ትግራይ፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ አሳሰቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, PM Office

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ለህወሓት መሪዎችና ኃይሎች የሰጡት ጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ አሳሰቡ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ ባወጡት መግለጫ "የወዳጆቻችን ስጋት እና ምክረ ሃሳብ ከግምት እያስገባን፤ በውሳጣዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግን ጥረትን አንቀበልም። ስለዚህም ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ተቀባይነት ከሌላው እና ሕጋዊ ካልሆነ ጣልቃ ገብነት እንዲቆጠብ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ጣልቃ-አለመግባት መሠረታዊ ምርሆዎችን እንዲያከብር በአክብሮት እናሳስባለን" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ያሉት የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ መቀለ መቃረቡን ተከትሎ በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የህወሓት አመራሮች እና ተዋጊ ኃይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ የሰጡት የ72 ሰዓታት ሊገባደድ በተቀረበበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጡት ቀነ ገደብ ሲጠናቀቅ በሚኖረው ወታደራዊ ዘመቻ በርካቶች ስጋት ገብቶናል እያሉ ነው።

የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በተቀመጠው ቀነ ገደብ እጃቸውን እንዲሰጡ የቀረበላቸውን ጥሪ እንደማይቀበሉት መግለጻቸው ይታወሳል። የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ " ክልላችንን እራሳችን ለማስተዳደር መስዋትነት እንከፍላለን" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በትግራይ በኩል ላሉ ኃይሎችና ለህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ያስቀመቱት የጊዜ ገደብ ዛሬ ረቡዕ አመሻሽ ላይ የሚያበቃ ይሆናል።

ይህ ተከትሎ ነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የመጨረሻ ይሆናል ባለው ዘመቻ በመቀለ ሊከሰት የሚችለው ሁኔታ ከወዲሁ አሳስቦኛል ያለው።

ድርጅቱ የጦር ወንጀል ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት እንዳለውም ከወዲሁ አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን በመግለጫቸው "ሕግ በማስከበሩ ሥራ" ንሑሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም የተለያዩ አገራት መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት ኃሎች ግጭቱን አብርደው ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ሊወያይ እንደሚችል የሚጠቁሙ ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ማሞ ምህረቱ ግን ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ "ከወንጀለኞች ጋር አንመካከረም . . . ለፍትሕ እናቀርባቸዋለን። በጠረጴዛ ዙሪያ ከእነርሱ ጋር የሚደረግ ድርድር የለም" ብለው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩም በመግለጫቸው "የዓለም አቀፍ የሕግ ሥርዓት መሠረት በሉዓላዊ አገር ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባት" መሆኑን አስታውሰው፤ ይህም በተባበሩት መንግሥታት መቋቋሚያ ቻርተር ላይ መስፈሩን ጠቅሰዋል።

በዚህም መሠረት ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ግንባታ ላይ እክል ሆኖ ቆይቷል ባሉት ቡድን እና በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በሰነዘረው ኃይል ላይ የሚወሰደውን እርምጃ፤ "ሕግን የማስከበር እና ጥፋተኞችን ወደ ሕግ የማቅብ ነው" ብለዋል።

"ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ ሕግን የማስከበር ሙሉ መብት አላት - እያደረግን ያለውም ይህው ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባትና መካሰስ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መባባሱ ይታወሳል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደ ግጭት ማምራቱ ይታወሳል።

ባለፉት ሳምንታት በተካሄዱት ወታደራዊ ዘመቻዎች የመንግሥት ኃይሎች የተለያዩ ከተሞችን መያዛቸው የተነገረ ሲሆን በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ አቅራቢያ መድረሳቸውም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ መቀለ የአገሪቱ ሠራዊት ከመንቀሳቀሱ በፊት ሊደርስ ይችላል የተባለ ጉዳትን ለማስቀረት የትግራይ ክልል ኃይሎችን የህወሓት አመራሮች እጃቸውን እንዲሰጡ ዛሬ ረቡዕ ምሽት የሚያበቃ የ72 ሰዓታት የጊዜ ገደብ አስቀምጠዋል።