ትግራይ ፡ "መቀለ ያለው ትንሹ ወንድሜ መድኃኒቱ እያለቀ ነው" ሐና ዘርኣጽዮን

የፎቶው ባለመብት, Hana Zeratsyon
ትንሽ ወንድም አለኝ። ገና 11 ዓመቱ ነው። የሚጥል በሽታ አለበት። በዚያ ላይ የህብለ ሠረሠር በሽተኛ ነው። ቆሞ መራመድ አይችልም። በተከታታይ የሚወስደው መድኃኒት አለ። ተጨንቄያለሁ። ምክንያቱም መድኃኒቱ በቀላሉ አይገኝም። መድኃኒት ቤቶች ዝግ ናቸው። መድኃኒት ሳልክለትም ጦርነቱ ተቀሰቀሰ።
ትንሹ ወንድሜ መቀለ ነው የሚኖረው። ከቤተሰቦቼ ጋር። የሚገርመው ልክ ጦርነቱ ሊጀመር ዋዜማ በቪዲዮ አውርቼው ነበር። መድኃኒቱን እንደምልክለት ቃል ገብቼለትም ነበር።
ወንድሜ የሚወስዳቸው መድኃኒቶች ውድ ናቸው። በዚያ ላይ ብዙውን ጊዜ መቀለ ያሉ መድኃኒት ቤቶች እነሱን መድኃኒቶች አይዟቸውም።
ለቤተሰብ ብር ልኬ መድኃኒቱን አዲስ አበባ ሲሄዱ በዚያው እንዲገዙለት ቃል ገባሁላቸሁ። ገንዘቡን ቶሎ ብዬ ከዚህ ከምኖርበት ናይሮቢ ላኩላቸው። ሆኖም የላኩትን ገንዘብ ሳያወጡት ባንክ ቤቶች ተዘጉ።
ብሔራዊ ባንክ በትግራይ የሚገኙ ከ600 በላይ የባንክ ቅርንጫፎች በሙሉ እንዲዘጉ ወሰነ።
ቤተሰቦቼ ገንዘቡ አልደረሳቸውም። ወንድሜ መድኃኒቱ አልተገዛለትም። ተጨንቄያለሁ።
ለነገሩ ገንዘቡ ቢደርሳቸው ኖሮም መድኃኒቱን አያገኙትም ነበር እያልኩ በግድ እጽናናለሁ። ምክንያቱም ወደ ትግራይ ማንኛውም በረራ ቆሟል። ይህ ማለት መድኃኒቱን ከአዲስ አበባ ለወንድሜ ሊያመጣለት የሚችል ሰው የለም።
የመንገደኞች በረራ ሙሉ በሙሉ ቆሞ አሁን የአየር ክልሉ የወታደራዊ ጄቶች መናኸሪያ ነው የሆነው።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኖቤል ሎውሬት ዐብይ አሕመድ በትግራይ ሰዎች በሚበዙባቸው ቦታዎች እንዳይገኙ አስጠንቅቀዋል።
የጦር ጄቶች ትግራይ ክልል የሚገኙ የስንቅና ትጥቅ ማከመቻዎችን እንዲደበድብ ትእዛዝ ሰጥተዋል።
የትግራይ ክልል በበኩሉ የትራንስፖርት እንቅስቃሰዎችን በእጅጉ ገድቧል። ገደቡ በአካባቢው ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ተከትሎ የመጣ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው በትግራይ ቢያንስ በስምንት ቦታዎች ጦርነት እየተደረገ ነው። ከእነዚህም አንዱ ሰሊጥ በማብቀል የሚታወቀው ሑመራ ነው።
በዚህ የአጨዳና ምርት የመሰብሰቢያ ጊዜ ከአጎራባች ክልል አማራ የሚመጡ በርከት ያሉ ዜጎች ይሳተፋሉ። አንዳንዴ ሑመራ የሰሊጥ ሥራውን ሳስብ የኢትዮጵያ በብሔር ብሔረሰቦች እጣ ፈንታ እንዴት እንደተሳሰረ ማሳያ ሆኖ ይታየኛል።
አሁን ግን እርስ በርስ ጥርጣሬውና ፍርሃቱ እንዳየለ ነው የምሰማው። በፌዴራል ፖሊስ እና በሠራዊቱ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች እንደሚነግሩኝ ከሆነ መሣሪያዎቻቸውን አስረክበው የግዳጅ እረፍት እንዲወስዱ እየተደረጉ ነው።

ውሃ በፈረቃ
ከ10 ቀናት በፊት ጦርነቱ ሲታወጅ የዓለም ትኩረት ሁሉ በአሜሪካ ምርጫ ላይ ሆኖ ነበር። ደንገት ከወዳጄ አንድ መልዕክት ደረሰኝ።
"ሰማሽ የተፈጠረውን? ቤተሰቦችሽ ጋ ደውለሻል ለመሆኑ?" የሚል ይዘት ያለው መልዕክት።
ወዲያውኑ መደዋወል ጀመርኩ። ቤተሰቦቼ የአንዳቸውም ስልክ አይሰራም። ኢንተርኔቱን ብለው የለም። ለካስ አኔን ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ትግራይ ውስጥ ከሚገኙ ወዳጅ ዘመዶቻችን ጋር ተቆራርጠናል።
ይህ እንዴት አስጨናቂ እንደሆነ ላልደረሰበት ሰው እንዴት ማስረዳት ይቻላል?
አሁን እጅግ እየናፈቀኝ ያለው ትንሹ ወንድሜ ነው። መናገር ስለማይችል በቤተሰቦቼ እገዛ በቪዲዮ እንዲሁ እያየሁ አዋራው ነበር። ላጫውተው እሞክር ነበር። አሁን በጣም ናፈቀኝ። ምንም ማድረግ አልቻልኩም። በናፈቀኝ ቁጥር ስልኬ ላይ ያለውን ፎቶውን አውጥቼ እያየሁ መቋቋም ያልቻልኩት ናፍቆቴን አስታግሳለሁ።
የትንሹ ወንድሜን ፎቶ እያየሁ መጽናናት አልችልም። ምክንያቱም በሽታው አለ። ሕመሙን እያሰብኩ ምነው ይህ ጦርነት ቶሎ በቆመ ስል እቆዝማለሁ። ምነው ጦርነቱ ቶሎ በቆመና ትንሹ ወንድሜ መድኃኒቱን መውሰድ በቻለ።
በዚያ ላይ ስንት ነገር አስቤ ነበር!
ወደዚህ ወደ ናይሮቢ አስመጥቼው የተሻለ ሕክምና ማግኘት የሚችልበትን ዕድል እንዴት እንደማመቻች ሁሉ አስብ ነበር። በሕመሙ ምክንያት መራመድ ስለማይችል ዊልቸር ልገዛለትም እያሰበኩ ነበር።
አሁን ሁሉም ሐሳቤ መና ቀርቷል። ቢያንስ ጦርነቱ እስኪቆም ድረስ ለወንድሜ ያለኝ ህልም እንዲቆም ሆኗል።
ከዚህ የባሰው አስጨናቂ የሆነብኝ ግን ጦርነቱ ቢራዘምስ የሚለው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቀረቡላቸውን የድርድር ሐሳቦች ገሸሽ አድርገዋቸዋል። ህወሓትም ቢሆን ጦርነቱን እስከመጨረሻው ከማካሄድ ላይመለስ ይችላል።
ነገሩ እንዲያ ከሆነ ታዲያ ትንሹ ወንድሜ ምን ሊውጠው ነው? ቤተሰቦቼስ?
በቀጣይ ቀናት የምግብ ዋጋ ይጨምር ይሆን? ከናካቴው የምግብ እጥረት ያጋጥም ይሆን? ቤተሰቦች እንዴት ነው ገንዘብ በእጃቸው ሳይኖራቸው መኖር የሚችሉት? ለምን ያህል ጊዜ?
እንዴት ነው ሌላውስ ቤተሰቡ ከውጭ በሚልክለት ገንዘብ ኑሮውን ሚገፉ ቤተሰብ በቀጣይ ኑሮውን የሚገፋው?
ገና ከአሁኑ የስንዴ ዱቄትና የነዳጅ እጥረት እያጋጠመ እንደሆነ እየተነገረ ነው። ይህ ያስጨንቀኛል።
ከዚህ ሁሉ የባሰው ደግሞ ውሃ ያለመኖሩ ነው።
መቀለ ከአራት እስከ አምስት መቶ ሺህ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ናት። ሆኖም የባንቧ ውሃ የምትመጣው በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ይህም ብርቅ ሆኖ የፈረቃ ሥርጭት አሁን ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።
የውሃ ክፍፍል ሲቋረጥ ነዋሪዎች ስልክ ደውለው በጋሪ ውሃ ያስመጡ ነበር።
አሁን ግን የስልክ ግንኙነት በመቋረጡ እሱም አገልግሎት ተቋርጧል።
ያለ ውሃ ስንት ቀናት ማሳለፍ ይቻላል?
ይህ አልበቃ ብሎ ደግሞ ሐሙስ ለታ ኤሌክትሪክ የሚያመነጨው ግድብ በጦር ጄት ተመቷል እየተባለ ነው። ይህም ነዋሪውን በጨለማ የሚያስቀር ነው የሚሆነው። ነገሩ ሁሉ አስጨንቆኛል።

"ነጭ እንዳትለብሺ"
እነዚህ ጭንቀቶቼ በቂ እንዳልሆኑት ሁሉ ሌላም ነገር ያስጨንቀኛል።
ቤተሰቦቼ በሚኖሩበት ከተማ አደጋ ቢደርስስ? አይበለውና የአየር ጥቃት ቢዘንብስ?
ልጅ እያለሁ የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ሲካሄድ ትዝ ይለኛል። እናቴ ስትደብቀን። የጦር ጄቶች በመጡ ቁጥር በእሷ ቀሚስ ስንከለል ትዝ ይለኛል።
እናቴ ነጭ ልብስ እንዳንለበስ ስትነግረን፤ በሰፈሩ ነጠላ አትልበሱ ሲባል ልጅ ብሆንም በደንብ አስታውሳለው።
ነጠላ አትልበሱ ይባል የነበረው ቦምብ ጣይ ጄቶች በቀላሉ አይተው አደጋ ሊጥሉ ይችላሉ በሚል ነበር።
የሚገርመው ይሄ ነጭ አትልበሱ የሚለው ነገር አእምሮዬ ላይ ተቀርጾ ከመቅረቱ የተነሳ እስካድግ ድረስ ፍርሃት ይሰማኝ ነበር። ካደግኩ በኋላ ነው አእምሮዬ "ኧረ ችግር የለውም" ብሎ ተደፋፍሬ መልበስ የጀመርኩት። የጦርነት ጠባሳ አእምሯዊ ጉዳቱ ከባድ መሆኑን የተረዳሁበት አጋጣሚ ነበር።
ይሄ ታዲያ የእኔ ብቻ ጠባሳ አይደለም፤ ጓደኞቼ ትምህርት ቤታቸው ውስጥ ምሽግ ሲሰራ ያስታውሳሉ። ምሽጉ ይሰራ የነበረው በሌላ ትምህርት ቤት የኤርትራ አውሮፕላን ቦምብ ጥሎ ልጆች ላይ አደጋ በመድረሱ ነበር።
ያኔ ብዙ ሰዎች ሞተዋል። ይህንን መጥፎ ትዝታ እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ማስታወስ አንሻም። ላይመለስ ጥሎን የሄደ፣ ከላያችን ላይ የተራገፈም መስሎን ነበር። ጦርነት እንዲህ ቅርብ ነው እንዴ?
እኔና ጓደኞቼ ብቻ አይደለንም በዚህ ውስጥ ያለፍነው። የእኛ ወላጆችም ሆነ የእኛ አያቶች የሌላ የእነሱ ዘመን የጦርነት ትዝታ አላቸው። የመንግሥቱ ኃይለማርያም ጦርነት፣ የኃይለሥላሴ ጦርነት። ከጦርነት ወደ ጦርነት።
የእኔ ከተማ መቀለ ብዙ ታሪኳና ትዝታዋ ከጦርነት ብዙም አይርቅም። ማብቂያ የሌለው ጦርነት፤ መቋጫ የሌለው አዙሪት።

የፎቶው ባለመብት, AFP
"እጮኛዬን ላገባው ቀጠሮ ነበረኝ"
የሚገርመው በሚቀጥለው ወር ገና በዓልን ከቤተሰቦቼ ጋር ለማክበር ቀጠሮ ነበረኝ።
በዚያውም ከእጮኛዬ ጋር ለመጋባት እያቀድን ነበር።
እኔ ከዓመታት በፊት ወደ ናይሮቢ ስመጣ እሱ እዚያው መቀለ ቆየ። አሁን ጦርነቱ ድንገት መሀላችን ገባ። በእኔና በትንሹ ወንድሜ መሀል፣ በእኔና በቤተሰቦቼ መሀል፣ በእኔና በፍቅረኛዬ መሀል። ጦርነት ህልም ነጣቂ ነው።
ይህንን ስል አባቴን አስታወሰኝ።
አባቴ አናጺ ነው። እሱም እንደኔው ጦርነት ቆርጦታል። ሕልሙን።
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር ድንገት ነበር ከእህቱ ጋር የተቆራረጠው። ኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበራቸውን ዘጉ። ለ20 ዓመት እህቱን እንዴት እንደሚናፍቃት ሲናገር ሰምቼዋለው። ለድፍን 20 ዓመት።
ከ2 ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኤትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ሰላም ፈጥረው ለጊዜውም ቢሆን ድንበር ሲከፈት አባቴ እህቱን ሊያገኛት ጓጓ። ጉጉቱ እጅግ ከፍተኛ ነበር። መሞቷ ተነገረው። ሕልሙ ሟሸሸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማስፈን ላደረጉት ጥረት ታላቁን የኖቤል ሽልማት በኦስሎ ሲቀበል እንዲህ ብለው ነበር።
"ጦርነትን ለመቀስቀስ ጥቂት ሰዎች ይበቃሉ። ሰላም ለመፍጠር ግን መንደር፣ አገር መሰለፍ አለበት። ለእኔ ሰላም ማምጣት ልክ እንደ ችግኝ ነው የምመለከተው። ችግኝ እንዲጸድቅና ዛፍ እንዲሆን ውሃ ማጠጣትና አፈር መኮትኮት እንደሚሻው ሰላምም የማያወላዳ ቁርጠኝነት፣ እልህ አስጨራሽ ትዕግስት እና ቀናነትን ይሻል።"
እንደ አብዛኛው ሕዝብ እኔም ዐቢይ አሕመድና ደብረጽዮን ሰላም እንዲያመጡ እመኛለሁ።
አለበለዚያ የጥላቻ ችግኝ ይጸድቃል። ያ ደግሞ አገር ያሳጣናል።
ከዚህ ሁሉ የሐሳብ መኳተን በኋላ ታዲያ አሁንም ወደ አእምሮዬ የሚመጣው ትንሹ ወንድሜ ነው። መድኃኒቱን ማግኘት አለበት።
ዶ/ር ዐቢይ፣ ዶ/ር ደብረጺዮን፤ ለትንሹ ወንደሜ መድኃኒቱን ስጡት።















