"በትግራይ ክልል የተካሄደው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ተጠናቋል" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

የፎቶው ባለመብት, PMAbiyAhmedAli

የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት የትግራይ ክልል ዋና ከተማን መቀለ መቆጣጠሩ ከተገለጸ በኋላ ሲያካሂድ የነበረው ዘመቻ መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሐሙስ ሠራዊቱ የመጨረሻው ምዕራፍ ያሉትን "ሕግ የማስከበር ዘመቻ" እንዲያካሂድ ካዘዙ በኋላ ቅዳሜ ኅዳር 19/2013 ዓ.ም የክልሉን ዋና ከተማ የፌደራል ሠራዊቱ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩ ተገልጿል።

ሠራዊቱ ቀደም ባሉት ቀናት ውስጥ በመቀለ አቅራቢያ ያሉ ከተሞችንና አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ ቅዳሜ ዕለት ነበር ወደ ከተማዋ የገባው።

የሠራዊቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጀኔራል ብርሀኑ ጁላም በሰጡት መግለጫ በከተማ ነዋሪ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ በተካሄደ ዘመቻ ሠራዊቱ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ መቀለን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የዘመቻውን መጠናቀቅ በገለጹበት መልዕክታቸው የፌደራል ፖሊስ በሕግ የሚፈለጉ የህወሓት አባላትን በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ እንደሚያከናውን ገልጸው "ቀጣይ ትኩረታችንም ክልሉን መልሶ መገንባትና ሰብአዊ ድጋፎችን ማድረስ ነው" ብለዋል።

ሠራዊቱ መቀለን በተቆጣጠረበት ጊዜ የግጭቱ መነሻ ነው የተባለውና በህወሓት ኃይሎች ጥቃት እንደተፈጸመበት የተነገረውን የሠሜን ዕዝ ካምፕን መያዙን እንዲሆም በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ የዕዙ አባላትን ማስለቀቁ ተገልጿል።

መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ የሰላማዊ ሰዎች ደኅንንትን በጠበቀ ሁኔታ ወደ መቀለ የገባው የፌደራል ሠራዊት የከተማዋን አየር ማረፊያና የክልሉን አስተዳደር ጽህፈት ቤትን ጨምሮ ቁልፍ ሕዝባዊና ሌሎች ተቋማትን በዋናነት መቆጣጠሩ ተገልጿል።

መቀለ በመንግሥት ሠራዊት መያዟ ከተገለጸ በኋላ የህወሓቱ መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደገለጹት "የእራስን እድል የመወሰን መብታችንን ለመከላከል ወራሪዎችን እስከ መጨረሻው እንታገላቸዋለን" ብለዋል።

ደብረጽዮን ለሮይተርስ በአጭር ጽሁፍ መልዕክት ላይ መቀለን በተመለከተ ስላለው ሁኔታ በቀጥታ አስተያየት ባይሰጡም የመንግሥት ኃይሎችን በመጥቀስ "የፈጸሙት ተግባር እስከመጨረሻው እነዚህን ወራሪዎቹን እንድንፋለማቸው ያደርገናል" ብለዋል።

መቀለ

ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች አሏት የምትባለው መቀለ የትግራይ ክልል አስተዳደር መቀመጫ ስትሆን የክልሉ ትልቋ ከተማ ናት። የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችና ቀደም ሲል በፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ይገኙ የነበሩ ባለስልጣናት መቀመጫቸው መቀለ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረው ህወሓት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው አለመግባባት ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ መካረሩ ይታወሳል።

ተከትሎም የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ባለመቀበል ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደው የተናጠል ምርጫ የፌደራል መንግሥቱን ተቀባይነት ካለማግኘቱ በተጨማሪ በአገሪቱ ምክር ቤቶች ሕገ ወጥ ተብሎ ውድቅ ተደርጓል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የክልሉን አስተዳዳሪዎች ሕገ መንግሥቱን በመጣስና ከሕግ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል በማለት የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል ክልል አስተዳደር ጋር የነበረውን የቀጥታ ግንኙነት አቋርጦ የበጀት ዕቀባ ጥሎ ነበር።

አለመግባባቱና መካሰሱ ያለማቋረጥ በቀጠለበት ሁኔታ ጥቅም 23/2013 ዓ.ም ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትግራይ ክልል በነበረው የፌደራሉ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ይፋ ካደረጉ በኋላ የፌደራሉ ሠራዊት በትግራይ ክልል ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይታወሳል።