ስር ከሚገኘው የትግራይ አካባቢ የተተኮሱ ሁለት ሮኬቶች አውሮፕላን ማረፊያውን ስተው ከአሥመራ ከተማ ዳርቻ ላይ ወድቀዋል" ብሏል።
ቀደም ሲል የህወሓት ቃል አቀባይ የኤርትራ ኃይሎች ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የፌደራል መንግሥቱን ሠራዊት በጦርነቱ እየተደገፉ መሆናቸውን በመግለጽ ኤርትራ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ አስጠንቅቆ ነበር።
የኤርትራ መንግሥት ግን በግጭቱ ውስጥ ምንም አይነት ሚና እንደሌለው የገለጸ ሲሆን፤ ከትግራይ ጋር በሚዋሰኑ የድንበር አካባቢዎች ውጊያዎች ስለመካሄዳቸውና የቆሰሉ ወታደሮች ኤርትራ ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የሚያመለክቱ ዘገባዎች እየወጡ ይገኛሉ።
ጥቃት በባሕር ዳርና በጎንደር
የኢትዮጵያ መንግሥት በባሕር ዳርና በጎንደር ከተሞች የሚገኙትን አውሮፕላን ማረፊያዎች ኢላማ ያደረገ የሮኬት ጥቃት ባለፈው አርብ መፈጸሙን ቅዳሜ ዕለት ይፋ አድርጓል።
በዚህም አንድ ሮኬት በጎንደር አየር ማረፊያ ላይ በከፊል ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ሰዓት የተተኮሰው ሌላኛው ሮኬት ግን በባሕር ዳር ከሚገኘው አየር ማረፊያ ውጪ መውደቁን አንድ ባለስልጣን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ሁለቱም አየር ማረፊያዎች ለሲቪልና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በሰው ላይ የተደረሰ ጉዳትን በተመለከተ ወዲያው የተሰጠ መረጃ የለም።
ጥቃቱ በቅርቡ ፌደራል መንግሥቱ አማካይነት ለተፈጸሙት የአየር ድብደባዎች የተወሰደ የአጸፋ እርምጃ መሆኑን አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
"በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙት ጥቃቶች አስካልቆሙ ድረስ፤ ጥቃቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ያሉ ሲሆን በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ባደረጉት ቃለምልልስም ተጨማሪ ጥቃቶች እንደሚኖሩ አስጠንቅቀዋል።
የደረሰ ጉዳት
በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መካከል ወታደራዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በመቶዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው የተነገረ ሲሆን፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን የሚያመለክቱ ዘገባዎችም እየወጡ ነው።
የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት የሆነው አምነስቲ ኢንትርናሽናል እንዳለው ባለፈው ሰኞ በማይካድራ ከተማ "በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በስለተማ ነገሮች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን" እንደረጋገጠ ሪፖርት አድርጓል።
አምነስቲ እንዳለው "በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ ጎዳናዎች ላይ የወዳደቁና ሰዎች በቃሬዛ ተሸክመዋቸው የሚታዩ አስከሬኖችን የሚያሳዩ እውነተኝነታቸው የተረጋገጡ ፎቶዎችን" ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለህወሃት አመራሮች ታማኝ የሆኑ ኃይሎችን ለጅምላ ግድያው ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፤ የትግራይ ክልል በበኩሉ እጃችን የለበትም ብለዋል።
በአገሪቱ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተፈጸመውን ግድያ ለመመርመር አጣሪ ቢድን ወደ ስፍራው መላኩን ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የተሰደዱ ሲሆን የሱዳን መንግሥትም በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ አስገባቸዋለሁ ብሏል።
















